Oromia police patrol
Oromia police patrol

ዋዜማ ራዲዮ- በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች እየተቀጣጠሉ ያሉ አመጾችን ለመቆጣጠር በሚደረገው ትግል የኦሮሚያ ፖሊስ ዝቅተኛ ተሳትፎና ተነሳሽነት እያነጋገረ ነው፡፡ ባለፉት ቀናት ብቻ አለምገናና ሰበታ አካባቢ በነበሩ መጠነ ሰፊ አመጾች አስራ ሁለት ፋብሪካዎች በከፊልና ሙሉ በሙሉ መውደማቸውና ከ60 በላይ ተሸከርካሪዎች መቃጠላቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ የከረረ የተቃውሞ ሂደት ላይ የአይን እማኝ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ለዋዜማ እንደተናገሩት የኦሮሚያ ፖሊስ ታቃውሞዎችን ለማብረድ እምብዛምም ፍላጎት አይታይበትም ነበር ይላሉ፡፡

በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይከተቃጠሉ ፋብሪካዎች ዉስጥ ከፊሎቹ የፌዴራል ፖሊስ ቀድሞ መድረስ ባለመቻሉ የተነሳ ብቻ መትረፍ እየቻሉ ወድመዋል የሚሉት እነዚህ ታዛቢዎች የክልሉ ፖሊሶች ላይ አመጹን በማብረድ ረገድ ዳተኝነትና ፍላጎት ማጣት በእጅጉ ይታያል ብለዋል፡፡

“በርግጥ በአካባቢዉ ለመድረስ ጊዜ አይወስድባቸውም፡፡ ቶሎ ይመጣሉ፡፡ ኾኖም ልጆች ተሰብስበው ጎማ ሲያቃጥሉና ንብረት ሲያወድሙ ዳር ቆመው ከማየት ባለፈ ብዙም ከፍ ጥረት ሲያደርጉ አላየንም ” ይላሉ በአለምገና ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ፡፡

ብዙዎቹ ፖሊሶች ከዋና መንገድ ላይ አማጺዎችን ከማባረር፣ መንገድ የዘጉ ድንጋዮችን ከማንሳት ያለፈ ሥራ ሲሰሩ አላየንም ያሉ ነዋሪዎች ፌዴራል ፖሊስ ከደረሰ በኋላ ብቻ መነቃቃት ይታይባቸዋል ይላሉ፡፡ ይህ ለምን ሊሆን እንደቻለ የተጠየቁ ነዋሪዎች ከፊሎቹ “ምናልባት በአመጹ ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ ወንድሞቻቸው ላይ እጃቸውን ማንሳት ስላልፈለጉ ይሆናል” ሲሉ ሌሎች ደግሞ በኤሬቻ የተፈጠረው ነገር ልቡ ያልተሰበረ የኦሮሞ ልጅ አለ ወይ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

የኦሮሚያ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሰለሞን ታደሰ ትናንት ማምሻውን መንግስት ዘመም ለሆነው ሬዲዮ ፋና እንደተናገሩት አንዳንድ ወረዳዎች ላይ የተነሳው ሁከት ከፖሊስ ቁጥጥር ዉጭ እንደነበር አምነው የሁከቱን ዓላማ ያልተገነዘቡ ወጣቶችና የነገ ሀገር ተስፋዎች በኃይል ማረም ተገቢ ባለመሆኑ ነው የክልሉ ፖሊስ ከፍተኛ ትእግስት ያሳየው ብለዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ዛሬ አለምገና አካባቢ መጠነኛ የንግድና የሰው እንቅስቃሴ ቢታይም ስፍራው በፌዴራል ፖሊስ ከበባ ዉስጥ ሆኖ መቆየቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ ሌሊቱን የወጣቶች አፈሳ በተጠናከረ መልኩ የቀጠለ ሲሆን በርካታ ታዳጊዎችና ወጣቶች ከየቤቱ እየታደኑ ወዳልታወቀ ስፍራ ተወስደዋል፡፡

ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን እንዲከፍቱ በክልሉ ፖሊስ እየተገደዱ እንደነበር የተናገረ ሌላው የአካባቢ ነዋሪ ፍቃደኛ ሆነው የከፈቱ ሱቆች ግን ለበቀል እርምጃ ተዳርገዋል ይላል፡፡ ለምሳሌ ዋጦ አዲስ ሰፈር አካባቢ አንድ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ በፖሊስ ተገዶ ሥራ በጀመረ በሰዓታት ዉስጥ የአካባቢው ወጣቶች ደርሰው ከፊል ንብረቱን በእሳት አውድመውበታል ይላሉ የአይን እማኞች፡፡