Ethiopian born Sweden athlete Abeba Aregawi
Ethiopian born Sweden athlete Abeba Aregawi

አበባ አረጋዊ ስዊድንን ወክላ በሪዮ ኦሎምፒክ እንደማትሳተፍ የአገሪቱ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። አበባ ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚመጣው የመጨረሻ ውጤት ሜልዶኒየም የተባለውን አበረታች ዕፅ መውሰዷ ከተረጋገጠ፣ በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን (IAAF) የአራት ዓመት እገዳ ይጣልባታል። አበረታች ዕፅን አጥብቆ ይዋጋል የተባለው የስዊድን ፌዴሬሽን ፖሊሲ ደግሞ ይህንን ቅጣት እጥፍ አድርጎ ለስምንት ዓመት ሊቀጣት ይችላል ተብሏል። ዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን ሜልዶኒየምን ከተከለከሉ ዕፆች ዝርዝር ያስገባው ከሁለት ወራት በፊት መሆኑን ባለሞያዎች ገልጸዋል።

ሌሎች ዘጠኝ ኢትዮጵያውያን ሯጮች በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምርመራ ላይ መሆናቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ከአዲስ አበባ ዛሬ ዘግቧል። የሯጮቹ ስምም ሆነ የተጠረጠሩበት ዕፅ ግን አልተገለጸም።

አበባ ስለውጤቱ የሰማችው ልምምድ በማድረግ ላይ ባለችበት ባለፈው ቅዳሜ መሆኑን የስዊድን ጋዜጦች ዘግበዋል። ሆላንዳዊው ወኪሏ “አለቀሰች፣ በጣም ደነገጠች። ከዚያ በኋላ ማውራት አልቻልንም” ሲል አጋጣሚውን አስታውሷል። አበባ ምንም አይነት አበረታች ዕፅ አለመውሰዷን እየተናገረች ነው። ሜልዶኒየምንም ሆነ ሌላ ዕፅ ከማናኛውም ዶክተር አልተቀበልኩም ብላለች። ወኪሏም ቢሆን አበባ በዚህ አይነት ድርጊት የምትጠረጠር አይደለችም፣ አሁንም እናምናታለን ሲል ተናግሯል።

የምርመራው ውጤት ትክክለኝነት የሚያከራክ አልሆነም። ጥያቄው ሜልዶኒየም ወደ አበባ ደም የገባው እንዴት ነው የሚል ነው። ዕፁንስ ከየት አገኘችው? ወኪሏ ለአንድ የስዊድን ጋዜጣ በሰጠው ቃለ ምልልስ “አንድ ዩክሬናዊ ዶክተር ወደ ኢትዮጵያ ይመላለሳል ሲባል ሰምቻለሁ፣ ምናልባት እርሱ ዕፁን ወደዚያ አስገብቶት ሊሆን ይችላል” በማለት ተናግሯል፤ ስለአበባ ግን ግምቱን ከመሰንዘር ተቆጥቧል።

ስዊድናውያን ለሪዮ ተስፋቸው ለአበባ አረጋዊ ከእግድ ነጻ መሆን ማንኛውንም ሕጋዊ ነገር ከመፈጸም አይቦዝኑም። በ2012 (እ.አ.አ) የስዊድን ዜግነት ከተቀበለችና አገሪቱን መወከል ከጀመረች ወዲህ ስዊድንን በዓለም አቀፈ አትሌቲክስ ስንጠረዥ ውስጥ በማስገባቱዋ ዝናዋ የናኘ ነው። የዚያኑ ያህልም የሚዲያው ክትትልና ምርመራ አልቀረላትም ነበር። እነሆ የመጨረሻውን ምናልባትም የሩጫ ሕይወቷን ሊለውጥ የሚችለውን ውጤት በስዊድን መኖሪያዋ፣ በሆላድ የወኪሎቿ ቢሮ፣ አለዚያም በፍንክንኳ አዲስ አበባ፣ ምናልባትም ስልጠናዋን ሳታቋርጥ ትጠብቃለች።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሜልዶኒየም በስፋት የሚታወቀው ላቲቪያን በመሳሰሉ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ብቻ ነበር። መድኀኒቱ ለምእራቡ ዓለም እንግዳ በመሆኑ ከሚከለከሉት ዝርዝር ሳይገባ መቆየቱን ባለሞያዎች ያስረዳሉ።
መድኀኒቱ ጉልበት የሚሰጥ ሲሆን የልብ ህሙማን ከተጠቃሚዎቹ የሚጠቀሱ ናቸው።

ሜልዶኒየም በአሜሪካ የተከለከለ ነው። ሆኖም ስፖርተኞች በተለይ ከጉዳት ፈጥኖ ለማገገም ሲጠቀሙበት ቢቆዩም ከሁለት ወር በፊት ከተከለከሉት ምድብ ተፈርጁዋል። ባለፉት 2 ወራት ብቻ ከአምስት ያላነሱ ስፖርተኞች በዚሁ መድኀኒት የተነሳ ታግደዋል።

የአዲስ አበባ ጋዜጠኞች ነገሩን ለመመርመር ዩክሬናዊውን ዶክተር ማግኘት የመጀመሪያ ሥራቸው ሳይሆን አልቀረም።