Gedion Timotiwos , Attorney General-FILE

ዋዜማ – በሀገራችን በተለያየ ጊዜ የተፈፀሙና  በዓለማቀፍ መስፈርት የተበየኑ የስብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ሌሎች ወንጀሎችን በሽግግር ፍትሕ አሰራር ልዩ ኮምሽን በማቋቋም ማየት የሚያስችል ምክረ ሀሳብ ለመንግስት መቅረቡን ዋዜማ ተገንዝባለች። 

የቅርብ ጊዜውን የሰሜኑን ጦርነት ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት በማህበረሰቡ ውስጥ ፍትሕ የሚጠየቅባቸውን ጥፋቶች በዝርዝር በማየት ምዕራፉን ለመዝጋት የሚያስችል የህግ አማራጮችን የያዘ ምክረ ሀሳብ መቅረቡን ዋዜማ ከሰነዱ ይዘት ተመልክታለች።  

የሽግግር ፍትህ አተገባበር ጉዳይ  በፌደራል መንግስትና በህውሓት መካከል የተደረገው የሰላም ስምምነት ስምምነት አካል ነው።

ይቋቋማል የተባለው አዲስ ኮሚሽን የሽግግር ፍትህ ሂደትን በማከናወን በባለቤትነት የሚመራና ሌሎች ተቋማትንም የሚያስተባበር ነው። 

ዋዜማ በደረሳት “የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ረቂቅ ፖሊሲ [አማራጭ አቅጣጫዎች]” የተለያዩ አማራጭ የፍትህ ሂደቶችን የያዘ ነው። በሦስት ምዕራፎች የተከፋፈለው ረቂቁ የአገሪቱን የሽግግር ፍትህ ልምዶች ፈትሾ ይጀምራል። በዚህም ኢትዮጵያ በመንግስታት መፈራረቅ የሽግግር ፍትህን ብትጠቀምም “እርቅና ሀገራዊ መግባባት” ላይ ባለመነጣጠሩ ሂደቱ ሊሳካ አልቻለም ሲል ገምግሟል።

ካለፈው አስከፊ ሁኔታ በመማር ወደ ፊት ለመራመድ የሽግግር ፍትህ ሂደቶች የሚፈጥሯቸውን አጋጣሚዎች እንዳንጠቀም ምክንያት ሆነዋል። ይህም በራሱ እስካሁን ድረስ ለቀጠለው ግጭት፣ የእርስ በእርስ ጦርነት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መንስኤ የሆኑ በርካታ ጉዳዮች ሳይፈቱ እንዲቀጥሉ አስተዋፅዎ አድርጓል ብሏል።

ረቂቁ ክስን፣ እርቅን፣ ምህረትን፣ እውነትን፣ ማካካሻንና ተቋማዊ ማሻሻያን ያካተተ ነው። የአማራጮቹን ዝርዝር ሀሳብ፣ ጠንካራ ጎናቸውንና ተግዳሮታቸውን  የጠቀሰው ረቂቁ፤ በሂደቱ የሚታዩ ወንጀሎች ክብደት፣ ተጠያቂዎች፣ ተጎጂዎችና አስፈጻሚ ተቋማት እነማን ሊሆኑ እንደሚችሉም በቢሆን እይታ አካቷል።

በሽግግር ፍትህ ሂደቱ የወንጀል ምርመራውንና ክስን ማን ይመሰርታል? ለሚለውም አማራጭ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል። ለሂደቱ ብቻ የተለዩ ልዩ ፍ/ቤቶችና ችሎቶች መሰየም፣ ከተለያዩ የፍትህ አካላት የተወውጣጡ የባለሞያዎች ቡድን ማቋቋምና ልዩ የአቃቢ ህግ ተቋምን መመስረት በአማራጭነት ተቀምጠዋል።

በፖሊሲው እውነትን ማፈላለግ፣ እርቅና ምህረት ትልቅ ስፍራ ተሰጥቷቸዋል። 

ለሽግግር ፍትህ እንደ ግብ የታዩት እነዚህ አማራጮች ቁርሾን ለማረቅ፣ ለመጠላላት መፍትሄ ለመስጠት፣ ቁስልን ለማከምና ከግፍ ለመሻገር አይን ተጥሎባቸዋል። አማራጮችን ማን ያስፈጽማቸው ለሚለው ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ታጭተዋል።

ቅድመ-ሁኔታዎችን ያላሟላ ምህረት እንደማይደረግ አጽንኦት የሰጠው ይህ ረቂቅ፤ የምህረት አዋጁ ይህን እንዲያቀናጅ መሻሻል አለበት ብሏል።

የሽግግር ፍትህ ተፈጻሚነትም አማራጮች ቀርበውበታል። መነሻና መዳረሻው መቼ ይሁን ለሚለው፤ 1983 በፊት፣ 1983 ጀምሮ ፣ ከ1987 ጀምሮ እና ከ2010 ጀምሮ ያለው ጊዜ መልካም እድሎችና ስጋቶች ተዳሰው ቀርበዋል።

በኢትዮጵያ ለሚተገበረው የሽግግር ፍትህ ሂደት አዲስ ኮሚሽን በማቋቋም ማከናወን ተሰምሮበታል። ኮሚሽኑ ስልቶችን በባለቤትነት የሚመራ፣ ሌሎች ተቋማትንም የሚያስተባብር እና የሚያቀናጅ ይሆናል።  

አማራጭ ስያሜዎች የቀረቡ ሲሆን  የሀቅ እና የእርቅ ኮሚሽን ፣ የእርቅ እና የሰላም ኮሚሽን ፣የእውነት እና እርቅ አፈላላጊ ኮሚሽን ፣ የሀቅ፣ የፍትህ እና የእርቅ ኮሚሽን ሊባል ይችላል ተብሏል።

ሦስት ዓመት የስራ ዘመን የተሰጠውና 40 የሚሆኑ ኮሚሽነሮች የተሰየሙለት የእርቀ-ሰላም ኮሚሽን በቅርቡ መበተኑ አይዘነጋም። ለውይይት በቀረበው ረቂቅ ሰነድ ይቋቋማል ተብሎ የሚጠበቀው ኮሚሽን ከከሰመው ኮሚሽን ትምህርት በመውሰድና ልምዶችን ከግምት ውስጥ እንደሚያስገባ ረቂቁ ያስረዳል።

በተጨማሪም 36 አባላት ያሉት ብሄራዊ የሽግግር ፍትህ አስተባባሪ ቦርድ (ም/ቤት) በፖሊሲው መሰረት ተቋማት ተግባሮቻቸውን ማከናወናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት የሚኖረው አካል ይቋቋማል። እንደ አግባብነቱ ተመሳሳይ አደረጃጀቶች በክልል ደረጃም ሊቋቋሙ የሚችሉ ሲሆን ከባህላዊ አደረጃጀቶችና ከህብረተሰቡ የሚመረጡ አባላት ይሆናሉ፡፡  የባለሞያዎች የሴክሬታሪያት ቦርድ እንደሚቋቋምና የማስተባበር ስራ እንደሚሰራም ሰነዱ ያትታል። [ዋዜማ]