Gebremeskel Chala, MoTI- FILE
  • ቡና ላኪዎች ውል ለማቋረጥ ተገደዋል
  • የበሬ ስጋ የወጪ ንግድ ሊቆም ጫፍ ላይ ደርሷል

ዋዜማ- በሀገር ውስጥ ያለውና በቁጥጥር ስር ሊውል ያልቻለው የዋጋ ንረት የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ እየተፈታተነው እንደሆነ ዋዜማ ከተለያዩ ምንጮች ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል።

የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ላኪዎች ከሀገር ውስጥ የሚገዙበት ዋጋ ከፍተኛ ጭማሬን እያሳየ በመምጣቱ ከሌሎች ሀገራት ላኪዎች ጋር መወዳደር እያቃታቸው በመምጣቱ ነው።

የስጋ የወጪ ንግድ በዚህ አመት ከፍተኛ የሆነ የተወዳዳሪነት ችግር አጋጥሞት የምንዛሬ ገቢያቸው እያሽቆለቆለ ከመጡት ከቀዳሚዎቹ ነው። ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የስጋ ላኪ ኩባንያ ባለሀብት ለዋዜማ እንደነገሯት የስጋ ምርት በስፋትና በዋነኝነት በሚላክበት የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (ዱባይ) ገበያ የኢትዮጵያ ምርት በኬንያ ከፍተኛ ብልጫ እየተወሰደበት ከገበያ እየወጣ ነው ።

ኢትዮጵያ ባለፈው አመት ለውጭ ገበያ ልካ 120 ሚሊየን ዶላር አካባቢ ካገኘችበት የስጋ ምርት ውስጥ 90 በመቶውን ድርሻ የፍየል ስጋ ይይዛል። 

“አሁን ላይ የፍየል ስጋን ውጭ ለመላክ ከሀገር ውስጥ የምንጠየቀው ዋጋ ከፍተኛ ጭማሬን አሳይቷል ” የሚሉት ባለሀብቱ  ከአንድ ወር በፊት ከሀገር ውስጥ አቅራቢዎች በኪሎ 340 ብር የነበረው የፍየል ስጋ አሁን 400 ብር ገብቷል ። ይኸው ዋጋ የዛሬ አመት 270 ብር ነበር ብለዋል። (ዋጋው የሚወጣው ፍየሎቹ በላኪዎቹ ታርደው በሚሰራ ልኬት ነው።)

በውጭ ምንዛሬ ሲሰላ አሁን ለፍየል ስጋ በኪሎ ለሀገር ውስጥ አቅራቢዎች 7.4 የአሜሪካ ዶላርን መክፈል ይጠበቅብናል የሚሉት ነጋዴው ብሄራዊ ባንክ ደግሞ ይሄንኑ ምርት ለውጭ ገበያ በኪሎ በትንሹ በ6.6 የአሜሪካ ዶላር እንድንሸጥ ነው ያዘዘን ይላሉ።

ይህ ኪሳራ መሆኑን የሚያነሱት ሌላ በስጋ የወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰብ ” ወጪያችንን ከግምት ያስገባ ዋጋን ተምነን እንዳንሸጥ ችግር የሆነብን የጎረቤት ሀገር ኬንያ ላኪዎች በተሻለ ዋጋ ከሀገራቸው አቅርቦት ስላላቸው በዱባይ ገበያ እንዳንፎካከር አድርጎናል “ ይላሉ።

የኬንያ ላኪዎች አንድ ኪሎ ግራም የፍየል ስጋን ከሀገራቸው አቅራቢዎች በ3.8 የአሜሪካ ዶላር ያገኛሉ። ይህንንም ዱባይ ላይ 6 ዶላር እየሸጡት በመሆኑ የኢትዮጵያን ላኪዎች ከገበያ እያስወጧቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ስጋ ላኪዎች ይናገራሉ። 

በዚህ በጀት አመት ለውጭ ገበያ የተላከ ስጋ በመጠንም በውጭ ምንዛሬ ግኝትም ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው።  ባለፈው በጀት አመት የመጀመርያ ሰባት ወራት ውስጥ 13800 ቶን ስጋ ለውጭ ገበያ ተልኮ 68 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የተገኘ ሲሆን በዚህ በጀት አመት የመጀመርያ ሰባት ወራት 9600 ቶን ስጋ ተልኮ የተገኘው የውጭ ምንዛሬ የ11 ሚሊየን ዶላር ቅናሽ አሳይቶ 57 ሚሊየን ዶላር ነው። 

በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ንረት የበሬ ስጋ ላኪዎችን ተወዳዳሪ ማድረግ ስላልቻለ አብዛኞቹ ላኪዎች የበሬ ስጋን መላክ አቁመዋል። የስጋ የወጪ ንግድ ባለፈው አመት ከግብርና ምርቶች ከቡና ቀጥሎ 120 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት ቀዳሚ ነበር።በዚህ አመት ግን ተመሳሳይ ውጤት ማስመዝገቡ ጥርጣሬ ውስጥ ወድቋል።

ቡናችን

የቡና የወጪ ንግድም በሀገር ውስጡ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ሳቢያ ፈተና ካንዣበባቸው ውስጥ ነው። በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች እንደነገሩን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚገዛ ቡና እጥፍ ሊደርስ የሚችል የዋጋ ጭማሬን ማሳየቱን ገልጸዋል።አንድ ኪሎ እሸት ቡና ከገበሬ ላይ የሚገዛበት ዋጋ 110 ብር ደርሷል። አምና ዋጋው 60 ብር ገደማ ነበር።

አንድ ኪሎ ለውጭ የሚቀርብ ቡናን ለማምረት ሰባት ኪሎ እሸት ቡና ያስፈልጋል። ስለዚህ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ደረጃ አንድ ፣ አንድ ኪሎ ቡናን አንድ ላኪ ከ770 ብር ያላነሰ ወጪ አውጥቶ ከሀገር ውስጥ ይገዛል። ይህ በውጭ ምንዛሬ 14 የአሜሪካ ዶላር ገደማ ነው።

ሆኖም በአለም ገበያ እንደየ ጥራትና የበቀለበት ሀገር የተለያየ ሆኖ የአንድ ኪሎ ቡና ዋጋ ከ7 እስከ 8 የአሜሪካ ዶላር ነው።  በኒው ዮርክ ዓለማቀፍ የቡና ግብይት ላይ ደግሞ ዋጋ ደግሞ ካለፈውም አመት የአንድ ዶላር አካባቢ ቅናሽ አሳይቶ አንድ ፓውንድ (ግማሽ ኪሎ አካባቢ) ቡና በ1.9 ዶላር አካባቢ ነው የሚሸጠው። 

አሁን ያለው የአለም የቡና ዋጋ የኢትዮጵያ ላኪዎች ከሀገር ውስጥ ከሚሰበስቡበት ዋጋ በእጅጉ በማነሱ በርካታ ላኪዎች ድንጋጤ ውስጥ ገብተዋል።ዋዜማ ከታማኝ ምንጮቿ እንዳረጋጠጠችው ከሆነ ከፍተኛ ቡና ላኪ የሚባሉ ሳይቀሩ አሁን ያለው ዋጋ ቀድሞ በገቡት ውል ላይ ሰፊ ልዩነት ስላለው ለመላክ የገቡትን ውል አላከበሩም። 100 ያህል ውል ያፈረሱ ላኪዎች እንዳሉም ሰምተናል። 

ቡና ባለፈው አመት 1.4 ቢሊየን ዶላር በማስገኘት ክብረወሰን አስመዝግቦ ነበር። በወቅቱ 300 ሺህ ቶን ቡና ለአለም ገበያ ቀርቧል። በዚህ በጀት አመት የመጀመርያ ሰባት ወራት የተላከው ቡና 126 ሺህ ቶን ሲሆን ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር በመጠን ያነሰ ነው። የተገኘው 702 ሚሊየን ዶላርም በቀሪ አምስት ወራት ውስጥ የባለፈውን አመት ገቢም ሆነ በመንግስት የታቀደውን ሁለት ቢሊየን ዶላር ለማስገኘቱ ጥርጣሬ ፈጥሯል።

ባለፈው አመት ከወጪ ንግድ አራት ቢሊየን ዶላር የተገኘ ሲሆን በዚህ አመት የመጀመርያ ሰባት ወራት ሁለት ቢሊየን ዶላር እንደተገኘ መረጃዎች ያሳያሉ። [ዋዜማ]