Food aid distribution in Somalia region
Food aid distribution in Somalia region

(ዋዜማ ራዲዮ) ኢትዮጵያ በራሷ የዘመን አቆጣጠር አዲሱን ሚሌኒየም ከተቀበለች ወዲህ ለሶስተኛ ጊዜ በድርቅና ረሃብ ተመትታለች፡፡ የአሁኑ ግን… አፋጣኝ መላ ካልተበጀለት ከሶስት አሠርት ዓመታት በፊት በ1977 ዓ.ም ከደረሰውም የከፋ ሊሆን እንደሚችል ቅድመ ማሳሰቢያ ሲሰጥ ሠንብቷል፤ እየተሰጠም ነው፡፡

ዳንኤል ድርሻ ያዘጋጀውን መዝገቡ ሀይሉ ያቀርበዋል አድምጡት

ኮርድኤይድ የተሰኘ ግብረ ሠናይ ድርጅት ባልደረባዎች ወደ አፋር ክልል ሠመራ እና ቆሬ ከተማዎች በማምራት የተመለከቱት አሳዛኝ ክስተት… በሃገሪቱ የወረደውንና እየወረደ ያለውን መዓት ሳያመላክት አይቀርም፡፡ የመጣውና እየመጣ ያለው የድርቅና ረሃብ፣ የችግርና ችጋር ሥጋት ማሳያ ሆኖ ሊጠቀስም ይበቃል፡፡ ተጓዦቹ ያዩትን ሲናገሩ “…መሬቱ ደርቋል ሳይሆን አግጥጧል፤ በአንድ ወቅት ወንዞች ይፈሱባቸው የነበሩ ቦዮች ክው ብለው ደርቀዋል፡፡” ነው ያሉት፡፡

የኮርድኤይድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲሞኒ ፊሊፒኒና ባልደረቦቿ በሥፍራው ተገኝተው የሰሙና የተመለከቱትን ሲያብራሩ “…ላለፉት ሁለት ዓመታት በአካባቢው ዝናብ የሚባል አልወረደም፤ በዚሕም የተነሳ መሬቱ ከአረንጓዴነት ወደ ብጫነት ተቀይሯል፡፡ ለአንድ ቤተሰብ በአማካይ 20 ሊትር ውሃ ይሰጣል፤ መላ ቤተሰቡ በ2ዐ ሊትር ውሃ ሁሉን ነገር መከወን እንደማይችል ግን ግልጽ ነው፡፡” በማለት የችግሩን ስፋት ያስረዳሉ፡፡

በመንግስትና በአንዳንድ ቡድኖች በአፋጣኝ ይሰጣል የተባለው አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ… እነሱ ጉብኝቱን እስካከናወኑ ድረስ እሥፍራው አለመድረሱን በመግለጽም ነዋሪው በረሃብና ጥም ስለመሰቃየቱ እማኝ ሆነዋል፡፡

“ድርቅና ረሃብ ከጋረጠው ሥጋት ይልቅ መንግሥት በፖለቲካዊ ጨዋታ ለማትረፍ ፈልጓል” የሚሉ ወገኖች በበኩላቸው… ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና በጎ አድራጎት ድርጅቶች ድርቁን በተመለከተ የሚጠቀሙበትን ቃላት ሳይቀር ለመምረጥ ገዢው ፓርቲ የተጓዘበት ርቀት… ይሕንኑ ያስረዳል ባይ ናቸው፡፡

መንግሥት ለረድዔት ተቋማት እና ለውጪ ሃገር መገናኛ ብዙሃን ባስተላለፈው ማስጠንቀቂያ “…ረሃብ፣ ድርቅ እና የሕጻናት ሞት” የሚሉ ቃላትን እንዳይጠቀሙ አዝዟል፤ በምትኩም “ኤልኒኖ ያስከተለው የምግብ ዕጥረት” እያሉ እንዲጽፉና እንዲናገሩ ሃሳብ መስጠቱን… ትዕዛዙ የደረሳቸው ኦል አፍሪካን የመሳሰሉ ሚዲያዎች ይፋ አድርገዋል፡፡

ከ2ዐ16 የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት አንስቶ “15 ሚሊየን ኢትዮጵያዊ ለምግብ እጥረት ይዳረጋል” ሲባል “ቁጥሩ አልተስማማኝም…” የሚል ውዝግብ ውስጥ የሰነበተው የኢሕአዴግ መንግስት ከሰሞኑ 10.1 ሚሊየን ሕዝብ አደጋ ላይ መሆኑን አምኖ ተቀብሏል፡፡

በዚሕ ስሌት እንኳ ቢኬድ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ አስረኛ የሚሆነው በምግብ እጥረት አደጋ ቀጣና መግባቱን እንደሚያሳይ የጠቀሱ የአደጋ አስጠንቃቂዎች… ከመንግስትና ከለጋሾች ተገኝቷል የተባለው 2ዐዐ ሚሊየን ዶላር… ከሚፈለገው አንጻር በእጅጉ ያነሰ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የዛሬ 3ዐ ዓመታት የተከሰተው ዓይነት ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይደገም ለኢትዮጵያ ረሃብ ቢያንስ አንድ ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያስፈልግም ማስጠንቀቂያ አከል መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ከ2016 መጀመሪያ አንስቶ 400 ሺህ ሕጻናት ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ የጤና እክሎች እንደሚዳረጉ፣ ችግሩ ሲባባስም ሕጻናቱን ለሞት የማጋለጥ ዕድሉን እንደሚያሰፋ የሚገልጸው ሴቭ ዘ ቺልድረን በበኩሉ በኢትዮጵያ ለተጋረጠው ሰብዓዊ ቀውስ የሚያስፈልገውን የገንዘብ መጠን ወደ 1.4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ከፍ ያደርገዋል፡፡

“ኦክስፋም” የተሰኘው ግብረ ሠናይ ተቋም ደግሞ በኢትዮጵያ ድርቅና ረሃብ የተከሰተው በሶስትዮሽ ቀውስ ድምር ውጤት ማለትም በሰብል ምርት ችግር፣ በምግብ አቅርቦትና በአመራሩ ፖለቲካዊ ምላሽ እጦት… የተነሳ መሆኑን ነው በጥናቱ የገለጸው፡፡

”የአዝመራው ያለመስመር እና ድህነት ሕዝቡን ለድርቅ አጋልጧል” የሚለው ኦክስፋም “የረሃቡ መንስዔ ግን የፖለቲካ አመራሩ ክሽፈት ብቻ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱ… ዓለም አቀፉ ተቋማት ለድርቅ መፈጠር የኤልኒኖን ክስተት ቢቀበሉም፣ ለሕዝቡ መራብና መጠማት… ግን ዋናው ተጠያቂ ሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ነው ብለው እንደሚቀበሉ አመላካች ይሆናል፡፡

በ1977ቱ ድርቅና ረሃብ የአራት መቶ ሺህ ዜጎች ሕይወት ማለፉን የሚያስታውሱ ወገኖች… አሁን እየተኬደበት ያለው መንገድ አሳሳቢ መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብዓዊ ጉዳዮችና አስቸኳይ ዕርዳታ ተቋም (ኦቻ) በመስከረም 2ዐ15 ቅድመ ትንበያዎችን ተመርኩዞ ይፋ ባደረገው ጥናት… የአደጋ ሥጋት ማስጠንቀቂያና ማሳሰቢያ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ከሶስት ወራት በፊት በተሰጠው በዚሁ ማሳሰቢያ ለ15 ሚሊየን ሕዝብ የምግብ እርዳታ፣ ለ1.2 ሚሊየኑ ተጨማሪ አልሚ ምግብ እንደሚያስፈልግ፣ 35ዐ ሺህ ሕጻናት በከፋ የምግብ እጥረት ለበሽታ እንደሚጋለጡ፣ 45ዐ ሺህ የቀንድ ከብቶች ሊሞቱ እንደሚችሉ፣ 18 ሚሊየን ሕዝብ የመጠጥ ውሃ እንደማያገኝ… ችግሩን ተከትሎ በሚከሰቱ እንደ ተቅማጥ ባሉ በሽታዎች ደግሞ የሕጻናት ሞት መጠን እንደሚጨምር ተጠቁሞ ነበር፡፡ አነዚህ መሰሎቹ ማንቂያ ማሳሰቢያዎች ግን ተገቢ ትኩረት አለማግኘታቸው አሳሳቢ ሆኗል፡፡

ሂደቱ ካሳሰባቸው መሐል ባሳለፍነው ሳምንት አራት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ልዩ መስሪያ ቤት ኃላፊዎች በጋራ መግለጫ በማውጣት ሥጋቱ ይቀረፍ ዘንድ ዓለም ለኢትዮጵያ ችግር ምላሽ እንዲሰጥ ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡

የተመድ ሰብዓዊ ጉዳዮችና አስቸኳይ ዕርዳታ አስተባባሪ ስቴፈን ኦብሪየን፣ የስደተኞች ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የዓለም ምግብ ድርጅት የበላይ ኤርሳሪን ኩዚን እና የሕጻናት ፈንድ ኃላፊ አንቶኒ ሌክ በጋራ ፊርማቸውን አሳርፈው ያሰራጩት መግለጫ እንደሚጠቀመው ለጋሾች ሁለት መቶ ሚሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል የገቡ መሆኑን፣ ሆኖም ግን በኢትዮጵያ የተከሰተውን ረሃብ ሥጋት ለመታደግ አንድ ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ አሁኑኑ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው ከ30 ዓመት በፊት የደረሰው ስሕተት እንዳይደገም ተማጽነዋል፡፡

መንግስት ግን የረሃቡና ሰቆቃው ሥጋት የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብን ያሕል ያስጨነቀው አይመስልም፡፡ የመንግስት ዳተኝነት ኢትዮጵያውያን በድርቁና ረሃቡ ጉዳይ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ሊያነቃ ይገባል የሚለው አስተያየት ከሰሞኑ በማሕበራዊ ድረ ገጾች ሲስተጋባ ተደምጧል፡፡

በኢትዮጵያ ነግደው ያተረፉ፣ በኢንቨስትመንት የተሰማሩ፣ ሃብትና ዝና የተቀዳጁ ግለሰቦች ሃገራዊ ብሎም ዓለም አቀፋዊ የዕርዳታ ማስተባበርን ተነሳሽነት ሊወስዱ ይገባል የሚሉ አስተያየት ሠጪዎች ድምጽም ተንጸባርቋል፡፡

ከ13 ዓመት በፊት “አንድ ብር ለአንድ ወገን” የተሰኘ አነስተኛ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ 13 ሚሊየን ብር መገኘቱን ያስታወሱ ወገኖች ደግሞ… በወቅቱ የተሰበሰበው ገንዘብ ብዙ የሚባል ባይሆንም ሌሎችን ለዕርዳታ ያነቃቃ ስለነበር ከዚያ ትምሕርት በመቅሰም ሕዝብን ማስተባበር እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ግን ዛሬም ድረስ ወደ ተግባር የተለወጠ እንቅስቃሴ ማየትም መስማትም አልተቻለም፡፡