ዋዜማ ራዲዮ- ኅዳር 19፣ 2014 ዓ.ም በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ሁለት የአሶሴትድ ፕሬስ ዘጋቢዎች የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም ለሦስተኛ ጊዜ በአራዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርበው ለፖሊስ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ተፈቅዶለታል። ትናንት ችሎት ቀርበው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የተፈቀደባቸው ተጠርጣሪ ጋዜጠኞች፣ አሚር አማን እና ቶማስ እንግዳ ናቸው።

ፌደራል ፖሊስ ባለፈው ዓርብ በዋለው ችሎት ላይ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የጀመረውን ምርመራ እንዳልጨረሰ ገልጦ፣ ችሎቱ 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር። ፖሊስ በወቅቱ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የጠየቀው፣ ብሄራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ተጠርጣሪዎቹን የሚመለከቱ ቴክኒካዊ ማስረጃዎች ገና እንዳላከለት፣ ከተጠርጣሪዎች እጅ በተያዙ የኤሌክትሮኒክ መሳሪያዎች ላይ የሚደረገው የምርመራ ውጤት እንዳልደረሰው እና ለ18 የተለያዩ ንግድ ባንኮች ያቀረበው የተጠርጣሪዎችን የባንክ ገንዘብ ዝውውር የሚያሳየውን ማስረጃ ገና እየተጠባበቀ መሆኑን በመጥቀስ ነበር።

ሆኖም የተከሳሽ ጠበቆች ፖሊስ ከዚህ ቀደም የጠየቀውን ጥያቄ መላልሶ እየጠየቀ እንደሆነ እና ቀደም ሲል ችሎቱ በፈቀደለት ዘጠኝ ቀናት ውስጥ ምንም ተጨባጭ ሥራ እንዳልሰራ በመግለጽ፣ ለፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቀድለት እንደማይገባ እና ደንበኞቻቸውም በእስር መቆየት እንደሌለባቸው ገልጸው ተከራክረዋል። ችሎቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ፣ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን አጠናቆ ለሰኞ የካቲት 28 እንዲያቀርብ ጠይቆ ነበር።

በችሎቱ ትዕዛዝ መሠረት ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ለችሎቱ አቅርቧል። ችሎቱም የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ከተመለከተ በኋላ፣ ለመርማሪ ፖሊስ የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ቀን ፈቅዶለታል።

ፌደራል ፖሊስ ጋዜጠኞቹ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት ከተፈረጀው የኦነግ ሸኔ አመራሮችና ታጣቂዎች ጋር በአካል እና በስልክ በመገናኘት፣ ወደ ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ቶኬ ኩታዬ የተባለ ቦታ ድረስ በመጓዝ ጅሬኛ ረቡማ የተባለ የኦነግ ሸኔ ቡድን አዛዥ እንዲሁም 30 ያህል የቡድኑን ታጣቂዎች በማነጋገርና በድምጽ በመቅዳት፣ የቡድኑን ወታደራዊ እንቅስቃሴ በተንቀሳቃሽ ምስል በመቅረጽ፣ በአገር ውስጥ እና ውጭ ካሉ የአሸባሪው ቡድን አመራሮችና አባላት ተልዕኮ ተቀብለው ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ በመሞከር፣ በአሶሴትድ ፕሬስ እና በዓለማቀፍ ጋዜጠኝነት ሽፋን ያሰባሰቧቸውን መረጃዎችና ማስረጃዎች ኢትዮጵያ-ጠል ለሆኑ የአውሮፓ አገራት በመላክ እና አገራቱ ስለ ኢትዮጵያ የተሳሳተ አመለካከት እንዲይዙ እና ኦነግ ሸኔን እንዲደግፉ በመስራት ወንጀል ጠርጥሮ እንደያዛቸው የካቲት 16 ለዋለው ችሎት መግለጹ ይታወሳል።

በሌላ በኩል የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የሽብር ወንጀሎች ምርመራ ዘርፍ ሃላፊ ኢንስፔክተር ተስፋዬ ኦላኒ አሸባሪውን ኦነግ ሸኔ በዓለማቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ የተጠረጠሩ ሦስት ጋዜጠኞች በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ኅዳር 6፣ 2014 ዓ.ም በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ቀርበው ተናግረው ነበር።

ሃላፊው ጨምረውም፣ ጋዜጠኞቹ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ሚዳ ቀኝ ወረዳ የሚንቀሳቀሰውን የኦነግ ሸኔ ወታደራዊ እንቅስቃሴ በተንቀሳቃሽ ምስል በመቅረጽ እና ለቡድኑ ታጣቂዎች ቃለ መጠይቅ በማድረግ እንዲሁም ተጨማሪ መረጃዎችን በማሰባሰብ ተቀማጭነቱ ኬንያ ለሆነው ለግብጻዊው የአሶሴትድ ፕሬስ የምሥራቅ አፍሪካ ወኪል ለካሊድ ካዚኻ በመላካቸው በቁጥጥር ስር ስለመዋላቸው መናገራቸው አይዘነጋም። [ዋዜማ ራዲዮ]