Yinager Dessie- National Bank of Ethiopia, Governor.

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያን የባንክ እና ፋይናንስ ዘርፍን የሚያስተዳድሩ ህጎች ተመልሰው ታይተው እንዲከለሱ እና ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መመሪያ መሰጠቱን ዋዜማ ሬዲዮ ከምንጮቿ ሰምታለች። 

መመሪያው ከተሰጠ ጥቂት ሳምንታት ያለፉ ሲሆን ብሄራዊ ባንክ እየተለወጡ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ ማስተካከያዎች እንዲያደርግና ሀሳብም እንዲያቀርብ ይጠበቃል።

ማሻሻያ ለማድረግ ምክንያት ስለሆኑት ጉዳዮች የዘርፉ ባለሙያዎች እንደነገሩን የቴሌኮምና ዲጅታል ኩባንያዎች ወደ ፋይናንስ ዘርፉ መቀላቀል በመጀመራቸው ነባሩን ህግ ከአዳዲሶቹ ፍላጎቶች ጋር ማዋደድ በማስፈለጉ ነው።

ኢትዮ ቴሌ ኮም የጀመረው የቴሌ ብር አገልግሎትን ተከትሎ የሀገሪቱን የቴሌ ኮም ኢንዱስትሪ የሚቀላቀሉ ኩባንያዎች በተንቀሳቃሽ ስልክ ገንዘብን የማስተላለፍ አገልግሎት ላይ የመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተዋል። 

ሚያዝያ ወር ላይ አገልግሎቱን የሚጀምረው ሳፋሪ ኮም በተንቀሳቃሽ ስልክ የገንዘብ ዝውውር አገልግሎትን ለመስጠት ከመንግስት ፍቃድን እንደሚያገኝ ተስፋ በማድረግ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ እንደሆነ በመግለጽ ላይ ነው።  ሆኖም ገንዘብ ማዘዋወር የመሰሉ ስራዎች ባንክ ነክ በመሆናቸውና ይህ አይነቱ ስራ ደግሞ ለውጭ ኩባንያዎች የተፈቀደ ባለመሆኑ ግልጽ የሆነ አሰራር በህግ እንዲቀመጥ ያለመ ማሻሻያ እንደሚጠበቅም ነው የሰማነው።

የፋይናንስ ዘርፍን በተመለከተ የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ህግም ለውጭ ኩባንያዎች አሁንም ዝግ ያደረገ ነው። ነገር ግን የውጪ ኩባንያዎች በምን አግባብ በፋይናንስ ዘርፉ ተሳታፊ መሆን እንደሚችሉ ወይም እንደማይችሉ የተብራራ የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት አንዱ ለብሄራዊ ባንክ የተሰጠ የቤት ስራ ነው። 

በቅርቡ የጸደቀው የካፒታል ገበያ አዋጅ በኢንቨስትመንት ባንክና ተያያዥ ስራዎች ላይ የመሰማራትን እድል ለውጭ ገበያ ክፍት አድርጓል። ይህም ከሀገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ህግ ጋር የሚናበብበት መንገድም ከማሻሻያው ይጠበቃል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው መንግስት የውጭ ምንዛሬ ስለሚያስፈልገው የባንክ ሴክተሩን ለውጭ ኩባንያ መክፈቱ እንደማይቀር ፣ ይህም በፖሊሲ አማራጭ እየታየ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል። 

ይሁንና የፋይናንስ ዘርፉን በቅርብ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ለውጪ ኩባን ያዎች ለመክፈት መንግስት ዝግጁ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች የሉም። እንደባለሙያዎች አስተያየት መንግስት ባረቀቀው የ10 አመት የፋይናንስ ዘርፍ ፍኖተ ካርታ ውስጥ የባንክ ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች ለመክፈት አስቀምጦት ከነበረው ጊዜ አስቀድሞ እውን ሊያደርገው ይችላል።  [ዋዜማ ራዲዮ]