Yonathan Tesfaye
Yonathan Tesfaye

የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዮናታን ተስፋዬ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ አስመልክቶ በጻፋቸው የ”ፌስ ቡክ” ጽሁፎች ምክንያት በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰሰ፡፡

ላለፉት አራት ወራት በማዕከላዊ በእስር የቆየው ዮናታን ክስ የተመሰረተበት ዛሬ ጠዋት ወደ ልደታ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከተወስደ በኋላ ነበር፡፡ በዳኛ መጓደል ምክንያት ችሎት እንኳ ያልሰየመው የከፍተኛው ፍርድቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የዮናታንን ጉዳይ የተመለከተው በቢሮ ውስጥ እንደሆነ በቦታው የነበሩ እማኞች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ ለዮናታን ክሱ ተነብቦለታል፡፡

ስድስት ገጽ የሚፈጀው የዮናታን ክስ ተከሳሹ በ2001 ዓ.ም የወጣውን የጸረ-ሽብር ህግ አንቀጽን አራት ስር የተደነገገውን በመተላለፍ እንደተከሰሰ ያመለክታል፡፡ ከ15 ዓመት እስከ እድሜ ልክ እና ሞት የሚያስቀጣው አንቀጽ አራት “የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴር፣ ማነሳሳት እና ሙከራ” ወንጀልን የሚያስረዳ ነው፡፡

“ተከሳሽ የፖለቲካ፣ አይዲዮሎጂ ዓላማን ለማራመድ በመንግስት ላይ ተጽእኖ ለማሳደር፣ ህብረተሰቡን ወይም የህብረተሰቡን ክፍል ለማስፈራራት እና የሀገሪቱን መሰረታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ሕገ መንግስታዊ. ኢኮኖሚያዊ ወይም ማህበራዊ ተቋማትን ለማናጋትና ለማፈራረስ” በማሰብ ወንጀሉን እንደፈጸመ በክሱ ዝርዝር ተጠቅሷል፡፡ ክሱ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የቀጠለውን ህዝባዊ ተቃውሞ “አመጽና ብጥብጥ” ሲል የጠራው ሲሆን ጀማሪውም የ”ኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)” እንደሆነ በወንጀል ዝርዝሩ ላይ ያብራራል፡፡

ዮናታንንም “ከህዳር 24 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ በሚጠቀምበት ድህረ-ገፅ በተለይም በፌስ ቡክ ተጠቅሞ በሽብር ቡድኑ [ኦነግ] የተጀመረውን አመጽና ብጥብጥ ለማስቀጠል” እንደሞከረ ይወነጅለዋል፡፡ ተከሳሹ በተለያየ ጊዜ የጻፋቸውን 11 የፌስ ቡክ ጽሁፎች በምሳሌነት በማንሳትም ዮናታን “ቀስቃሽ ጽሁፎች በመጻፍ” ወንጀል በመፈጸሙ መከሰሱን ይገልጻል፡፡

ሀፍታሙ ቸኮለ በተባሉ የፌደራል አቃቤ ህግ አማካኝነት የቀረበው ክስ የሰው እና የሰነድ ማስረጃ እንደዚሁም ኤግዚቢት እንደተካተቱበት በክሱ ላይ ተመልክቷል፡፡ የሰው ምስክሮች ዝርዝር በምስክሮች ጥበቃ አዋጅ መሰረት ያልተጠቀሰ መሆኑን ክሱ ያሳያል፡፡ “የሰነድ ማስረጃ ናቸው” በሚል በአቃቤ ህግ የቀረቡት 11 ገጽ ጽሁፎች ግን “ተከሳሽ ከሚጠቀምበት ድህረ-ገጽ” የተወሰዱ እንደሆኑ በክሱ ተጽፏል፡፡ ተከሳሹ ሰጠ የተባለው 20 ገጽ “የእምነት ቃል”ም አብሮ መያያዙ ተገልጿል፡፡

የሽብር ድርጊት ለመፈጸም አሲሯል በሚል በዮናታን ላይ ኤግዚቢት ተብለው የቀረቡት አንድ ኖክያ ሞባይል፣ ሁለት ሲም ካርድ እና አንድ 64GB ሜሞሪ ናቸው፡፡

ዮናታን በሰማያዊ ፓርቲ ከነበረው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊነት በገጻ ፍቃዱ መልቀቁን ከማሳወቁ በፊት በ2007 ዓ.ም ምርጫ ፓርቲውን ወክሎ በቦሌ ክፍለ ከተማ ለፓርላማ የተወዳደረ ነበር፡፡