• የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ሲወርድም ከሁለት አመት ከስድስት ወር በሁዋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ከታህሳስ 30 ቀን 2013 አ.ም ጀምሮ በሁሉም ባንኮች ተግባራዊ እንዲሆን ያዘዘው የገንዘብ ማዘዋወር ገደብ ወደ ስራ ከገባ በሁዋላ በጥቁር ገበያ ያለው የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ቅናሽን አሳይቷል። ብሄራዊ ባንኩ በአንድ ባንክ በሳምንት ከአምስት ጊዜ በላይ ገንዘብ ማዘዋወርን አይቻልም ሲል ነው ለባንኮች መመሪያ ያስተላለፈው። ይህ መመሪያ ለሰራተኞች የሚከፈል ደሞዝንና መሰል የሂሳብ ዝውውሮችን አይመለከትም። የመመሪያው አላማም የህገ ወጥ ሀዋላ አዘዋዋሪዎች እንቅስቃሴ ላይ ጫናን ማሳረፍ እንደሆነ በሀገር ውስጥ የዜና አውታሮች መዘገቡ የሚታወስ ነው።

አሰራሩ ተግባራዊ ከሆነ ከታህሳስ 30 2013 በሁዋላ ከሁለት አመት ከግማሽ በሁዋላ ለመጀመርያ ጊዜ የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሬ መገበያያ ዋጋ ከእለት እለት ቅናሽን አሳይቷል። መደበኛ ባልሆነው የውጭ ምንዛሬ ገበያ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ54 ብር እየተገዛ በ54 ብር ከ50 ሳንቲም በላይ በሆነ ዋጋ እስከመሸጥ ደርሶ ነበር ። በዚህም ሳቢያ በባንኮችና እና በጥቁር ገበያ የአንድ የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ልዩነት ከ16 ብር በላይ ሆኖ ቆይቷል።ይህም ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከበፊቱም በባሰ ሁኔታ የዋጋ ግሽበትን ያመጣ ሆኗል። በተለይ ህወሀት በኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ፈጽሞ ከፌዴራል መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ በቆየባቸው ጊዜያት የውጭ ምንዛሬ ዋጋ በተለይም መደበኛ ባልሆነው ገበያ ንሯል።


ሆኖም ብሄራዊ ባንክ በአንድ ባንክ በአንድ ሳምንት ከአምስት ጊዜ በላይ በባንክ ሂሳብ ገንዘብን ማስተላለፍ የሚከለክለውን ህግ ካወጣ በኋላ ባልተለመደ ሁኔታ የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ቅናሽን አሳይቷል።

ይህን ዘገባ በሰራንበት ጥር 12 ቀን 2013 አ.ም በጥቁር ገበያ የአንድ የአሜሪካ ዶላር መግዣ 51 ብር ከ50 ሳንቲም ሲሆን መሸጫው ደግሞ ደግሞ 52 ብር ሆኗል። በመሸጫውም በመግዣውም ዋጋ ላይም በ12 ቀናት ውስጥ የ2 ብር ከ50 ሳንቲም ቅናሽ ታይቷል ። በባንኮችና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የአንድ አሜሪካ ዶላር ዋጋ ልዩነትም ከ16 ብር ወርዶ ከ12 ብር በታች ሆናል።

የታየው ቅናሽ መነሻም ብሄራዊ ባንክ በየጊዜው ያወጣቸው የገንዘብ ዝውውርን የሚገቱ መመሪያዎች መሆኑን ባለሙያዎች ነግረውናል። ከዚህ ቀደም በቀን ከአንድ ባንክ ከ50 ሺህ ብር በላይ ማውጣት የከለከለው ህግ በጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሬ ገበያ ላይ የተሰማሩ አካላት በባንክ ሂሳብ ገንዘብን በማዘዋወር የውጭ ምንዛሬን ለመገበያየት እንዲጠቀሙ ቢያደርጋቸውም አሁን ላይ በሳምንታዊ የባንክ ሂሳብ ዝውውር ላይም ገደብ መጣሉ መደበኛ ባልሆነው ገበያ ላይ የውጭ ምንዛሬን ለሚገበያዩ አካላት ለመገበያየት የሚያስችላቸውን ገንዘብ እንደልብ ማዘዋወር እንዳላስቻላቸው መረዳት ተችሏል። የውጭ ምንዛሬን በሚገዙትም ሆነ በሚሸጡትም በኩል የብር እንቅስቃሴ ገደቡ ጫና እየፈጠረ መሆኑም የጥቁር ገበያውን የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ዝቅ አድርጎታል።


በኢትዮጵያ የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡ ሰሞን ቅናሽ ከማሳየትም አልፎ ከባንኮች የመገበያያ ዋጋም በጥቂት ሳንቲሞች እስከማነስ ደርሶም ያውቃል። ይህ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የውጭ ምንዛሬ በእጃቸው ያላቸው ሰዎች ለባንክ እንዲሸጡ ካስጠነቀቁ በሁዋላ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ገና ወደ ስልጣን በመምጣታቸው ሰዎችም አዲስ አይነት አሰራር ሊመጣ ነው የሚል ፍራቻ ስላደረባቸው ነበር የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ከባንኮች ዋጋ እስኪያንስ ሰዎች እጃቸው ላይ ያለውን ምንዛሬ ለባንኮች ሲሸጡ ነበረ።

ነገር ግን ከጥቂት ቀናት በሁዋላ መደበኛ ባልሆነው የውጭ ምንዛሬ የታየው የዋጋ መውረድ መልካም ነው ሊባል ቢችልም ከባንኮችም ጋር ያለው የዋጋ ልዩነት በበቂ ሁኔታ ያልጠበበና ለገበያ መረጋጋት ዋስትና የሚሰጥ አይደለም። በተለይ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት የሚያግዙ ስልቶች ካልተቀየሱ ኢኮኖሚው ወደባሰ ችግር ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ።

ብሄራዊ ባንክ አሁን ተግባራዊ ያደረገው በሳምንት ከአምስት ጊዜ በላይ ገንዘብ ማዘዋወርን የሚከለክለውን ህግን ጨምሮ የብር ኖት ለውጥ ካደረገ በኋላ የተገበራቸው ህጎች የወረቀት ጥሬ ብር ዋና መገበያያ የሆነባትን ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ ለንግዱ ማህበረሰብ ከፍተኛ ፈተናን የደቀነ ሆኗል። [ዋዜማ ራዲዮ]