Former TPLF veteran and current ARENA Party Chair Gebru Asrat

ዋዜማ ራዲዮ-በሀገር ቤት ህጋዊ ተብለው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተንሰራፋው አፈናና የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ ሳቢያ ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ለማድረግ ፈተና አለባቸው። አንዳንዶች እንደውም መኖራቸው ለገዥው ፓርቲ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ከመሆን የሚያልፍ አልሆነም። እንዲህ እንደሰሞኑ ተቃውሞ በሚበረታበት ወቅት ተቃዋሚዎች የህዝቡን አጀንዳ ይዘው አደባባይ ለመውጣት ትልቅ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ነው። በሰሞኑ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ምንጩ ከትግራይ የሆነውን አረና እንዲሁም የተለያዩ ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው መድረክና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት አባል የሆነው ኢዴፓ ምን እያደረጉ ነው ብለን ተመልክተናል። 

መዝገቡ ሀይሉ ዝርዝሩን በድምፅ አሰናድቶታል፣አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ

የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ /ሕወሐት/ ቀደምት መስራች በነበሩበትና በኋላም በኢሕአዴግ መንግስት ውስጥ ከፌደራል መንግስት ሀላፊነት እስከ ትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት ባገለገሉት አቶ ገብሩ አስራት የተመሰረተው አረና ለሉአላዊነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲበገዥው ፓርቲ ላይ ጠንካራ ትችት ሰነዘረ። አረና የወልቃይት ጉዳይ ሕዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) የሚያስፈልገው ነው የሚል አቋም እንዳለው አስታውቋል፡፡ በወቅታዊው የሀገሪቱ ሁኔታ ላይ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እና የፓርቲዎች ጥምረት የሆነው መድረክም አቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡

በትግራይ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በብቸኝነት ያለተፎካካሪ ፓርቲ ለዓመታት ሲንቀሳቀስ የነበረውን የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ /ሕወሐትን/ ለመገዳደር ከሕወሐት ለሁለት መሰንጠቅ በኋላ በተቃዋሚነት በቆሙት በነባር የሕወሐት ታጋዮች በነ ወ/ሮ አረጋሽ አዳነናበአቶ ገብሩ አስተባባሪነት የተመሰረተው አረና ፓርቲ በትግራይ ክልል ከሕወሐት በተሻለ ደጋፊ ማግኘቱ በብዙዎች ዘንድ ሲነገር ይሰማል።

በቅርቡ በአማራ ክልል የወልቃይት የማንነት ጥያቄ እና በኦሮሚያ የአ/አ አጎራባች አካባቢ መሬቶችን በተመለከተ በተነሱ ግጭቶች ሰዎችመሞታቸውን ተከትሎ ብዙ ፓርቲዎች መግለጫ መስጠታቸው የሚታወስ ሲሆን አረና ገዢው ፓርቲ አፋጣኝ መፍትሔ የሚያሰፈልገውን ጉዳይ ያለአግባብ በማዘግየት የችግሩ ምንጭ ሆኗል ይላል፡፡

የወልቃይት ጠገዴን የማንነት ጥያቄን በተመለከተ ኢህአዴግ በቅርቡ በመቀለ ከተማ ጉባኤውን ባደረገ ጊዜ ጥያቄው ቀርቦለት የነበረቢሆንም እንደ ፌደራል መንግስት ለችግሩ ቀጥተኛ መፍትሔ መስጠት ሲገባው ጉዳዩን የትግራይና የአማራ ክልሎች ተነጋግረውእንዲፈቱት በይደር ማለፉ አሁን ለተፈጠረው የከፋ ግጭት  ምክንያት መሆኑን ብዙ ወገኖች ይስማሙበታል።

በትግራይ ክልል እንቅስቃሴ የሚያደርገው አረና የትግራይን እና የአማራን ክልል የሚመለከተው የወልቃይት ጉዳይ ሊፈታ የሚችለው በውሳኔ ሕዝብ ነው የሚል አቋም አለው፡፡

 የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ ጉዳይ በህዝበ ውሳኔ ይፈታ የሚለው አረና ፓርቲ እንደ አስቸጋሪ ጉዳይ ያነሳው ህዝብ ውሳኔውንለማድረግ ከነባሩ ነዋሪ እኩል ሆን ተብሎ የሚደረግ አዳዲስ ስዎችን በአካባቢው የማብዛት ጉዳይ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ ይህንን ለመከላከል ደግሞ የአካባቢውን ሽማግሌዎችንና ታዋቂ ግለሰቦችን መጠቀም ያስፈልጋል ይላል።

የመድረክ ፓርቲ አባል ድርጅት የሆነው አረና ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት በ2007 አምስተኛው ዙር አጠቃላይ ሀገር አቀፍ ምርጫ ብዙእጩዎችን በትግራይ ለማስመረጥ ማዘጋጀቱንና ነገር ግን ሕወሐት በምርጫ ቦርድ በኩል ተጽእኖ እያሳደረብኝና አባላቴንም እያሰረብኝነው በምርጫው ውስጥ የምቆየውም በችግር ውስጥ ነው ሲል ደጋግሞ ተናግሮ ነበር። በ2007 ምርጫ ነበር ብሎ እንደማይቀበል መግለፁም ይታወሳል፡፡

ወቅቱ ኢህአዴግ በሙሉ ድምፅ መርጦኛል ያለው ህዝብ ብቻ ሳይሆን በገንዘብ ጭምር የሚደግፋቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይቀር ኢሕአዴግን ፊት የነሱበት መሆኑ እየታየም ነው፡፡

በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተነሳውን የህዝብ ጥያቄ እንዲያወግዝለት ገዥው ፓርቲ በጠራው የጋራ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤት ውስጥ አባል የሆነው ኢዴፓ በመገናኛ ብዙሃን የተላለፈውንና የሰሞኑን የህዝቡን ጥያቄ ሁሉም ፓርቲዎች ከህግ ውጭ ነው ብለው አውግዘዋል የሚለውን መግለጫ የኔን አቋም አይወክልም ብሏል፡፡ ኢዴፓ ም/ቤቱ ተቃውሞ ማሰማቴን በመደበቅ በመግለጫው የተስማማሁ አስመስሎ በማቅረቡ ምክንያት ከጋራ ምክር ቤቱ ልወጣ እችላለሁ ሲል አስታውቋል፡፡

የሰሞኑን ተቃውሞ እንዲያወግዝ በገዥው ፓርቲ የተጠራውን ስብሰባ የመሩት የመኢብን ፓርቲ ሊ/ መንበር አቶ መሳፍንት ኢዴፓንጨምሮ የትኛውም ፓርቲ አሁን ባለው ሁኔታ ከምክር ቤቱ አይወጣም ምክንያቱም ጉዳዩ የህልውና ጉዳይ ነው  ኢዴፓም ከማስፈራራትአልፎ ከምክር ቤቱ  አይወጣም ሲሉ ተናግረው በስብሰባውም ላይ ኢዴፓ የተለየ ሐሳብ ስለማቅረቡ እርግጠኛ አይደለሁም ብለዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዜና መድረክ በበኩሉ ባወጣው ወቅታዊውን የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚመለከት መግለጫ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተነሣው የህዝብ ተቃውሞ ኢህአዴግ እንደሚለው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወይም ፀረ ሰላም ኃይሎች የጠሩት ሣይሆን ግፍና በደል ያንገፈገፈው ህዝብ ያቀረበው የመብት ጥያቄ የወለደው የህዝብ ቁጣ ነው ብሎታል፡፡

የመድረክ ሊ/መንበር  ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ ከሌሎች የሥራ አጋሮቻቸው ጋር በሰጡት መግለጫ የኢህአዴግ መንግሥት በዜጐች ላይ እያደረሰ ያለውን ጭፍጨፋ እንግልትና እስር በአስቸኳይ እንዲያቆም አሳስበዋል፡፡

ኢህአዴግ በኃይል እንጂ በዴሞክራሲያዊ አግባብ ህዝቡ ለሚያነሣቸው ጥያቄዎች መፍትሔ የመስጠት ባህሉም ሆነ ባህሪ የሌለውበመሆኑ የሀገራችን ችግር እየገዘፈ ዛሬ ካለበት እጅግ አሣሣቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ያለው መድረክ ህጋዊ የሆነ የመብት ጥያቄ ይዞና ብሶትፈንቅሎት ለሰልፍ የወጣን ህዝብ ለመጨፍለቅ በቂ አቅም አለኝ ብሎ በአደባባይ መናገሩ  ኢሕአዲግ ለህዝብ ያለውን ንቀት የሚያሣይነው ብሏል፡፡

አሁን እየተቀጣጠለ ያለው የህዝብ የእምቢታ እንቅስቃሴ ምክንያቱ ራሱ ኢህአዴግ ያመጣው ችግርና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስርአቱን ለመቃወም ያደረጓቸው ሙከራዎች የመታፈናቸው ውጤት  ነው ሲል መድረክ ያብራራል፡፡

መድረክ በመግለጫው ኢህአዴግ የህዝብ ጭፍጨፋውን የገፍ እስሩንና አፈናውን በአስቸኳይ በማቆም ጭፍጨፋውን ያደረሱትንና ትዕዛዝ የሰጡትን የመንግሠት ባለሥልጣናት ለፍርድ እንዲቀርቡ ፣ ለተጐጂዎቹም ካሣ እንዲከፈል ጥያቄ አቅርቧል፡፡