Ethiopian assembled electric vehicle-FILE

ዋዜማ- የኢትዮጵያ መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ለኤሌክትሪክ መኪና አስመጪ እና አምራቾች ከፍተኛ ማበረታቻዎችን እያደረገ ቢሆንም በሀገሪቱ ያሉ አብዛኞቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ግን ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከሶስተኛ ወገን ውጭ ሙሉ የኢንሹራንስ ሽፋን “አንሰጥም”  እያሉ መሆኑን ዋዜማ ከተለያዩ አሽከርካሪዎች እና የመድን አቅራቢ ኩባንያዎች መረዳት ችላለች።

የመድን አቅራቢዎቹ የሶስተኛ ወገን አገልግሎት እንዲሰጡ ህግ ያስገድዳቸዋል። በዚህም ሳቢያ የኤሌክትሪክ መኪኖቹ በሶስተኛ ወገን ንብረትም ሆነ ተሽከርካሪ ላይ ላደረሱት ጉዳት ብቻ ሽፋን ያገኛሉ። የኤሌክትሪክ መኪኖቹ አደጋ ቢደርስባቸው ፣ ቢሰረቁ ግን የሚያስፈልጋቸውን የመድን ሽፋን እንደማያገኙ ካሰባሰብነው መረጃ ተገንዝበናል።

የኢትዮጵያ መንግስት የነዳጅ ወጪንና የአየር ብክለትን ለመቀነስ ከውጭ የሚገቡ የኤሌክትሪክ መኪኖችን ከአንዳንድ የቀረጥ አይነቶች ነጻ እንዲሆኑና ቅናሽ እንዲያገኙ አድርጓል። ይህም ብቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥ የኤሌክትሪክ መኪናን ለሚገጣጥሙ ኩባንያዎች ለየት ያለ ማበረታቻን እንዲያገኙ ማድረጉን ሲገልጽ ቆይቷል። 

የውጭ ምንዛሬ ለመቆጠብ እና የጥቁር ገበያ እንቅስቃሴን ለመግታት በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርሪዎች ከሌሎች ምርቶች ጋር ከውጭ እንዳይገቡ ሲታገዱም የኤሌክትሪክ መኪኖችን ግን እገዳ አልተደርገባቸውም ነበር። 

በዚህም ሳቢያ ከቅርብ ወራት ወዲህ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ማየት የተለመደ ሆኗል።

በአመት ከሁለት ትሪሊየን ብር የሚልቅ ዋጋ ላላቸው ንብረቶች ሽፋን የሚሰጠው መንግስታዊው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ለዚህ በምክንያትነት የሚጠቅሰው የህግ ክፍተትን ነው። 

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የተሽከርካሪ መድን መመሪያ የሚለው ሙሉ የመድን ሽፋን የሚሰጠው መካኒካል እና በነዳጅ ለሚሰሩ ተሽከርካሪዎች እንጂ ለኤሌክትሪክ መኪኖች አይልም በዚህም ሳቢያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አገልግሎቱን እንዳይሰጥ አግዶታል። ስለዚህም ለኤሌክትሪክ መኪኖች ሽፋንን ለመስጠት የመድን ድርጅቱ መመሪያዎቹን መከለስ እና አዋጭነቱን በድጋሚ ማየት አለበት። 

በተጨማሪም የኤሌክትሪክ መኪኖች ለኢትዮጵያ አዲስ በመሆናቸው ዋጋቸውም ውድ በመሆኑ አዋጭነታቸውን በቅድሚያ ማየት እንደሚገባ የመድን ድርጅት የሰራ ሃላፊዎች ነግረውናል።

አሁን በገበያ ላይ ያሉት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከ2 እስከ 5 ሚሊየን ብር ድረስ ዋጋ የሚሸጡ ናቸው።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የሚጠቀሙት ሀይል ማከማቻ ባትሪ በተለየ ውድ በመሆኑና አደጋ ሲደርስ ባትሪውን መተካት ከፍተኛ ወጪ ስላለው በርካቶቹ የኢንሹራንስ ኩባን ያዎች የመድን ሽፋን መስጠቱ ላይ እንዲያመነቱ ማድረጉን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

አዲስ አይነት መኪኖች ሲገቡ መለዋወጫቸው በጣም ስለሚወደድ ፣ ቢበላሹ እንኳ ጠጋኞችን ማግኘት ከባድ ስለሚሆን አደጋ በሚያጋጥም ጊዜ ወጭያቸው ስለሚንር ለኢንሹራስ ኩባንያዎች ስጋት ፈጣሪ ናቸው ያሉት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሃላፊዎች በተመመሳይ ነገር ሲኖ ትራክ የሚባሉት ቻይና ሰራሽ ከባድ የጭነት መኪኖች መጀመርያ ኢትዮጵያ የገቡ ጊዜ ነበር ብለዋል።

ያኔ እነዚህ ከባድ ተሽከርካሪዎች ኢትዮጵያ ሲገቡ መለዋወጫቸው እና የሚሰሩበትን ጋራጅ ማግኘት ከባድ ስለነበር በዚህ ላይ ደግሞ ስማቸው ከአደጋ ጋር ተደጋግሞ ይነሳ ስለነበር መድን ሰጭ ኩባንያዎች ሙሉ ሽፋን ለመስጠት ያፈገፍጉ ነበር ወይንም የሚጠይቁትን አረቦን ከፍ ያደርጉ ነበር። 

በሂደት ግን የሲኖ ትራክ መኪና መለዋወጫ በስፋት ሀገር ውስጥ ሲገባና የጥገና ባለሙያዎችም ቁጥር ሲጨምር ሲገቡ  የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም በስፋት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ያሉን የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ ጉዳይም ልክ እንደ ሲኖ ትራክ መኪኖቹ እየተስተካከለ እንደሚሄድ እምነታቸው መሆኑን የመድን ድርጅት የሰራ ሃላፊዎች ገልጸውልናል።

ከህብረት ኢንሹራንስ መረዳት እንደቻልነውም  ሁሉም ቅርንጫፎች የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የተመለከተ ጉዳይ ለዋና መስሪያ ቤት ሳያሳውቁ ምንም ውሳኔ እንዳያሳልፉ መታዘዛቸውን ነው። 

ዋዜማ እንደተረዳችው በሀገሪቱ ካሉ 20 ከሚደርሱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለኤሌክትሪክ መኪኖች በአንጻሩ ሙሉ ሽፋንን እየሰጠ ያለው አንድ ኩባንያ መሆኑን እና እሱም የሚጠይቀው አረቦን ከፍተኛ መሆኑን ነው። ሌሎቹ ግን ገና በጥናት ላይ ነን የሚሉ ናቸው።ይህም የኤሌክትሪክ መኪና ገዥዎችን ስጋት ከፍ አድርጎታል። [ዋዜማ]