ዋዜማ ራዲዮ፡ ሰሞኑን ንግድ ባንኮች ያለፈ አመት ሂሳባቸውን እያወራረዱ ትርፋቸውን ይፋ የሚያደርጉበት ነው።
ወጋገን ባንክም ባደረገው የባለ አክስዮኞች ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ባንኩ 1.05 ቢሊየን ብር ትርፍን ከታክስ በፊት ማግኘቱን ይፋ አድርጓል።ይህም ባለፈው አመት ካገኘው ትርፍ በ50 በመቶ ብልጫ ያለው እንደሆነ ገልጿል። በትርፍ ቢሊየን ብርን በመቀላቀል በግል ንግድ ባንኮች ታሪክ አዋሽና ዳሽን ባንክን ተከትሎ ሶስተኛ ሆኖ መግባቱም ተነግሮለታል።
ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ ግን ወጋገን ባንክ በየጊዜው አገኘሁት የሚለው ትርፍ ላይ ከፍተኛ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ መሆኑን ያሳያል።ምንጮቻችን እንደጠቆሙን ከሆነ ባንኩ ;የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ መከፈላቸው ለሚያጠራጥሩ ብድሮች ንግድ ባንኮች እንደ መጠባበቂያ ወይንም ባለሙያዎቹ provision ተብሎ የሚታወቀውን ገንዘብ እንደ ትርፍ አድርጎ አስቀምጧል።ለባለ አክስዮኖችም አከፋፍሏል።ይህም ባንኩ በ2009 አ.ም አተረፍኩት ባለው ገንዘብ ላይ መታየቱን በርከት ያሉ የባንኩ ምንጮቻችን ነግረውናል።
ወጋገን ባንክ በ2009 አ.ም ወይንም በአውሮፓውያኑ 2016/2017 ከታክስ በሁዋላ ወይንም የተጣራ ትርፍ 532 ሚሊየን ብር እንዳተረፈ ገልጾ ነበር።ነገር ግን ባንኩ በወቅቱ ያተረፈው ትርፍ በሪፖርቱ የተገለጸው እንዳልሆነ ማወቅ ችለናል።ባንኩ በዚህ አመት መመለሳቸው አጠራጣሪ ለሆኑ ብድሮች በብሄራዊ ባንክ ንግድ ባንኮች መጠባበቂያ እንዲያስቀምጡ የሚያዘውን ገንዘብ የተበላሸ ብድሩን መጠን ዝቅ በማድረግ ወደተጣራ ትርፍ ውስጥ ጨምሯል።
ብሄራዊ ባንክ እየተጠቀመበት ባለው ህግ መሰረት ንግድ ባንኮች ያበደሩት ገንዘብ ሳይመለስ 90 ቀን ሲያልፈው ብድሩ አደጋ ውስጥ ስለገባ የብድሩን 20 በመቶን ከትርፋቸው ላይ ቀንሰው መጠባበቂያ እንዲያስቀምጡ ያዛል።እያንዳንዱ ብድር ደግሞ ሳይመለስ 180 ቀን ሲያልፈው የእያንዳንዱን ብድር 50 በመቶ ; 360 ቀን ሲያልፈው ደግሞ የብድሩን ሙሉ ገንዘብ ከትርፉ ላይ ቀንሰው መጠባበቂያ እንዲያስቀምጡ ብሄራዊ ባንኩ ያዛል።ይህ የሆነበት ምክንያት ንግድ ባንኮች የሚያበድሩት ቀጥታ ከህዝብ በቁጠባ መልክ የሰበሰቡትን ገንዘብ በመሆኑ የህዝብ ገንዘብ አደጋ ውስጥ እንዳይገባና ከሚያበድሩት ገንዘብ መመለሱ የሚያጠራጥረው ብድር ከ5 በመቶ እንዳያልፍ የሚል ህግም ስላለው ነው።
ሆኖም ወጋገን ባንክ በማእከላዊ ባንኩ የተቀመጠውን ትእዛዝ ተግባራዊ ባለማድረግ 525 ሚሊየን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝቻለሁ ብሎ ትርፍ ክፍፍል አድርጓል።
ነገሩ የተከሰተው እንዲህ ነበር
ወጋገን ባንክ 2009 አ.ም ላይ ትርፉ የባንኩን ቦርድ አመራሮችን ጭምር ባስደነገጠ ሁኔታ ይቀንሳል።እንዳገኘነው መረጃ ከሆነም ትርፉ 200 ሚሊየን አይሞላም ነበር።ስለዚህ ምርጫው ያደረገው መመለሱ አጠራጣሪ ለሆነው የባንኩ ብድር መጠባበቂያ መቀመጥ ያለበት ገንዘብ ላይ የቁጥር መዛነፎችን ማድረግ ነው ። ይህም በእያንዳንዱ ተቀናናሽ በሚሆነው የተቀማጭ ገንዘብን ዝቅ በማድረግ ወደ ትርፍ እንዲገባ ለማድረግ ይረዳል በሚል ነው።ባንኩ ራሱ ይፋ ያደረገው የ2009 አ.ም ሪፖርቱ ሳይመለስ የቀረውና 90 ቀን ያለፈው ብድሩ 63.4 ሚሊየን ብር ; ሳይመለስ 180 ቀን ያለፈው ብድር 32 ሚሊየን ብር እንዲሁም በተመሳሳይ አመት ሳይመለስ 360 ቀን ያለፈው ገንዘብ 36 ሚሊየን ብር መሆኑን ጠቅሷል።ስለዚህም እንደ ቅደም ተከተላቸው ለነዚህ መከፈላቸው አጠራጣሪ ለሆኑ ብድሮች እንደየ ቅደም ተከተላቸው ከትርፉ ላይ 20,50 እና 100 ፐርሰንትን በመጠባበቂያነት ከትርፍ ላይ ይቀንሳል ማለት ነው።
ዋዜማ ራዲዮ እንዳረጋገጠችው ግን ባንኩ በወቅቱ መመለሱ አጠራጣሪ የሆነበት ብድር ከላይ በሶስት ተከፍሎ የተቀመጠው ብቻ አይደለም።ማለትም ሳይመለስ 90 ቀን ያለፈው በድር 63.4 ሚሊየን ሳይሆን ከዚህም በእጅጉ ይበልጥ ነበር።ሳይመለስ 180 ቀን ያለፈው ብድርም 32 ሚሊየን ብር ሳይሆን ብልጫ ያለው ብር ነው።እንዲሁም ሳይመለስ 360 ቀን ያለፈው ብድርም 36 ሚሊየን ብር ብቻ አልነበረም።ከእያንዳንዱ ያልተመለሰ ብድር ገንዘብ ላይ እንዲቀንስ አድርጓል። ወጋገን ባንክ ይህን ያደረገው ከ90 እስከ 360 ቀናት ባሉት ጊዜ ውስጥ ያልተመለሱት ብድሮች እውነተኛው ቁጥር ሪፖርት ከተደረገ የተጣራ ትርፍን ስለሚቀንስ ነው።ለምሳሌ ከ100 ሚሊየን ብር ላይ 20 በመቶ መቀነስና ከ32 ሚሊየን ላይ 20 በመቶን መቀነስ እንደሚለያየው ማለት ነው።ስለዚህም የባንኩ ባለሙያዎች የቁጥር ማስተካከያ እንዲያደርጉ የቦርድ አመራር በነበሩት አቶ ስብሀት ነጋ ተገደው እንደነበርም ማረጋገጥ ችለናል።በዚህ መልክ ባንኩ ያልተገባ ትርፍን በህገ ወጥ መንገድ አጋብሷል።
አንድ ያነጋገርናቸው የባንክ ባለሙያ እንዳሉንም ባንኩ የ2010 አ.ም አፈጻጸሙን አስመልክቶ ያወጣው ሪፓርቱ የሚያስጠረጥር ነው።የባንኩ የ2010 አ.ም ሪፖርት ላይ ሳይከፈል 90 ቀን ያለፈው ያበደረው ገንዘብ 1.6 ቢሊየን ብር ነው።ይህ ቁጥር 2009 አ.ም ላይ ከነበረው ሳይመለስ 90 ቀን ያለፈው ብድር ጋር ልዩነቱ ከፍተኛ ነው።በ2009 አም ሳይመለስ 90 ቀን ያለፈው ብድር 63.4 ሚሊየን ብር ብቻ ነበር።ያነጋገርናቸው ባለሙያ እንዳሉን ይህን ያህል የብር ልዩነት በአንድ አመት ውስጥ ማየት የተለመደ አይደለም። የባለፈው ወይንም የ2010 አ.ም ሪፖርት ላይ ችግር ስለመኖሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል ብለውናል።ወጋገን ባንክ ግን ይህን በማድረጉ ትርፉን ከፍ ለማድረግና የትርፍ ክፍፍሉን ከፍ ለማድረግ እንደረዳው ለማወቅ ተችሏል።ነገር ግን ባንኩ ለሚያበድረው ገንዘብ ከህዝብ የሰበሰበው ገንዘብ ላይ ሀላፊነት ያልተሞላት እንደነበር ማሳያ ነው።
ወጋገን ባንክ ትርፉን ከፍ ለማድረግ ካልተፈቀደ የውጭ ምንዛሬ ትርፍ እንዳገኘ አድርጎም ሪፖርት ማቅረቡም ትርፉን በ2009 አ.ም ከ500 ሚሊየን ለማስበለጥ እንዳገዘው ተረድተናል።
ሌሎች ጥቂት ባንኮች ትርፋቸውን ከፍ ለማድረግ ተመሳሳይ ያልተገባ ድርጊትም ውስጥ ሲሳተፉ ይሰማል።ሆኖም ብሄራዊ ባንክ ህዝብ በቆጠበው ገንዘብ ላይ ያልተገባ ትርፍ የማጋበስ ስራ ሲሰራ ቅጣት ሲያስተላልፍ ተሰምቶ አይታወቅም። [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/R-ZefDYid6A