Protesting refugees sleeps infornt of UNHCR  office
Protesting refugees sleeps infornt of UNHCR office

(ዋዜማ) መዕዲ በግብጽ ካይሮ የምትገኝ እና ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባት ቦታ ናት፡፡ እንደ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሁለቱ ወንድማማቾች ነሲቡ እና ቶፊቅ አብደላ የሀገራቸው ሰው በበዛበት በዚያ አከባቢ ቤት ተከራይተው የስደት ኑሯቸውን ይገፋሉ፡፡ መነሻቸው ከምስራቅ ኢትዮጵያ የሆኑት ሁለቱ ወንድማማቾች በአንድ ነገር ላይ ሁሌም አይስማሙም፡፡

ከዓመት በፊት ካይሮ የደረሰው ታናሽዬው ቶፊቅ ቀደም ብሎ ወደ ግብጽ የመጣውን ታላቁን በቶሎ ወደ አውሮፓ እንዲያሻግረው ቢጎተጉተውም ነሲቡአሻፈረኝብሎ ቆይቷል፡፡ ገለምሶ አቅራቢያ በምትገኘው ሚልካዬ በተሰኘች አነስተኛ ከተማ በንግድ ስራ ተሰማርቶ የነበረው ቶፊቅ በወንድሙ እምቢታ ቅሬታ አዝሎ ቆይቷል፡፡   

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በተነሳው ተቃውሞእጅህ አለበትተብሎ ሲፈለግ ሀገሩን ጥሎ የተሰደደው ቶፊቅ አውሮፓ የመግባት ትልሙን ትቶ በተቀመጠበት ከታላቅ ወንድሙ አንድ ግብዣ ይቀርብለታል፡፡ ቀኑ መጋቢት 29 ቀን 2008 .ም፣ ግብዣው ደግሞ ወደ አውሮፓ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያንን መሸኘት ነበር፡፡ በመኪና ስድስት ሰዓት የሚወስደውን ከካይሮ እስከ አሌክሳንድሪያ የተንጣለለውን መንገድ ከወንድሙ ጋር ተጉዞ ኢትዮጵያውያንን ለመሰናበት ተስማማ፡፡

አሌክሳንድሪያ ሲደርሱ ግን ቶፊቅ ያልጠበቀውን ዜና ከወንድሙ ሰማ፡፡ለተጓዦቹ ኢትዮጵያውያን የሚሰጥ ነውተብሎ በሻንጣ የተሸከፈ ልብስ የእርሱ መሆኑን እና የዛን ዕለት ምሽት ጉዞ በምትጀምረው ጀልባ ተሳፍሮ ወደ አውሮፓ እንደሚጓዝ ተነገረው፡፡ ቶፊቅ በወንድሙ የቀረበለትን ድንገቴ (surprise) አላመነም፡፡

ምንም እንኳ ወደ አውሮፓ የመጓዝ ፍላጎት ቢኖረውምእንዴት ሳልዘጋጅ?…ጓደኞቼን ሳልሰናበት?” ሲል ከወንድሙ ጋር ተከራከረ፡፡ ነገር ግን አንዴ የተቆረጠ ጉዳይ ሆኗልና ከታላቁ ጋር በለቅሶ ተሰናባብቶ ወደ ጀልባው አመራ፡፡

ከግብጽ ወደ ጀርመን አሊያም ጣሊያን ስደተኞችን በድብቅ ለማስገባት ሁለት ሺህ ዶላር በነፍስ ወከፍ የሚቀበሉት አጓጓዦች ቶፊቅን እና ሌሎች ኢትዮጵያውያንን በአነስተኛ ጀልባ አሳፍረው 24 ሰዓት ጉዞ በኋላ ወደሚደርሱባት መርከብ መገስገስ ቀጠሉ፡፡ ኢትዮጵያውያኑ አየሩ ከሰጠ ከሳምንት በኋላ፤ ማዕበል ካስቸገረ ደግሞ በስምንተኛው ቀን አውሮፓ እንደሚደርሱ ተገምቷል፡፡

ይህንን ትንበያ በልቡ ይዞ ወደ ካይሮ የተመለሰው ነሲቡ እንደ እርጉዝ ሴት ቀን ከመቁጠር አልፎ የደላላዎች ሞባይል ላይ እየደወለ የወንድሙን ነገር ማጠያያቁን አላቋረጠም፡፡ እነርሱም ተስፋ ከመመገብ አልቦዘኑም፡፡ ወንድሙን የያዘው መርከብ ቅዳሜ ሚያዝያ 8 አውሮፓ እንደሚደርስ በእርግጠኝነት ደጋግመው ይነግሩታል፡፡

የተባለው ቀን አለፈ፡፡ ቀጣዩ ቀን ግን ጥሩ ዜና ይዞ አልመጣም፡፡ ነሲቡ ከወንድሙ ጋር አብሮት ከተጓዘ ኢትዮጵያዊ አንደበት የመርከቡን የመገልበጥ አደጋ እና የብዙ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ማለፍ በስልክ ሰማ፡፡ ከሟቾቹ ውስጥ ታናሹ ቶፊቅም አንዱ መሆኑን ተረዳ፡፡ ከጓደኞቹ ጋር እየተጋገዘ ስለ አደጋው ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ሞከረ፡፡

ወደ 300 ገደማ ሰዎችን አሳፍሮ ከሊቢያ የተነሳው መርከብ ከአሌክሳንደሪያ የተጓዙ ወደ 240 ገደማ ስደተኞችን ለማሳፈር ሲሞክር ከአቅሙ በላይ በመሆኑ መገልበጡን ሙዐዝ መሐመድ ከተባለ ከአደጋው የተረፈ ኢትዮጵያዊ ሰሙ፡፡ በእንዲህ ዓይነት ስራ የሚሰማሩ መርከቦች ከጠረፍ ጠባቂዎች ዕይታ ለማምለጥ ስደተኞችን የሚያሳፍሩት ሜዲትራንያን ባህር መሀል ቆመው ነው፡፡ ስደተኞቹ በአስተላላፊዎች አማካኝነት እስከ መርከቦቹ ድረስ የሚጓጓዙት በአነስተኛ ጀልባዎች ነው፡፡

ከአደጋው በኋላ በቢቢሲ እና ቪኦኤ ድምጹ የተሰማው ሙዐዝልጁ እና ሚስቱ ዓይኑ እያየ መስመጣቸውንተናግሯል፡፡ እርሱም ሊተርፍ የቻለው ወደ አነስተኛዎቹ ጀልባዎች ዋኝቶ መመለስ በመቻሉ እንደሆነ ያብራራል፡፡ 

እነ ነሲቡ ጥያቄያቸውን አላቋረጡም፡፡ ከባሌ አካባቢ የተሰደደው ሙዐዝን ከቀዬአቸው የመጣ ሰው ያገኙ እንደሆነ ጠየቁት፡፡ ሙዐዝ በህይወት ከተረፉት 12 ኢትዮጵያውያን መካከል አንድ የሀረርጌ ልጅ እንዳለ ነገራቸው እና በስልክ አገናኛቸው፡፡ ገመቹ የተባለው የቦርዴዴ ተወላጅ ስለ አደጋው በዝርዝር አስረዳቸው፡፡    

እንደ ገመቹ አባባል 550 ሰዎችን ጭኖ በግምት ከእኩለ ለሊት በኋላ ከተገለበጠው መርከብ የተረፉት 36 ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከተረፉት ኢትዮጵያውያን መካከል አራቱ ከባሌ የመጡ ሲሆኑ አንዱ ከድሬዳዋ የተሰደደ መሆኑን ነግሯቸዋል፡፡ 

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ የተራፊዎቹ ቁጥር 41 መሆኑን እና አስራ አንዱ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አሳውቋል፡፡ ሃያ ሶስት ሶማሌዎች፣ ስድስት ግብጻውያን እና አንድ ሱዳናዊም የኢትዮጵያውኑ ዓይነት መልካም ዕድል ገጥሟቸዋል፡፡

12 Survivors of the accident
12 Survivors of the accident

ነፍሳቸው ከተረፉት ውስጥ የሶስት ዓመት ህጻን እና ሶስት ሴቶች ይገኙበታል፡፡ UNHCR ባለፉት 12 ወራት ከደረሱ አደጋዎችየከፋሲል በጠራው በዚህ አደጋ 500 ገደማ ሰዎች መሞታቸውን ገልጿል፡፡ የዛሬ ዓመት ግድም በሜዲትራንያን ባህር ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ በደረሰ አስከፊ አደጋ ወደ 800 ሰዎች ገደማ ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡  

የዚህ ሳምንቱ የመርከብ መገልበጥ አደጋ የተከሰተበት ትክክለኛ ቦታ አለመታወቁን የሚገልጸው የስደተኞች መርጃ ድርጅቱ በሊቢያ እና ጣሊያን መካከል በሚገኝ የሜዲትራንያን ባህር መሀል መሆኑን ግን ማረጋገጫ ሰጥቷል፡፡ ባለፈው ሳምንት ቶብሩክ ከተሰኘች የሊቢያ ቦታ 30 ሜትር ርዝመት ባለው ጀልባ ተሳፍረው የተነሱት ስደተኞች በሰዎች አለቅጥ ወደተጨናነቀ ትልቅ መርከብ እየተዘዋወሩ ባለበት ወቅት አደጋው መከሰቱን ድርጅቱ ተራፊዎችን ጠቅሶ አስታውቋል፡፡   

በአነስተኛ ጀልባዎች ተንጠላጥለው ህይወታቸውን ያተረፉት ስደተኞች በነጋዴዎች መርከብ አማካኝነት ባለፈው ቅዳሜ ሚያዝያ 8 ወደ ግሪክ እስኪወሰዱ ድረስ ቢያንስ ለሶስት ቀን ያህል በባህር ላይ ሲንገላቱ ቆይተዋል፡፡ በግሪክ ፔሎፖኒሶስ ባህረ ሰላጤ ወደምትገኘው ካላማታ ከተማ ከተወሰዱ በኋላ በስቴድየም ውስጥ እንዲጠለሉ ተደርገዋል፡፡ ነሲቡ እና ጓደኞቹ ከሙዐዝ እና ገመቹ ጋር በስልክ መረጃ የሚለዋወጡት ተራፊዎቹ በጊዜያዊነት ካረፉበት ከዚህ ቦታ ነው፡፡   

ነሲቡ እና ጓደኞቹ የሟቾቹ ኢትዮጵያውያንን ትክክለኛ ቁጥር እና የመጡባቸውን አካባቢዎች ለማወቅ ለግብጻውያን ደላሎች እና አጓጓዦች ገንዘብ ወደሚያስረክቡ ኢትዮጵያውያን መሄድ ነበረባቸው፡፡ በግብጽታማኝ ኢትዮጵያውያንተብለው የሚታወቁት እነዚህ ግለሰቦች ወደ አውሮፓ ለመሻገር ከደላላሎች ጋር ከተስማሙ ስደተኞች ገንዘብ በመቀበል በጊዜያዊነት የሚያሰቀምጡ ናቸው፡፡ በአሰራሩ መሰረት ያስቀመጡትን ገንዘብ ለደላሎች የሚከፍሉት ስደተኞቹ ያቀዱበት ሀገር መድረሳቸውን ደውለው ከነገሯቸው በኋላ ይሆናል፡፡ 

ታማኝ ኢትዮጵያውያንበተገኘ መረጃ መሰረት ከኤሌክሳንድሪያ የተሳፈሩት ኢትዮጵያውያን ቁጥር 213 ነው፡፡ ህይወታቸውን በአደጋው ካጡት ውስጥ 72 ያህሉ ከባሌ እና ሮቤ የተሰደዱ ሲሆኑ 54 ደግሞ ከድሬዳዋ እና አካባቢው መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡ አስራ ሁለቱ ደግሞ ከምዕራብ እና ምስራቅ ሀረርጌ የሄዱ ናቸው፡፡ የአርሲ እና ወለጋ ተወላጆችም በአደጋው ህይወታቸውን እንዳጡ ቢታወቅም ትክክለኛ ቁጥራቸውን ማወቅ አልተቻለም፡፡

በአደጋው ከሞቱት ብዙዎቹ ባለፉት አምስት ወራት ከሀገር ለቀው የወጡ ናቸውይላል ቶፊቅ ረሺድ የተባለ በካይሮ የሚገኝ ስደተኛ ለዋዜማ ስለ አደጋው ሲያስረዳ፡፡አብዛኞቹ የኦሮሚያ ተወላጆች ናቸው፡፡

Ethiopian Protestors infront of UNHCR office in Cairo
Ethiopian Protestors infront of UNHCR office in Cairo

UNHCR የግብጽ ቢሮ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው እስከ ጥር ወር ብቻ በድርጅቱ የተመዘገቡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር 6,733 ደርሷል፡፡ የስደተኞቹ ቁጥር ከአንድ ወር በኋላ 183 ሰዎች ጨምሯል፡፡ 2008 . ጥር ወር የስደተኞች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 2,458 ሰዎች ከፍ ያለ ነው፡፡

ከስደተኞቹ ውስጥ አብዛኞቹ ከኦሮሚያ የሚመጡ መሆናቸውን የሚናገሩት በግብጽ ያሉ ስደተኞች የቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ የማሻቀቡ ምክንያት በክልሉ የተቀሰቀሰው መጠነ ሰፊ ተቃውሞ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በተቃውሞው ከመገደል፣ ከመቁሰል እና ከመታሰር ስደትን የመረጡ ወጣቶች ከመተማ እስከ ካይሮ ያለውን አስቸጋሪ እና አደገኛ የስደት ጉዞ መጋፈጥ ግድ ይላቸዋል፡፡

ለዚህም 23 ሺህ እስከ 30 ሺህ ብር መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአሌክሳንድሪያ አድርገው ወደ አውሮፓ ለመሻገር ደግሞ ተጨማሪ ሁለት ሺህ ዶላር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ረጅሙ ጉዞ ከመተማ ተነስቶ በጋላባት እና ገዳሪፍ አድርጎ ካርቱም ከገባ በኋላ ወደ ሺማሌያ እና አስዋን አቅንቶ ካይሮ ላይ ይጠናቀቃል፡፡

ቤተሰብ ልጆቼ ከሚገደሉብኝ እና ከሚታሰሩብኝ በሚል ለስደት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከብቶቹንም ሆነ መሬቱንም ቢሆን ሸጦ ይሰጣልይላል ከመጀመሪያው የማስተር ፕላን ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ታስሮ ከዓመት በላይ በእስር ከቆየ በኋላ የተፈታው ቶፊቅ፡፡

ወጣቶቹ ስደተኞች ገንዘባቸውን ከስክሰው እና አስቸጋሪውን ጉዞ አገባድደው ካይሮ ሲደርሱ የሚያጋጥማቸው ያልጠበቁት ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞ ያሰለፋቸውም ሆኗል፡፡ ካይሮ በሚገኘው UNHCR ቢሮ ደጃፍ ላለፈው አንድ ወር እያካሄዱት ያለው ተቃውሞ ሶስት ጥያቄዎችን ያነገበ ነው፡፡

ባለፉት ሁለት እና ሶስት ወራት የስደተኝነት እውቅና እንዲሰጣቸው UNHCR ያመለከቱ ወደ 200 የሚጠጉ አመልካቾችኬዛችሁ አሳማኝ አይደለምበሚል ጥያቄያቸው ውድቅ መደረጉ ከተቃውሞ መነሻዎች የመጀመሪያው ነው፡፡ ፋይል ተከፍቶላቸው ጉዳያቸው እየታየላቸው ይገኙ የነበሩ ስደተኞች ያለ በቂ ምክንያት ፋይላቸው እንዲዘጋ መደረጉ ሁለተኛው ምክንያት ነው፡፡ለአደጋ የተጋለጥን ሆነን ሳለ በቂ ጥበቃ ተነፍጎናልየሚለው ደግሞ የመጨረሻው የተቃውሞ ነጥብ እንደሆነ ስደተኞቹ ይናገራሉ፡፡

ድርጅቱ ውድቅ ያደረጋቸውንም ሆነ የዘጋቸውንኬዞችተመልሶ እንዲመለከት እንደዚሁም በቂ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው የሚሹ ስደተኞች UNHCR ጽህፈት ቤት ቅጽር ግቢ ውጭ በመተኛት ጭምር ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ፡፡

በአደጋው የሞቱት እንደ እኛው ሜዳ እና አስፋልት ላይ እየተኙ፤ ጸሀይ እና ብርድ እየተፈራረቀባቸው ተቃውሞ ሲያቀርቡ የቆዩ ናቸውይላል ቶፊቅ፡፡ ” ‘ኬዛችን ውድቅ ከተደረገ በኋላ መመለሻ የለንም፡፡ የግብጽ መንግስት ቢያስረን እና ወደ ሀገራችን ቢመልሰን ችግር ይደርስብናል፣ እንገደላለንብለው ተስፋ ስለቆረጡ ነው ለዚህ አደጋ የበቁትሲል ህይወታቸውን እንዲያጡ ያደረጋቸውን መንስኤ ያብራራል፡፡   

የወገኖቻቸው በወጡበት መቅረት ያንገበገባቸው በካይሮ የቀሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለሚቀጥለው እሁድ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ለማዘጋጀት እየሞከሩ ነው፡፡ ስደተኞቹ ተቃውሞውን ለሀዘን መግለጫነት ሊጠቀሙበት ያስባሉ፡፡ 

በአደጋው ሰዎች የሞቱባቸው ብዙ ቤተሰቦች ናቸው፡፡ እንደ ሀገራችን ድንኳን ተክለን ሀዘናችንን ለእነሱ መግለጽ አንችልም፡፡ የሀገሩ ሰዎችም አይፈቅዱልምይላል ቶፊቅ፡፡እንደ ሀገራችን ሀዘናችንን በሰፊው ለመግለጽ ያለን አማራጭ UNHCR ፊት ለፊት ያለውን ሜዳ መጠቀም ነው፡፡ የሟች ቤተሰቦችን ሰብስበን እናጽናናለን፡፡ በዚያውም የእዚህ ምክንያቱ UNHCR መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡