ዋዜማ –  የወለኔ አርሶ አደሮች ህብረት ፓርቲ (ወአህፓ) ‘ን በመመስረት ከምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅና የማግኘት ሂደት ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት የፓርቲው አባላት ” ይሁንና ፓርቲው እንዳይመሰረት የተለያዩ ችግሮች እያጋጠሙን ነው ” ብለዋል።

እንደ ኮሚቴ አባላቱ ገለፃ ከፓርቲው ምስረታ በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠሩ ባዘዘው መስረት ህዳር 16 , 2015 ዓ.ም በወልቂጤ ወረዳ ኢንጌ ላይ ጠቅላላ ጉባኤ ተዘጋጅቶ አንድ ቀን ሲቀረው ኮማንድ ፖስት በመታወጁ ስብሰባው ሳይካሄድ ቀርቷል።

” ከዚያ ቀን በኋላም ኮማንድ ፖስቱ ተነስቶልን ጉባኤ እንድናካሂድ አሁን ድረስ የተለያዮ ጥረቶች እያደረግን ቢሆንም አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጠን አካል አላገኘንም” ሲሉም የኮሚቴው ዋና አስተባባሪ አቶ ሰይፈ ጀማል ሐጂ ከድር ለዋዜማ ተናግረዋል ።

” የወለኔ አርሶ አደር ህዝብ የረጅም አመታት ህገመንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች እንዳሉት ” የሚገልፁት የኮሚቴ አባላቱ ” በዚህ ወቅት ፓርቲ መስርቶ መንቀሳቀሱ ያስፈለገው የህዝቡን ጥያቄዎች ለማስመለስ ነው ” ብለዋል ።

” የአርሶ አደሩን ጥያቄ ወደ ጎን በመተው የወለኔን ብሄር ስም በመያዝ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም የአካሄድ ስህተት በመሆኑ አዲሱ ፓርቲ ክልላዊ ሆኖ የሚመዘገብ ነው ” ሲሉም ያክላሉ ።

እንደ ኮሚቴ አባላቱ ገለፃ ‘ አዲሱ ፓርቲ የወለኔን አርሶ አደር ህዝብ ህገመንግስታዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎችን ለማስመለስ በንቃት እየተሳተፈ የወለኔ ልዮ ዞንን ለመመስረት የሚያስችል ህዝበ ውሳኔ በምርጫ የማካሄድ ግብንም ‘ አስቀምጧል ።

የወለኔ አርሶ አደሮች ህብረት ፓርቲ የወለኔ ህዝብ የብሄር ማንነት ጥያቄው ምላሽ አግኝቶ የራሱን ባህል ፣ ቋንቋ ፣ ታሪክና እሴቶች እንዲያበለፅግ ብሎም ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ፓርቲው እንደሚታገልም መስራቾቹ እየተናገሩ ነው።

በሌላ በኩል የወለኔን ህዝብ የረጅም ጊዜ ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲረዳው ለዚህም ኮሚሽኑ በወረዳው ላይ ስብሰባ እንዲያዘጋጅ ደብዳቤ ማስገባታቸውንም የፓርቲው መስራቾች ለዋዜማ ገልፀዋል።

የወለኔን የአርሶ አደር ህዝብ የሚከፋፍል የልዩነት ግንብ ለረጅም ጊዜ ቆሟል የሚሉት የኮሚቴ አባላቱ በብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አማካኝነት ወደ አንድነት የሚያመጣ ስራ እንዲስራ ጠይቀዋል ።

የወለኔ አርሶ አደር ህዝብ የራሱ ልዮ ቋንቋ ፣ የራሱ ልዮ ባህል ፣ የራሱ ልዮ ታሪክ ያለው ፤ ጉራጌም፣ ሰባት ቤት ጉራጌም ስልጤም ያልሆነ ህዝብ እንደሆነም በአፅንዖት ያስረዳሉ። [ዋዜማ ]