Omar_Guelleየጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌህ ስሞኑን ለመንግስታቱ ድርጅት ባቀረቡት አቤቱታ ከኤርትራ ጋር የገቡበት የድንበር ውዝግብ ሊፈታ ባለመቻሉ አለማቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ እንዲገብ ተማፅነዋል። የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በስልጣን እስካሉ ድረስ አካባቢው ሰላም ሊሆን አይችልም ብለዋል ጊሌህ።

የኢትዮጵያ የወደብ እስትንፋስ የሆነችው ጅቡቲ ፖለቲካዋ አምብዛም ጤናማ አይመስልም፡፡ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በህገመንግስቱ የተፈቀደውን የስልጣን ገደብ አስነስተው እነሆ ለሶስተኛ ዙር ሀገሪቱን እየመሩ ነው፡፡ ከዓመት በኋላ ስልጣናቸውን እደሚለቁ ቢናገሩም ተተኪያቸው ማን እደሚሆን እንኳ አይታወቅም፡፡ የጤናቸው ሁኔታም ስጋት አንዣቦበታል፡፡

(የቻላቸው ታደዝ ዝርዝር የድምፅ ዘገባ እነሆ)

ለበርካታ ዓመታት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መገለል የደረሰባቸው የአፋር ነፃ አውጭዎችም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል እንደገና ትጥቅ ትግል ጀምረዋል፡፡ የሰብዓዊ ፖለቲካ መብቶች ጥሰትም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ሀገሪቱ ከኤርትራ ጋር ያላት የድንበር ውዝግብም መፍትሄ ሊያገኝ አልቻለም፡፡
ኤርትራና ጅቡቲ በባዔል መንደብ ሰርጥ አቅራቢያ በሚገኘው ራስ ዱሜራ በተባለው ኮረብታ እና ዱሜራ በተባለ የቀይ ባህር ደሴት ላይ ባነሱት የይገባኛል ውዝግብ ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ለሦስት ጊዚያት ያህል ጦር ተማዘዋል፡፡ እኤአ በ2008ቱ ግጭትም አስራ ሁለት ጅቡቲያዊያን እና ቁጥራቸው ያልታወቀ የኤርትራ ወታደሮች ተገድለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ፀጥታው ምክር ቤትም ኤርትራን ጥፋተኛ በማድረግ እኤአ በ2009 ዓ.ም የመሳሪያ እና በተወሰኑ የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት ላይ ደግሞ የጉዞ እና የተቀማጭ ገንዘብና ንብረት እገዳ ማዕቀብ ጥሎባት ነበር፡፡ በኋላ ላይ ከሁለቱ ሀገሮች ጋር መልካም ግንኙነት ባላት ኳታር ሸማጋይነት እኤአ በሰኔ 2010 ዓ.ም የሰላም ስምምነት ደርሰው አወዛጋቢው ድንበርም በኳታር ወታደራዊ ታዛቢዎች ሲጠበቅ እንደኖረ ይታወቃል፡፡

ሆኖም ባለፈው መስከረም ወር የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኡመር ጌሌ ለተባበሩት መንግስታት ጠቅላላው ጉባዔ ያደረጉት ንግግር ኤርትራን ክፉኛ በመተቸት ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡ የኤርትራ መንግስት በአፈንጋጭ ባህሪው እየገፋበት ስለመሆኑ ያስታወሱት ፕሬዝዳንቱ “ለጠቅላላ ጉባኤው በተደጋጋሚ አቤቱታ ብናቀርብም እኤአ ከ2008 ጀምሮ ከፊል የሀገሬ ግዛት በኤርትራ ወረራ ስር ይገኛል” በማለት ነበር አቤቱታቸውን ያሰሙት፡፡

በወቅቱ የኤርትራ ስሌት ግልፅ ባይሆንም እርምጃዋ ኢትዮጵያን ከጅቡቲ ወደብ ጋር በሚያገናኛት ዋነኛ የንግድ መስመር ላይ አደጋ ስለደቀነ የኢትዮጵያ መንግስት ሰራዊቱን ወደ ድንበር ያስጠጋው ወዲያውኑ ነበር፡፡ በዚያውም ለጅቡቲ ሉዓላዊነት ያለውን አጋርነት አሳይቷል፡፡ ሆኖም የኤርትራ መንግስት ከዚያ በኋላ ተጨማሪ ስጋት ሊፈጥርባት አልቻለም፡፡
ሀገሪቱ ነፃነቷን እኤአ በ1977 ዓ.ም ካገኘች ጀምሮ ስልጣን ላይ ያለው የሱማሌ ኢሳዎች ፓርቲ የሆነው People’s Rally for Progress የተሰኘው ገዥ ፓርቲ ሲሆን ከጥቂት ዓመታት በፊትም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ጥምረት ፈጥሮ Union for Presidential Majority በሚል ስያሜ ስልጣኑን በብጨኝነት ተቆጣጥሯል፡፡ ፓርቲው ከመንግስት መዋቅር ጋር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ሆነዋል፡፡ የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣን መሆን ማለት በቀጥታ ከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ቦታን ያጎናፅፋል፡፡ ገዥው ፓርቲ እስከታች ባሉ መዋቅሮች የራሱን አባላት በመሰግሰግ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር ችሏል፡፡
ሆኖም የሀገሪቱ ፖለቲካ ከድሮም ጀምሮ በጎሳ በተለይም ደግሞ በቤተሰባዊ ዝምድና ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ከሀገሪቱ የሃብት እና ስልጣን ክፍፍል በመገለሉ ሳቢያ ያኮረፈው ህዝብ በርካታ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አናሳዎቹ አፋሮች ጠቅላይ ሚንስትርነቱን በአብዱልቃድር ሞሃመድ ካሚል አማካኝነት ቢይዙም ዋናው ስልጣን ሙሉ በሙሉ በኢሳ ተወላጁ ፕሬዝዳንት ኡመር ጌሌ ቁጥጥር ስር ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ ጭራሹንም በህገመንግስቱ በሁለት ዙር ተገድቦ የነበረውን የስልጣን ዘመናቸውን እኤአ በ2010 በማሻሻልና ገደቡን በማስነሳት ለሶስተኛ ዙር ተመርጠው ሀገሪቱን እስከ 2016 ድረስ በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ፕሬዝዳንት ጌሌ እንደ እርሳቸው በኢትዮጵያዊቷ ድሬዳዋ ከተወለዱት ፖለቲከኛውና ቱጃሩ አብዱራህማን ቦሬህ ጋር በተያያዘ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ቦሬህ ፕሬዝዳንቱ ህገመንግስቱን ለማሻሻል ሲሞክሩ በመቃወማቸው ለስደት ከተዳረጉ በኋላ መንግስት በሽብር እና ሙስና ወንጀል ወንጅሏቸው የአስራ አምስት ዓመታት እስር ፈርዶባቸው ነበር፡፡

በእንግሊዝ ሀገር ፍርድ ቤትም ክስ መስርቶባቸው በውጭ ያለ ሃብታቸው እንዲታድ አስደርጎ የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ግን በኋላ ላይ የሽብርተኝነት ክሱ የተጭበረበረና ከጀርባው ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ስለመሆኑ መረጃ ስላገኘ የሃብት እገዳውን ፍርድ ቀልብሶታል፡፡ ሆኖም ግን ባልተለመደ ሁኔታ ባለፈው መስከረም ወር ፕሬዝዳንቱ ራሳቸው በአካል ቀርበው በተከሳሹ ላይ እንዲመሰክሩ ወስኖባቸዋል፡፡
አለመረጋጋት ቢነሳ ግን ፈረንሳይም ሆነች ሌሎች በጅቡቲ ወታደራዊ ጦር ሰፈር ያላቸው ሃያላን መንግስታት ፕሬዝዳንቱን ደግፈው ጣልቃ ላይገቡ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ምዕራባዊያን በሚያካሄደው ሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በፖለቲካዊ ማሻሻያዎች አለመኖር እጅጉን እንደተሰላቹ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል ፕሬዝዳንቱ ቻይና በሀገራቸው ጦር ሰፈር እንድትገነባ በመፍቀድ ከአሜሪካ ጋር ከባድ የፖለቲካ ቁማር የጀመሩት፡፡ የኃያላን ሀገሮች ጦር ሰፈሮችን በሙሉ ማስተናገድ ግን ወደፊት በሀገሪቱ ደህንነት ላይ ስጋት ሊፈጥር እንደሚችል ቻታም ሃውስ በአንድ ጥናቱ ያስጠነቅቃል፡፡
የ67 ዕድሜ ባለፀጋው ፕሬዝዳንት ጌሌ ጤና እያሽቆለቆለ መሆኑን የሚጠቁሙ ዘገባዎች መውጣት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ያም ሆኖ እስካሁን ተተኪያቸው ማን እንደሚሆን እንኳ ፍንጭ አልሰጡም፡፡ ምናልባት ፕሬዝዳንቱ በ2016 ስልጣን የሚለቁ ከሆነ ግን እንደሚተኳቸው ተስፋ ከተጣለባቸው መካከል አንዱ የፋይናንስ ሚንስትሩ ኢልያስ ዳዋሌህ ናቸው፡፡
በጠቅላላው አሁን የጅቡቲ መፃዒ ዕጣ ፋንታ ፕሬዝዳንት ጌሌ እጅ ውስጥ ይገኛል፡፡ ሆኖም ፕሬዝዳንቱ መሰረታዊ የፖለቲካና የፖሊሲ መዋቅራዊ ማሻሻያዎች በማድረግ እውነተኛ ፖለቲካዊ ብዝሃነት ከማስፈን ይልቅ በ”ከፋፍለህ ግዛ” ፖሊሲ ተቃዋሚ ልሂቃንን በጥቅማጥቅም በመደለል ስልጣናቸውን በማስቀጠል ገፍተውበታል፡፡ ይህ አካሄዳቸውም ፖለቲካዊ አደጋን እንዳረገዘ ግልፅ እየሆነ ነው፡፡