book collectionዋዜማ ራዲዮ-በክረምት ወትሮም አንባቢ ይበረክታል፡፡ አንባቢ መበርከቱን የሚያውቁ ሁሉ ሥራዎቻቸውን ለአንባቢ የሚያቀርቡት ከግንቦት አጋማሽ  እስከ ነሐሴ ባሉት ወራት ነው፡፡ ከወዲያኛው ሳምንት ወዲህ ብቻ በርከት ያሉ ጠቃሚ መጻሕፍት ለገበያ ቀርበዋል፡፡ አንዳንዶቹን በወፍ በረር ከዚህ እንደሚከተለው እንቃኛቸዋለን፡፡

ባቢሌ ቶላ

የቀይ ሽብር ሰቆቃን ለእንግዝኛ አንባቢ ያስተዋወቀ ዝነኛ የብዕር ስም ነው ይላሉ ፀሐፊውን የሚያውቁ፡፡ እርሱ የእንግሊዝኛ ቅጂውን የጻፈው በ1989 እ አውሮፓውያን አቆጣጠር ነው፡፡  በወቅቱ ባገሪቱ የተንሰራፋው የያን ጊዜው ወታደራዊ መንግሥት ከሚያሳድዳቸው የህተመት ዉጤቶች አንዱ ስለነበረ አገር ቤት የሕትመት ብርሃን ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ ደራሲው ከዚያ ክፉ ጊዜ ጀምሮ በአንዲት የአፍሪካ አገር ራሱን ሸሽጎ ነው የሚኖረው ይባላል፡፡ ባቢሌ ቶላ፡፡ የዋናው መጽሐፍ የእግሊዝኛ ቅጂው ርዕስ To Kill A generation- The Red Terror in Ethiopia ነበር፡፡  አውግቻው ተረፈ ‹‹የትውልድ እልቂት-ቀይ ሽብር በኢትዮጵያ›› ሲል ነው ወደ አማርኛ የመለሰው፡፡ በእርግጥ ይህ የትርጉም ሥራ ኢህአዴግ አገሪቱን እንደተቆጣጠረ ከ2 ዓመት በኋላ ታትሞ ነበር፡፡ ዘንድሮ በድጋሚ ለገበያ ሲቀርብ ታዲያ ከ23 ዓመታት በኋላ መሆኑ ነው፡፡

የባቢሌ ቶላን መጽሐፍ ‹‹ፀጋዬ ወርቁ  አሳታሚ›› ነው ያሳተመው፡፡ ኢምፕረስ ማተሚያ ቤት ነው መባዛቱ ተመልክቷል፡፡ ካለፈው ሳምንት ወዲህ በ69 ብር ተመን ለአንባቢ እየተዳረሰ ነው፡፡

ሙሉጌታ ሉሌ

ይህ ስም በራሱ ብዙ ይናገራል፡፡ በሞት ከተለየን ስንት ዓመት ሆነው?

የሙሉጌታ ሉሌን ሥራዎች ሴት ልጁ ኤዶም ሙሉጌታ ሉሌ መልክ አሲዛ የሕትመት ብርሃን እንዲያገኝ ብዙ ደክማለች፡፡ ዛሬ አርብ ነሐሴ 13 በዕለተ ቡሔ ለገበያ የቀረበው የሙሉጌታ ሥራ ‹‹ ሰው ስንፈልግ ባጀን›› የሚል ቆንጆ ርዕስ ተሰጥቶታል፡፡ ሽፋኑ በብዙ የቀድሞው የጦቢያ መጽሔት መስሎች መዥጎርጎሩ ያለምክንያት አይደለም፡፡ የነጻው ፕሬስ እንዲህ እንደዛሬው ‹‹አለ ወይስ የለም?›› መባል ሳይጀምር ያኔ በደጉ ጊዜ የጦቢያ መጽሔት አንጸባራቂ የፖለቲካ ጋዜጣ ነበረች፡፡ ፈጣሪዋ ደግሞ ሙሉጌታ ሉሌ ነበር፡፡ ‹‹ፀጋዬ ገብረመድኅን አርአያ›› በሚል የብዕር ስም አያሌ ጽሑፎችን በዚሁ መጽሔት ያስነበበን እርሱ ነበር፡፡ ‹‹ስንሻው ተገኝ›› የሚለው የብዕር ስምም የርሱ ነበር ይባላል፡፡

በአንድ ወቅት ለምን በብዕር ስም መጻፍ እንደሚቀናው ተጠይቆ ሲናገር ‹‹ከሙሉጌታ ሉሌ ብዬ በመጻፍ ሰው ስለኔ ዉይይት ከሚያደርግ መልዕክቴን ቢነጋገርበት ይሻላል በሚል ነው›› ብሎ መለሰ፡፡

ሙሉጌታ ሉሌ ከ50 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ፀሐፊ፣ የታሪክና የፖለቲካ ተንታኝ በመሆን ለሚወዳት አገሩ አገልግሏል፡፡ ይህ መጽሐፉም በነዚህ ዓመታት ዉስጥ የጻፋቸው መጣጥፎቅ ቅንብር ነው፡፡ ‹‹ልሳነ ሕዝብ›› እና ‹‹ጦቢያ›› መጽሔቶች ላይ ካስነበባቸው ጽሑፎቹ ምርጥ የሚባሉት ተመርጠው ነው ዛሬ ‹‹ሰው ስንፈልግ ባጀን›› መጽሐፍ የተወለደው፡፡

The late Mulgeta Lule-Photo SM
The late Mulgeta Lule-Photo SM

እስኪ አጭር የሕይወት ታሪኩን እናውሳ፡፡

ሙሉጌታ ሉሌ በ1933 ዓ.ም ነበር የተወለደው፡፡ የትውልድ ቦታው ግደበረት ነው፡፡ አባትና እናቱ በንግድ ሥራ ይተዳደሩ ነበር፡፡ ሙሉጌታ ለቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ ነው፡፡ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት አምቦ ከተማ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱን ተማረና፣ 2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ደብረብርኃን ኃይለማርያም ማሞ አጠናቀቀ፡፡ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ ገብቶ ደግሞ በፖለቲካ ሳይንስና ሥነ-መንግሥት ዘርፍ የ4 ዓመት ትምህርቱን በማታው ክፍለጊዜ ተከታትሏል፡፡

የመጀመርያ ዲግሪውን ከተቀበለ በኋላ ሙሉጌታ ሉሌ በባይብል አካዳሚ የታሪክና የአማርኛ መምህር ሆኖ አገልግሏል፡፡ በዚያ ቆይታው ታዲያ የአሁኖቹን ኃያላን እነ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን፣ እነ ፕሮፌሰር ላጲሶ ጋዲቦን እነ አቶ ሌንጮ ለታን አስተምሯል፡፡ ይህ የሆነው በ1955 ዓ. ም አካባቢ ነው፡፡

ሙሉጌታ ሉሌ በኤርትራ የቀይ ኮከብ ዘመቻ ሲጀመር በበዓሉ ግርማ የተመራውን የጋዜጠኞች ቡድን በምክትል ኃላፊነት እየመራ እዚያው ቆይቷል፡፡ አቶ ሙሉጌታ በኢትዮጵ ፕሬስ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ በመሆን እስከ 1983 የመንግሥት ለውጥ ድረስ አገልግሏል፡፡

የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ በብዕሩ ለመፋለም የቆረጠው ሙሉጌታ ጦቢያ መጽሔትን ፈጠረ፡፡ ከዚይን ጊዜ ጀምሮ በከፍተኛ የደኅንነት ክትትልና ወከባ ዉስጥ ቆይቷል፡፡ 16 የሚሆኑ የክስ ፋይሎች ተከፍተውበታል፡፡ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በመኪና የተቀነባበረ የግድያ ሙከራ አድርጎበት በተአምር እንደተረፈም ተናግሯል፡፡

የሙሉጌታ ሉሌ አዲሱ መጽሐፍ ‹‹ሰው ስንፈልግ ባጀን›› ገና ቅጽ አንድ ነው፡፡ ሌሎች ሥራዎቹ በቅጽ 2 ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ አታሚው ፋርኢስት ማተሚያ ሲሆን በ81 ብር ለአገር ዉስጥ አንባቢ፣ በ30 ዶላር ለዉጭ አንባቢ ቀርቧል፡፡

አበራ ጀምበሬ፣ ኤስ ጴጥሮስ፣ ተመስገን ደሳለኝ

የበላይ ዘለቀ ታሪካዊ ልቦለድ በአበራ ጀምበሬ ተጽፎ በ1983 ታትሞ ነበር፡፡ ትናንት በድጋሚ ለሕትመት በቅቷል፡፡ 280 ገጾች አሉት፡፡ ዋጋው 81 ብር ይባላል፡፡ ‹‹የአድዋው ጀግና ልዑል ራስ መኮንን›› ኤስ ጴጥሮስ ፔትሪዲስ  ጽፎት እንዲሁ በተመሳሳይ ለሕትመት በቅቷል፡፡ ወፈር ባለ የድሮ የሚመስል ጽሑፍ ነው የተጻፈው፡፡ የገጹ ብዛት ከ450 ይልቃል፡፡ ዋጋው 102 ብር ተተምኗል፡፡ 

ዝዋይ ማረሚያ የሚገኘውና ደፈር ባሉ ጽሑፎቹ የምናውቀው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እርሱን የሚመስል ርዕስ የሰጠው መጽሐፉ ገበያ ከዋለ ገና 3 ቀናት አልሞላዉም፡፡ ‹‹የፈራ ይመለስ›› ይሰኛል፡፡ 260 ገጾች ያሉት ሲሆን ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል በተዘጉበት ጋዜጠና መጽሔቶች ያተማቸው ሥራዎቹን ነው በመጽሐፍ መልክ አበጅቶ ያቀረበው፡፡ መቅድሙን ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም ጽፈውለታል፡፡ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ና አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከያሬድ ጥበቡ ጋር በመሆን በመጽሐፉ ጀርባ ደራሲውን ደመቅ ያለ አድናቆትና ሙገሳ ችረውታል፡፡ ተመስገን ይህን መጽሐፉን እጅግ ለሚወዳቸው አባቱ አቶ ደሳለኝ ዋሲሁን መታሰቢያ ያደረገው ሲሆን ‹‹ለልጆችህ ራስህን አሳልፈህ የሰጠህ ቀናኢ ዜጋ ስለነበርክ መንግሥተ ሰማያት መዉረስህን ቅንጣት አልጠራጠርም›› ብሏቸዋል፡፡

በተመስገን ደሳለኝ ‹‹የፈራን ይመለስ›› መጽሐፍ ዉስጥ በገዢው ፓርቲ ዉስጥ የተሰገሰጉ ግለሰቦች ከፍ ባለ ደረጃ ተብጠልጥለዋል፡፡ እነ ሬድዋን ሁሴን፣ እነ ሽመልስ ከማል፣ እነ ፕሮፌሰር አንድሪያስ… ማን የቀረ አለ?

ከመጽሐፉ አንዱን ገጽ በድፍረት ገለጥ አድርጌ ማንበብ ጀመርኩ፡- እንዲህ ይላል-

‹‹ከአንድሪያስ ምሁርነት ኢትዮጵያ ምን አተረፈች? መቼም ለዚህ ጥያቄ የእንድሪያስ አድናቂዎችም ቢሆኑ ምላሽ የላቸውም፡፡ እኛም የለንም፣ ምናልባት ከዉብ የእንግዝኛ ቋንቋ ችሎታ ጋር ‹‹ቢትልስ›› ለብሶ መንጎማለል የሀገር ገጽታ ይገነባል ካልተባለ በቀር፡፡

የተመስገን ደሳለኝን ‹‹የፈራ ይመለስ›› መጽሐፍ አተምኩ የሚል ማተሚያ ቤት የለም፡፡ አሳታሚውም እንዲሁ በጽሑፍ አልተቀመጠም፡፡ ተመስገን ለምን እንደታሰረና በማን እንደታሰረ የአታሚና አሳታሚ በዉል አለመገለጥ በራሱ መልስ ይሰጣል፡፡