ሀገሪቱ በከፍተኛ የፖለቲካና የፀጥታ ቀውስ ውስጥ ገብታ ህዝባዊ አመፅ በበረታበት ወቅት የደህንነት መስሪያቤቱ ሹማምንት በውጪ ሀገር ካሉ የዲፕሎማቲክ ሰራተኞች ጋር በመመሳጠር አድንዛዥ ዕፅን ጨምሮ ከፍ ባለ ህገወጥ ንግድ ላይ ተሰማርተው እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ነው። ህገወጥ ንግዱ በዲፕሎማሲ ቀረጥ ያለመክፈልና ያለመፈተሽ ከለላ የሚከናወን ነበር። ዋዜማ በጉዳዩ ላይ ምርመራ ሲያደርጉ ከነበሩና ጉዳዩን በቅርበት ከሚያውቁ ያሰባሰበችውን መረጃ አንብቡት

Ethiopian Protest 2016-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- በ2009 አ.ም በብሄራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ስም ወደ ሀገር ውስጥ በገፍ እየገባ የሚቸበቸበው እንዲሁም ወደ ሌላ ሀገር የሚወጣው ንብረት በርካታ ነበር። ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው በደህንነት ተቋሙ ስም እቃ እያስገቡ ሀገር ውስጥ መሸጥና ወደ ሌላ ሀገር መላክ የተለመደ ቢሆንም ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ሲታይ የነበረው ግን ከማንኛውም ጊዜ የከፋ ነበር። ከዚህ ውስጥ ከዱባይ የመጣው 350 ኪሎ ግራም የሚመዝን ንብረት ይገኝበታል። ይህ እቃ የዲፕሎማሲ ስራ የሚያስገኘውን ያለመፈተሽና ክፍያ ያለመፈጸም ሕጋዊ ከለላ በመጠቀም ነው የገባው።

ሆኖም በወቅቱ ከነበረው ጥርጣሬ አንጻር የንብረት ምልልሱ የበዛባቸው የደህንነት ሰራተኞች በዲፕሎማሲ እና ደህንነት ስም የሚመጣውን ንብረት ሲፈትሹ ይህ 350 ኪሎ ግራም የሚመዝን እቃ ትኩረታቸው ውስጥ ይገባል። ጭነቱ ዱባይ ባለው የኢትዮጵያ ቆንጽላ ጽህፈት ቤት በኩል የተላከና የተረከበውም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ሲሆን; የጭነቱ መልእክት ተፈርሞ የወጣውም በቆንጽላው ልዩ ጽህፈት ቤት ሀላፊው በአቶ ሙሉጌታ መኮንን በኩል ነበር። የመረጃ ምንጮቻችን እንደነገሩን ይህ ንብረት በወቅቱ የብሔራዊ የመረጃና የደንነት አገልግሎት ዋና ዳይረክተር የነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ ሙሉ ዕውቅና የተሰጠው ነበረ። 

ጭነቱ ሲፈተሽ የተጻፈበት ዝርዝር ላይ ለአገር ደህንነት የሚውሉ የተለያዩ የኮምፒውተርና የኤሌክትሮኒክስ መሳርያዎች የሚል ጽሑፍ ሰፍሮበት ነበር። ይህ ጽሑፍ ስላለበትም የአየር መንገዱ የጉምሩክ ሰራተኞችና የደህንነት ሰዎች ጭነቱን ያለፍተሻ እንዲያልፍ ያደርጉታል። በንብረቱ ርክክብ ወቅት ግን ሁለት አጠራጣሪ ነገሮች ተከሰቱ። አንደኛው ጉዳይ ጭነቱ ከአየር ማረፊያው ርክክብ ተፈጽሞበት ሲወጣ የተጓጓዝው በግለሰብ የኪራይ መኪና መኾኑ ነው። እንደ አሰራሩ ከአገር ደህንነት ጋር ተያይዞ የሚገባ እቃ በራሱ የብሔራዊ ደህንነት መስሪያ ቤት መኪና እንጂ በግለሰብ መኪና አይጓጓዝም። ሁለተኛው አጠራጣሪ ጉዳይ ደግሞ ይህ ለአገር ደህንነት ተብሎ የመጣ ንብረት በተቋሙ ግቢ ውስጥ መግባት ሲኖርበት ላምበረት አካባቢ ባለ አንድ የግለሰብ ግቢ ውስጥ እንዲራገፍ መደረጉ ነበር።

ይህን ያዩ የደህንነት ሰራተኞች ጭነቱ እንዲመረመር ያደርጋሉ። ጭነቱ ሰፈተሽም አገር ውስጥ ሲገባ ከተጻፈው የንብረት ዝርዝር ይልቅ ኮኬይን፥ ወርቅ እና የተለያዩ አገራት ገንዘብ መሆኑ ይደረስበታል። ጭነቱ ውስጥ የተገኘው ኮኬይን የተሰኘው አደንዛዥ እጽ በአሜሪካ አውሮፓና መካከለኛው ምስራቅ አገራት ውስጥ በድብቅ የሚዘዋወር እና በከፍተኛ ገንዘብ በሕገወጥ ገበያ የሚሸጥ እነው። ነገር ግን ከጭነቱ ውስጥ ምን ያክሉ ወርቅ; ምን ያክሉ ኮኬን እንዲሁም ምን ያክሉ የውጭ ምንዛሪ ነበር የሚለው እስካሁን ባይገለጥም ከፍተኛ መጠን እንደነበረው ከንብረቱ ሚዛን ትልቅነት ግምት ተወስዷል።

የቅብብል ሰንሰለቱን በቅጡ ያልተረዱት የደህንነት ሰራተኞች የንብረቱን ምንነት ከማወቅ በዘለለ በምርመራው መግፋት አልቻሉም ነበር። በወቅቱም የምርመራ ስራቸውን ሳያጠናቅቁ እንዲያቆሙ ተደርገዋል። በመረጃውም መሰረት ስራቸውን እንዲያቆሙ የተደረገው አማኑኤል ኪሮስ የተባለ የደህንነት አመራር ጉዳዩ ላይ ወደፊት ሰፋ ያለ ዘመቻ እንደሚደረግና የአሁኑ ምርመራ ግን እንዲቋረጥ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ አዘዋል የሚል ከደህንነት ሹሙ ከጌታቸው አሰፋ የወረደ ትእዛዝ በማቅረብ ነበር። ይሁንና የተባለው ሰፊ ዘመቻ አልተካሄደም። በጥፋተኞቹም ላይ ርምጃ ሲወሰድ አልታየም።

ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ የቀድሞው የብሔራዊ የመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት በኢትዮጵያ ካሉ የተለያዩ የዲፕሎማሲ ተቋማት ጋር ያደርጋቸው የነበሩ ህገ ወጥ ንግዶች ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ፈታኝ ሆነው እንደነበረ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዋዜማ አስታውቀዋል።

የመረጃ ምንጮቻችን እንደነገሩን በአፍሪካ ህብረት ስም; በኢንዶኔዥያ፥ በናይጄሪያ፥ ቱኒዝያ; የተባበሩት አረብ ኤምሬት; በአልጄሪያ; በሱዳንና በቻይና ኤምባሲዎች ስም ያለመፈተሽ መብትን ጥቅም ላይ በማዋል የንግድ እቃዎች በሕገ ወጥ መንገድ አገር ውስጥ እየገቡ ፈተና ደቅነው ነበር። ዲፕሎማሲን ከለላ አድርጎ ሲፈፀም የነበረውንና የአገሪቱን ክብርና ተዓማኒነት የሚያጎድፍ ተግባር አደገኛ እንደነበረም ምንጮቻችን ጨምረው ይናገራሉ። 

በየመን ኤምባሲ ስም የቀድሞውን የብሔራዊ የመረጃ እና የደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ ሀላፊዎችን ጨምሮ 20 ግለሰቦች የተካተቱበት ከፍተኛ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እንደነበረና የወርቅ፥ የውጭ ምንዛሪ፥ የጦር መሳርያና የመድሀኒት ህገ ወጥ ንግድ ላይ በሰፊው ይንቀሳቀሱ እንደነበር ዋዜማ ከሶስተኛ አገር ጭምር የተገኘ መረጃ አላት። ለአብነት በ2009 አ.ም በየመን አምባሲ ስም አራት ኮንቴይነር እቃ በጅቡቲ በኩል ሊገባ ሲል ተይዟል። እንደ ደህንነት ምንጮቻችን መረጃም የቀድሞው የደህንነት መዋቅር ከሰብዓዊ መብት ጥሰትና አፈና ባሻገር በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ፈተናዎችን ደቅኖ ቆይቷል። [ተጨማሪ የድምፅ መረጃ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/mSvuxU4iA5A