ዋዜማ ራዲዮ- በፋና ቴሌቭዥን ሲቀርብ የነበረውና በይዘቱ ፖለቲካዊ ሽሙጥ ላይ ያተኮረው ምን ልታዘዝ ሳምንታዊ ድራማ “በተደረገበት የተቀነባበረ ዘመቻ” ለመቋረጥ መገደዱን የድራማው አዘጋጆች ለዋዜማ ተናገሩ።


ከድራማው ፀሃፊዎች አንዱ የሆነውና የፊልም ባለሙያ በኋይሉ ዋሴ (ዋጀ) እንደነገረን ያለፉትን ወራት የገጠሟቸው ፈተናዎች በተቀነባበረ መልክ ወደ ህዝብ ተመልሰው እንዳይቀርቡ እንዳደረጋቸው ይገልፃል።


ድራማውን በፋይናንስ ሲደግፍ የነበረውና የድራማው ተባባሪ አዘጋጅ የሆነው አያልነህ ተሾመ ለ17 ቀናት ያህል በፖሊስ ተይዞ መታሰሩንና በዋስ መለቀቁን ዋዜማ ከፖሊስ ከምንጮቿ ሰምታለች።
አያልነህ የታሰረው ለምን እንደሆነ ያልተገለፀለት ሲሆን ፍርድ ቤትም ሳይቀርብ ቆይቶ በዋስ መለቀቁንና በምርመራ ወቅት ምን ልታዘዝ ድራማን ማን በፋይናንስ እንደሚረዳው ጥያቄ ቀርቦለት እንደነበር ስምተናል።


ምን ልታዘዝ በነፃ በተገኘ የግለሰብ መጋዘን ውስጥ ቀረፃው ይካሄድ የነበረ ሲሆን ሁለት ስፖንስሮችም ይደግፉት ነበር፣ አዋሽ ባንክና ኖህ ሪል ስቴት። ድርጅቶቹ በሳምንት ልዩነት ድጋፋቸውን ያቋረጡ ሲሆን ሌሎች ስፖንሰሮችም ድጋፍ ለማድረግ ከመጡ በኋላ በድንገት ሀሳባቸውን ቀይረው ይመለሱ እንደነበርም ተረድተናል።


ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት ጋር ተከትሎ የተጀመረው ምን ልታዘዝ ድራማ የሀገሪቱ የሚዲያ ነፃነት ትኩሳት መለኪያ ተደርጎ ሲታይ ቆይቷል፣ በተለያዩ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀንም ሽፋን አግኝቷል።


ድራማውን የሚያስተላልፈው ፋና የገዥው ፓርቲ ንብረት ሲሆን ወትሮ ሕወሐት መር ለነበረው መንግስት ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቶ ከለውጡ በኋላ አሰላለፉን አስተካክሎ ራሱን ነፃ ሚዲያ ለማድረግ ሞክሯል። ምን ልታዘዝ በፋና ላይ የተጀመረው በዚህ የሽግ ግ ር ወቅት ነበር።

ምን ልታዘዝ የሚያቀርባቸው ሽሙጦች ትኩረታቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ ላይ መሆኑ ያልተዋጠላቸው የፋና የስራ ሀላፊዎች የድራማው ይዘት ላይ ሳንሱር ለማድረግ ይሞክሩ እንደነበርና በዚህም ከድራማው አዘጋጆች ጋር ተደጋጋሚ ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ እንደነበር የፋና ባልደረባ ለዋዜማ ትገልፃለች።


በፓርቲ የተደራጁ የፋና ጋዜጠኞች ድራማው እንዲቆም ግፊት ሲያደርጉ እንደነበርና ሌሎች ሀላፊዎች ደግሞ ምን ልታዘዝ መቅረቡ ተዓማኒነታችንን ስለሚጨምር በዚሁ ይቀጥል ባይ ነበሩ።


ምን ልታዘዝ 38 ክፍሎችን አቅርቦ ለሁለተኛ ዕረፍት ሲቋረጥ ግን ፋና ውል ማቋረጡን እንኳን ሳይነግራቸው በምትኩ በተመሳሳይ ስዓት አዲስ ድራማ ማስተላለፍ መጀመሩን በኋይሉ ዋሴ ለዋዜማ ገልጿል።


ፋና በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ለሀላፊዎቹ ጥያቄ አቅርበን ምላሻቸውን ለሁለት ቀናት ጠብቀናል፣ እስካሁን ምላሽ አላገኘንም።


“ለሀገር የሚጠቅም፣ የመናገር ነፃነትን የሚያበረታታ የተሻለ ስራ ሰርተን ለተመልካቹ ማሳየት እንፈልጋለን። አሁን ባለው ሁኔታ በፋና ተመልሰን እንደማንመጣ ግልፅ ሆኗል። ሌሎች የግል ሚዲያዎችም ምን ልታዘዝን ለመቀበል የሚደፍሩ አይደሉም። ስለዚህ በድረ ገፅ ወደ ተመልካች ለመድረስ ሀሳብ አለን” ይላል በኋይሉ። [ዋዜማ ራዲዮ]