ንግድ ባንክና አዲስ አበባ መስተዳድር እየተወዛገቡ ነው

ዋዜማ ራዲዮ- በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ አማካይነት 18 ሺህ 576 የ40/60 የጋራ መኖርያ ኮንደሚኒየም ቤቶች የካቲት ወር ላይ ለባለ እድለኞች እጣ መውጣቱ የሚታወስ ነው።ከሰኔ ወር ጀምሮም ባለ እድለኞቹ የ40/60 የጋራ መኖርያ ቤቶች ምዝገባን ያከናወነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመሄድ የቤቱን ዋጋ አርባ በመቶ ክፍያ በማጠናቀቅ የቀሪ 60 በመቶ የቤቱን ዋጋ ከባንኩ ጋር የብድር ውል በማድረግ የቤት ርክክብ ሂደቱን ማከናወን ተጀምሯል።


ነገር ግን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጋራ መኖርያ ቤት እድለኞቹ ንግድ ባንክ ውል ለመፈጸም ሲሄዱ ለባንኩ ያቀረቡት የስምና እንዲሁም የጋብቻ መረጃ ለማጭበርበር ከፍተኛ አዝማሚያን ያሳየ መሆኑን የባንኩ ምንጮች ለዋዜማ ራዲዮ ገልጸዋል። በ2005 አ.ም የ20/80 እና የ40/60 የቤት መርሀግብር ምዝገባ ሲደረግ ቤት ያላቸው እንዲሁም የትዳር አጋሮችም በአንዴ የሁለት ኮንደሚኒየምም ሆነ የሌላ ቤት ባለቤት መሆን እንደማይችሉ ተደንግጓል።ነገር ግን አሁን የ40/60 ቤቶች ርክክብ ሲደረግ ይህን ህግ የመጣስ አዝማሚያዎች እንዳሉ ተስተውሏል ተብሏል።


ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው የቤቱን ርክክብ ለመፈጸም እጅግ በርካታ የቤት እድለኛ ግለሰቦች የግል መጠሪያ ስማቸውን ፣ የአባት ስማቸውን ፣ የአያት ስማቸውን እንዲሁም የእናት ስማቸውን በፍርድ ቤት ለመለውጥ አስወስነው ንግድ ባንኩ መረጃውን እንዲያስተካክልላቸው አቅርበዋል።በማቅረብም ላይ ያሉ አሉ።ይህም በቀድሞ ስማቸው የተመዘገበ ቤት ቢኖራቸው በዚያ ሳቢያ ኮንደሚኒየሙን እንዳያጡት በሚል ያደረጉት ነው የሚል ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዳሳደረበት ባንኩ ገልጿል።


ሌሎች ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የቤቱ ባለእድለኞች ደግሞ ለ40/60 ሲመዘገቡ “ያገባ” ይል የነበረ የጋብቻ ሁኔታ መረጃቸው “ያላገባ” በሚል እንዲቀየርላቸው ከወሳኝ ኩነቶች የተሰጠ ማስረጃን ለባንኩ በማቅረብ በማስተካከያው መሰረት እንዲስተናገዱ ጥያቄ ማቅረባቸውን እና በማቅረብ ላይ እንዳሉም ሰምተናል።ይህ የጋብቻ ሁኔታን ቀይሮ የማቅረቡ ሁኔታም የቤት እድለኞች በትዳር አጋራቸው በኩል ቤት ቢኖራቸው የ40/60 ተጠቃሚ መሆን ስለይችሉ ከእድሉ ውጭ እንዳይሆኑ የሚያደርጉት ለመሆኑ ጥርጣሬ እንዳለው ባንኩ ገልጿል።


የነገሩ በከፍተኛ ሁኔታ መደጋገም አሳስቦኛል ያለው ባንኩ ውል እየተዋዋሉ ያሉት ባለእጣዎች ከዚህ በፊት ቤት ይኑራቸው አይኑራቸው መጣራት እንዴት ይቻላል ? የሚለውን ለማወቅ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ደብዳቤ መጻፉን ባንኩ ነግሮናል።ባንኩ ለቢሮው ለላከው ይህ ጥያቄ ከቢሮው ያገኘው ምላሽ ; የ40/60 መኖርያ ቤቶች ምዝገባ ያካሄደው ንግድ ባንክ በመሆኑ : አጠቃላይ የሀርድ ኮፒ ፣ የሶፍት ኮፒም ሆነ የተደራጀ ሲስተም በእጁ ስላለ የባለ እድለኞችን የስም ለውጥ የመረጃ ማስተካከያና የመሳሰሉትን የደንበኞችን ጥያቄ በፍርድ ቤት ተወስኖ በሚቀርብ የስም ለውጥ እንዲሁም የመረጃ ማስተካከያ አገልግሎት እንዲሰጥ ቤቶች አስተዳደር መወሰኑን ለባንኩ በደብዳቤ ገልጿል።

ሆኖም የአዲስ አበባ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ መፍትሄ ብሎ የላከው ደብዳቤ ስጋቴን የሚቀርፍ አይደለም ብሏል ባንኩ።የንግድ ባንኩ ስጋት ባለእጣዎች የተለያዩ መረጃ ለውጥን በማድረግ በተለያየ መንገድ የቤት ባለቤት ሆነው ሳለ በድጋሜ የጋራ መኖርያ ቤት ባለቤት ይሆናሉ የሚል ሲሆን ከቤቶች ልማት ቢሮ የቀረበለት መፍትሄ የመረጃ ለውጥ እንዲደረግላቸው የሚጠይቁ ግለሰቦች በቀድሞ ስማቸው ቤት ይኑራቸው አይኑራቸው ለማወቅ አያስችልም የሚል ነው። ባንኩም ይህን የሚያጣራበት መንገድ የለውም። ነገሩም መረጃም የማስተካከል ብቻ ሳይሆን የኮንደሚኒየም መርሀ ግብሩ ከታሰበለት አላማ ውጭ ሆኖ ግለሰቦች የተደራቢ ቤት ባለቤት ሆነው ኢ ፍትሀዊነት እንዳይፈጠር የማድረግ ስለሆነ የቤቶች ቢሮ እንዲያስብበት ሲል ባንኩ ይታሰብበት ብሏል።

ንግድ ባንኩ ለእድለኞች ቀድሞ በስማቸውም ሆነ በጋብቻ ቤት ይኑራቸው አይኑራቸው ከሚመለከታቸው ከክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ጋር በመነጋገር በተለይ የመረጃ ለውጥ እንዲደረግላቸው በጠየቁ ግለሰቦች ላይ ማጣራት እንዲደረግ ጠይቋል።ይህ ሳይሆን ቀርቶ አንድ ግለሰብ የሁለት ቤት ባለቤት ቢሆን ባንኩ ሀላፊነት እንደማይወስድ ገልጿል።ባንኩ የጋብቻን ሁኔታ ለውጥን ጨምሮ ሌሎች መረጃዎች እንዲቀየርላቸው የሚጠይቁ ባለእድለኞችን ለማስተናገድ መጀመርያ ለቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ እንደሚያሳውቅና ለዚህ የባለ እድለኞችን የቀድሞና የአሁን መረጃን አያይዞ ቢሮው እንዲያጣራ እንደሚልክለትም ገልጿል። [ዋዜማ ራዲዮ]

ሌሎች የዋዜማ የድምፅ ዘገባዎችን ከታች ያድምጡ