KSA expel foreignersዜማ ራዲዮ- ከሳዑዲ አረቢያ የሚመለሱ ዜጎችን በራሴ አቅም ተቀብዬ አቋቁማቸዋለሁ ሲል የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት ከለጋሾች 90 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ካልተገኘ ስራውን ለማከናወን እንደሚቸገር አስታወቀ።

የሳውዲ አረብያ መንግስት ህገ ውጥ የሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎች ሀገሩን ለቀው እንዲወጡ በሰጠው የ90 ቀናት የምህረት ጊዜ ውስጥ ይመለሳሉ ተብለው ለተገመቱ 250 ሽህ ኢትዬጵያዊያን ወጭ የሚሆን ከ85 እስከ 90 ሚሊዬን ዶላር እንደሚያስፈልገው መንግስት ለአለም አቀፍ ተቋማትን በሚስጢር መጠየቁን ዋዜማ ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች አረጋግጣለች።

በሀገሪቱ ስምንት ሚሊየን ወገኖች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ በሚፈልጉበት በዚህ ወቅት ከለጋሾች ተጨማሪ ያውም የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ቀላል እንደማይሆን በረድዔት ድርጅት በሀላፊነት የሚሰሩ ባለሙያ ሀሳባቸውን ነግረውናል።
ከሳውዲ ይመለሳሉ ተብሎ የሚጠበቁትን ኢትዬጵያዊያንን በተመለከተ ጠ/ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝም ሆኑ ሌሎች ባለስልጣናት ይመጣሉ ተብለው ከሚጠበቁ ዜጎች ቁጥር ውጭ ስለሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን በግልፅ አለመናገራቸው በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ዙሪያ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ግራ አጋብቶ መቆየቱን የገለፁት ምንጮች በሚስጢር የተነገራቸውና ያስፈልጋል የተባለው የገንዘብ መጠን ከፍ ያለ መሆኑ ተጨማሪ ግራ መጋባት እንዳስከተለባቸው ለዋዜማ ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የበላይነት የተመሰረተው እና ልዩ ልዩ የመንግስት ተቋማትን የያዘው ሀገር አቀፍ ኮማንድ ፓስት የክልል መንግስታት ለተመላሾቹ የስራ እድል እና አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ተመላሾቹን እንዲቀበሉና ተመላሾቹ ወደ ክልላቸው ሲመለሱ መስራት በሚመርጡት ዘርፍ ቅድሚያ እንዲሰጧቸውና  የስራ መጀመሪያ ካፒታልም በብድር እንዲያቀርቡላቸው ጥብቅ መመሪያ ማስተላለፉን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግስት ለተመላሾቹ ያስፈልገኛል ብሎ በሚጥር አለም አቀፍ ተቋማቱን የጠየቀው የገንዘብ መጠን ብዛትና የጉዳዩ ሚስጢራዊነት እንዳልገባቸው የገለፁት ምንጮች ተመላሾቹን በተመለከተ ከመግስት ጎን በመሆን የሚያደርጉትን እንቅስቃሴም በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሀኖች መግለጫ እንዳይሰጡም እንደተነገራቸው ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከሳውዲ ተመላሽ ኢትዬጵያውያንን በተመለከተ እና በሀገር ላይ የሚያመጣውን ተፅዕኖን     በሚመለከት የሀገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሀን ተቋማት ተገቢውን ሽፋን እየሰጡ አይደለም ብሎ እየወቀሰ  እንዴት አስፈላጊውን በጀት በይፋ መግለፅ ተስኖት በሚስጢር ድጋፍ ሰጭ ተቋማትን  ለመጠየቅ ፈለገ ሲሉም ምንጮች ለዋዜማ ጥያቄ አቅርበዋል።

የሳውዲ መንግስት ከሰጠው የ90 ቀናት የምህረት ጊዜ ውስጥ ከ50 ቀናት በላይ የተቆጠረ ሲሆን እስከ አሁን ሀገር ቤት የተመለሱትና ለመምጣት የጉዞ ሰነድ የወሰዱ ኢትዬጵያዊያን ቁጥር ከ20  ሺህ አይበልጥም።