Tilaye Gete (PhD) PHOTO-MoE
Tilaye Gete (PhD) PHOTO-MoE

ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ ከአመታት በፊት የተጀመረው የጎልማሶች እና መደበኛ ያልሆነው ትምህርት ውጤታማ መሆን አልቻለም ተብሏል ።
በ2004 የተጀመረው እና 20.4 ሚልዪን ምንም አይነት ትምህርት ያላገኙ ጎልማሶችንና እድሜያቸው ከ15 – 60 አመት ያሉ ዜጎችን ለማስተማር በመንግሥት ያወጣው ፕሮግራም ውጤታማ አለመሆኑን የመንግሥት የስራ ሀላፊዎች ይናገራሉ።
በትምህርት ሚኒስቴር የጎልማሶች እና መደበኛ ያልሆነ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሀመድ አቡበከር ለዋዜማ እንደተናገሩት ፕሮግራሙ ውጤታማ ያልሆነው በመንግሥት ትኩረት በማጣቱ እና እራስን የቻለ በጀት ተመድቦለት እንዲንቀሳቀስ ከማድረግ ይልቅ ስራውን መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጂቶች በመተውና መንግስታዊ መውስቅሩ ውስጥ ተጠያቂነትን የሚያስከትል አሰራር ባለመኖሩ ነው ብለዋል ።
ፕሮግራሙ ከተጀመረ አምስተኛው መርሃ ግብር ላይ ቢደረስም በመንግስት ሀላፊዎች ትኩረት በማጣቱ እስከ አሁን የተሰራው ስራ ውጤት አለማምጣቱንና በሀገሪቱም በአሁኑ ወቅት በፕሮግራሙ መድረስ የተቻለው በፕሮግራሙ አምስተኛ መርሃ ግብርና ማብቂያ ላይ ሁሉንም 20.4 ሚሊዮን ጎልማሶች እና በወቅቱ ትምህርት ቤት ያልሄዱትን ለመድረስ እቅድ ቢያዝም መድረስ የተቻለው ለ 7.2 ሚሊዪን ብቻ ነው ሲሉ አቶ መሀመድ ለዋዜማ ገልፀዋል።

መንግስት በዳይሬክቶሬት ደረጃ ስራውን የሚመራ ክፍል ቢያቌቁምም ፕሮግራሙ ሊመራበት የሚችልበትን አደረጃጀትና ተጠያቂነትን የሚያስከትል የህግ ማእቀፍ ከማውጣት ይልቅ ፕሮግራሙን “አለ” ለማለት ያህል ብቻ በት/ት ሚኒስቴር ውስጥ ” በቂ በጀት የሌለውና የመጠየቅም የህግ ድጋፍ የሌለውን ክፍል ነው” በሚል ተናግረዋል ።
ዳይሬክቶሬታቸው ፕሮግራሙ እንዳይቌረጥ ያህል ረጂ ድርጅቶችን በማግባባት ከጄኔቫ ግሎባል ጋር በመሆን አምስተኛው መርሃ ግብር ላይ መድረሳቸውን የገለፁት ሀላፊው ምንም አይነት ትምህርት ያላገኙትን ከ13 ሚሊዩን የሚበልጡ ወገኖችን ለመድረስ እና መንግስትም ተገቢውን የበጀት ድጋፍ እና የህግ ተጠያቂነትን እንዲያወጣ በጎትጎታ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል ።
መንግስት ፕሮግራሙን በሀገር አቀፍ ደረጃ በመዘርጋት ክልሎች ጭምር ተግባራዊ እንዲያደርጉት ቢነድፍም በመላው የሀገሪቱ ክፍል ትኩረት በመነፈጒ ውጤታማ አልሆነም ተብሏል ።
የኢትዮጵያ መንግስት በ2004 ያወጣው ይህ የፕሮግራም አይነት በየሁለት አመት የሚታደስ ሲሆን አሁን ባለው የመንግስት ትኩረት ማጣት ምክንያት ረጂ ተቋማት የማይገኙ ከሆነ የፕሮግራሙን እጣ ፈንታ መናገርም ሆነ መገመት እንደማይቻል አቶ መሀመድ ለዋዜማ ገልጸዋል ።
መንግስት ለእስከአሁኑ ኘሮግራም ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጣ እና በቢሮው ስለ ታቀፋ የሰራተኞች ብዛት ሃላፊው ለዋዜማ ለመናገር አልፈቀዱም ። [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ ]

https://youtu.be/l8abxrKQ2U8