Meles Alem, MoFA spokesperson
Meles Alem, MoFA spokesperson

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ መንግስት ከሳዑዲ አረቢያ በ90 ቀናት ውስጥ እንዲወጡ የሚደረጉ ኢትዬጵያዊያን የመገልገያ እቃዎቻቸውን ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገቡ ውሳኔ አስተላለፈ።
የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንደተናገሩት ተመላሽ ኢትዬጵያዊያኑ የሚያስገቧቸውና ቀረጥ የማይጠየቁባቸው የመገልገያ ቁሳቁሶች 21 አይነት ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ  በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ መንግስት የሚሲዬን ፅ/ቤቶች ከሆኑት ከሪያድና ከጂዳ በተጨማሪ በ7 ቦታዎች ለተመላሽ ኢትዬጵያዊያኑ የሚሆን የጉዞ ሰነድ ማዘጋጃና መመዝገቢያ ማዕከላት  መዘጋጀታቸውን ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።

የተፈቀዱት የዕቃ አይነቶች ለቤት ውስጥ መገልገያ የሚሆኑ ቁሳቁሶች፣ ሳተላይት ዲሽ፣ ፍሪጅ፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽን ፣ቴሌቭዥንና ለአንድ ሙሉ ቤተሰብ ቅያሪ ልብሶችን ያካትታል።
ብዙዎቹ ተባራሪዎች ያዛን ያህል ከፍ ያለ ዋጋ ያለው ንብረት ያላፈሩና ይልቁንም በችግር የዕለት ኑሯቸውን የሚገፉ ዜጎች ይገኙበታል። አንዳንዶቹ የፖለቲካ ስደተኞች ሲሆኑ በፍፁም ወደሀገር ቤት የመመለስ ፍላጎት የላቸውም።
የሳዑዲ መንግስት ከአንድ ሚሊያን በላይ የውጪ ሀገር ዜጎች ሀገሩን ለቀው እንዲወጡ የሶስት ወር የጊዜ ገደብ አስቀምጧል። አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ከሁለት አመት ያላነሰ በእስር ላይ ሲሆኑ በዚህ የምህረት ዕድል ተጠቅመው ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ተነግሯቸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ተጠቅመው ከሳዑዲ እንዲወጡ እያሳሰበ ሲሆን፣ በገደቡ ያልወጣ ዜጋ ለሚገጥመው ማናቸውም ችግር መንግስት ድጋፍ ለማድረግ ይቸግረኛል ብሏል።