Kinfeዋዜማ ራዲዮ- ለመከላከያ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) በከፍተኛ የገንዘብ መጠን እንዲሰራቸው ተሰጥተውት የነበሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ትዕዛዝ እንዲሰረዙ መወሰኑን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ተናገሩ።

በመንግስት ሀላፊነት ላይ ያሉና ስማቸውን መግለፅ ያልፈለጉ ምንጭ ስኞ ዕለት ለዋዜማ እንደተናገሩት የሰኳር ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ቢያንስ አንድ መቶ ቢሊየን ብር የሚጠጋ ፕሮጀክቶች ላይ ሜቴክ የነበረው ተሳትፎ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ ከውሳኔ ተደርሷል።

በምትኩ ፕሮጀክቶቹን ለግልና ለዓለማቀፍ ተቋራጭ ድርጅቶች ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን እኚሁ ባለስልጣን ይናገራሉ።
ሜቴክ በዚህ ውሳኔ ሳቢያ ሰባ በመቶ ያህል ፕሮጀክቶቹን የሚነጠቅ ሲሆን በቀሪ ፕሮጀክቶች ላይ ክትትል እንዲደረግበትና በተያዘለት ጊዜ ሰርቶ እንዲያጠናቅቅ ከውሳኔ ተደርሷል።
የተሰረዙት ፕሮጀክቶች አምስት እንደሆኑና በቅርቡ ለህዝብ ይፋ እንደሚደረጉም ተነግሯል። የያዩ የማዳበሪያ ፕሮጀክት ከወራት በፊት መሰረዙ ይታወሳል።
የሜቴክ ሀለፊ ጀነራል ክንፈ ዳኘው ስልጣን መልቀቅም የኮርፖሬሽኑን ስራ መምራት ባለመቻላቸውና በድርጅቱ እጅግ ከፍተኛ የገንዘብ ብክነት በመታየቱ እንደሆነ ተነግሯል። እስካሁን ለባከነው በቢለየን የሚቆጠር ገንዘብ ሀላፊነትየወሰደ አካል የለም።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ከዚህ በኋላ መከላከያ ከአቅሙ በላይ በሆኑ ፕሮጀክቶች እንዳይሳተፍ ብሎም መንግስት ለሜቴክ ያደርግ የነበረው ድጎማና ከለላ እንዲያበቃ ከመከላከያ ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ተናግረዋል።
በጉዳዩ ላይ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይም የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ አቅጣጫ ተቀምጦ ነበር ይላሉ የፓርቲው አመራሮች። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማንበብ ከፈለጉ እዚህ ይጫኑ