Debebe Eshetu
Debebe Eshetu

ዋዜማ ራዲዮ- ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ከመድረክ ከራቀ ዓመታትን ያስቆጠረው አንጋፋው ተዋናይ ደበበ እሸቱ ወደ ትያትር ሊመለስ ነው፡፡ ከአንድ ወር ተኩል በኋላ በብሔራዊ ትያትር ለመድረክ እንደሚበቃ በሚጠበቀው ትያትር ላይ ደበበ ታላቁን የግሪክ ፈላስፋ ሶቅራጥስን ሆኖ ይተውናል፡፡

ደበበ የሚተውንበት ትያትር “ባዶ እግር” የሚሰኝ ሲሆን ተመሳሳይ ትርጉም ከያዘው እና በአሜሪካዊው ጸሀፌ-ተውኔት ማከስዌል አንደርሰን ከተጻፈው “Barefoot in Athens” ተውኔት የተተረጎመ ነው፡፡ ወደ አማርኛ የተመለሰው ተውኔቱ በድራማ ዘውግ የሚሰራ ነው፡፡

እ.ኤ.አ በ1951 የተጻፈው የማክስዌል ተውኔት የሶቅራጠስን የመጨረሻ ቀናት የሚያሳይ ነው፡፡ የማያስከፍላቸው በርካታ ተከታይ ተማሪዎች የነበሩት ሶቅራጠስ ራሱን እንደ መምህር ይቆጥር የነበረ ቢሆንም በወቅቱ አቴናን በሚያስተዳድሩ ባለስልጣኖች ዘንድ ግን “ወጣቶችን የሚበክል” ተደርጎ ይወሰድ ነበር፡፡

ባልተለመዱ አስተምህሮቶቹ ደስተኛ ያልነበሩት የአቴና መሪዎች ሶቅራጠስን ሞት በሚያስፈርዱት በ“ሀገር ክሀደት” እና በ “ኑፋቄ ትምህርት” ሊከሱት ሲዘጋጁ በስፓርታዎች ይወረራሉ፡፡ የስፓርታዎች ወረራ በአቴና የነበረውን የዲሞክራሲ አገዛዝ እንዲያከትም ምክንያት ይሆናል፡፡ ለዕውነት እና ለዲሞክራሲ ሟች የሆነው ሶቅራጠስ በአቴናውያን መሪዎች ፊት አጥብቆ የሚከራከርላቸውን መርሆዎች በስፓርታዎች ጊዜም ሊያስጠብቅ ይሞክራል፡፡

ይህ አመለካከቱ ግን በስፓርታዎችም ዘንድ አልተወደደለትም፡፡ ጉዳዩ ወደ ችሎት ያመራል፡፡ በዓለም ታሪክ ውስጥ ከሚጠቀሱ የፍርድ ሂደቶች አንዱ የሆነው የሶቅራጠስ ችሎት የትያትሩ አንድ አካል ነው፡፡

ወደ 20 ገደማ ተዋንያንን የሚያሳትፈው ይህ ተውኔት በብሔራዊ ትያትር መድረክ ሊቀርብ ልምምድ ከተጀመረ አንድ ወር ከ15 ቀን አስቆጥሯል፡፡ ሳምንቱን ሙሉ ልምምድ እየተደረገበት የሚገኘው ትያትር የልምምድ የ“መጨረሻው ደረጃ” ላይ እንደደረሰ ምንጮች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡ በብሔራዊ ትያትር በሚቀርቡ ትያትሮች በተዋናይነት እየተሳተፈች የምትገኘው ወጧቷ ራሄል ተሾመ አንጋፋ እና ወጣት ተዋንያኖችን የቀየጠውን “ባዶ እግር” የማዘጋጀት ሚና ወስዳ እየሰራች ትገኛለች፡፡

ከተዋናያን መካከል በአዳም ረታ የ“ሎሚ ሽታ” ፊልም ብቃቷን ያሳያቸው እና በበርካታ ትያትሮች ላይ የተወነችው ኤልሳቤጥ መላኩ የሶቅራጠስን ሚስት ወክላ ትጫወታለች፡፡ እንደ እርሷ ሁሉ የአዲስ አበባ ትያትር እና ባህል አዳራሽ ፈርጥ የሆነው ስዩም ተፈራም በትያትሩ ቦታ አለው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፊልም ስራዎች ላይ በብዛት ሲሳተፉ የሚታዩት ነባሩ የብሔራዊ ትያትር ተዋናይ ሰለሞን ተካ ከአንጋፋዎቹ ይመደባሉ፡፡

ደበበ እሸቱ እንደ ትዕግስት ባዬ፣ ሄኖክ ዘርዐ ብሩክ፣ ሳሙኤል አካሉ እና ንጉሴ ባይሌን ለመሰሉ ወጣት ተዋናያን ልምዱን እያከፈለ አብሯቸው ለመተወን ወደ ትያትር መድረክ የቀረበው ከ10 ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ ደበበን በዚህ ዘመን ያሉ የትያትር አፍቃሪያን ከሀገር ፍቅር ትያትር ቤት ጋር ያይዙት እንጂ ብሔራዊ ትያትርን ለበርካታ ዓመታት ቆይቶበታል፡፡ ከተዋናይነት እስከ አዘጋጅነት እና ዋና ስራ አስኪያጅነት ሰርቶበታል፡፡ በተዋናይነት ከሰራባቸው ውስጥ “እናት ዓለም ጠኑ”፣ “ንጉስ ሊር” እና “ዋናው ተቆጣጣሪ” ይጠቀሳሉ፡፡

ከትያትር ዓለም ጠፍቶ የሰነበተው ደበበ እያለሰለሰም ቢሆን ወደ ፊልም መንደር ብቅ ሲል ሰንበቷል፡፡ “ሻፍት ኢን አፍሪካ”ን ጨምሮ ወደ ሰባት የሚጠጉ የውጭ ፊልሞች ላይ የተሳተፈው ደበበ ከዓመት በፊት ለዕይታ በበቃ እና በእስራኤል ሀገር በተሰራ “ሬድ ሊቭስ” (ቀያይ ቀንበጦች) በተባለ ፊልም ላይ ተውኗል፡፡ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ለሁለተኛ ጊዜ ከታሰረ በኋላ ወደ ጥበቡ ዓለም የተመለሰውም “ሰባ ሰላሳ” በተሰኘ ሀገርኛ ፊልም ነበር፡፡

በምርጫ 97 የቅንጅት ድምጽ የነበረው ደበበ የቅንጅት መስራች ፓርቲ በነበረው “ቀስተ ደመና” ውስጥ ከፍተኛ ተሳትፎ ነበረው፡፡ ምርጫውን ተከትሎ የቅንጅት አመራሮችን እና ጋዜጠኞች ለእስር ሲዳረጉ እርሱም ለሁለት ዓመት ያህል በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ወህኒ ቆይቷል፡፡