ዋዜማ ራዲዮ- የባንኮች የወለድ ምጣኔ በገበያ ፍላጎትና አቅርቦት እንዲወሰን መንግስት በአስር አመት የልማት እቅዱ ላይ መወሰኑን ዋዜማ ራድዮ የተመለከተችው የእቅዱ ሰነድ አመለከተ። ከዚህኛው አመት ማለትም ከ2013 አ.ም እስከ 2022 አ.ም እንዲተገበር ታስቦ የተዘጋጀውና “የልማት እቅድ : ፍኖተ ብልጽግና” የሚል ስያሜ ያለው ሰነዱ : የገንዘብ ፖሊሲና የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ልማት እቅድ በሚለው አርስት ስር የፋይናንስ ኢንዱስትሪው የታቀደውን መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያግዝ ለማድረግ የወለድ ምጣኔ ተመን በገበያ ፍላጎትና አቅርቦት እንዲመራ ይደረጋል ብሏል።

በዚህ የአስር ዓመት የልማት ዕቅድ ላይ ከተመረጡ ተቋማት፣ የሕዝብ ተወካዮች፣ አለም ዓቀፍ ለጋሾችና አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ጋር ውይይት እየተደረገ ነው። ይህ ዕቅድ የሚተገበር ከሆነም ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብትና የፋይናንስ ዘርፍ አዲስ አቅጣጫ ነው።

የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ለማረጋጋጥ እና የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለማሳደግ በገበያ ፍላጎትና አቅርቦት የሚመራ የውጭ ምንዛሪ ተመን እንዲኖር ይደረጋል። የፋይናንስ ኢንዱስትሪው የታቀደውን መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያግዝ ለማድረግ የወለድ መጣኔ ተመን በገበያ ፍላጎትና አቅርቦት እንዲመራ የማድረግ እና ዲጂታል የፋይናንስ ሥርዓት የሚዘረጋ ይሆናል። ወቅታዊ ሁኔታን ያገናዘበ የካፒታል አካዉንት ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የተሳለጠ የካፒታል ገበያ በመፍጠር አማራጭ የልማት ፋይናንስ ምንጮች ለማስፋት የሚሰራ ይሆናል። ይላል ስነዱ በገፅ 100 ላይ

ለዋዜማ ራዲዮ አስተያየታቸው የሰጡ የምጣኔ ሐብት ባለሙያዎች መንግስት ለረጅም ዓመታት የዘለቀውን እና አሁን ደግሞ በእጅጉ የናረውን የዋጋ ግሽበት ባልተቆጣጠረበት ሁኔታ የወለድ ምጣኔን በገበያ እንዲወሰን ማድረግ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ድርብርብ ፈተና የሚያስከትል ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ንግድ ባንኮች ለገንዘብ አስቀማጭ ደንበኞቻቸው የሚከፍሉት ወለድ ከዜሮ በታች (Negative interest rate) ነው። ይህም የሆነው የወለድ ምጣኔያቸው ከሀገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በእጅጉ ያነሰ በመሆኑ ነው።

ከዜሮ በታች ወለድ ?

አንድ መቶ ብር የቆጠበ የባንክ ደንበኛ የንግድ ባንኮች የሚያስቡለት ወለድ ብሄራዊ ባንክ ባስቀመጠው መሰረት ሰባት በመቶ ነው። ይህም ገንዙን 107 ብር ያደርግለት ይሆናል። አሁን 20 በመቶ አካባቢ ባለው የዋጋ ግሽበት ሳቢያ ግን የአስቀማጩ ገንዘብ ቀድሞ የ20 ብርን ዋጋ አጥቷል። መቶ ብር ባንክ ያስቀመጠ ደንበኛ የዋጋ ግሽበት ሀያ ብር ተቀንሶ : ሰባት ብር ደግሞ ወለድ ተጨምሮለት የ87 ብር ዋጋ ያለው ገንዘብ ነው ባንክ ያለው ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ገንዘብን ባንኮች ውስጥ ማስቀመጥን አዋጭ ያላደረገው የወለድ ምጣኔ ከዋጋ ግሽበት ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ነው። መንግስት በተደጋጋሚ በዚህ ውሳኔ ሲተች የቆየ ቢሆንም ከዋጋ ግሽበት ጋር የሚመጣጠን የወለድ ምጣኔን መተመን ኢንቨስትመንትን ይጎዳል የሚል ማስተባበያን ሲሰጥ ቆይቷል።

የዋጋ ግሽበትን የሚመጣጠን ዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ ቢተመን ባንኮች ለማበደር የሚጠይቁት ወለድ ትርፋቸውንም አስበው ስለሚጨምሩ ተበድሮ ስራ መስራት የበለጠ ከባድ ይሆናል ተብሎ ይታመናል። አሁን ያለውን 20 በመቶ አካባቢ የዋጋ ግሽበት የሚመጣጠን የወለድ ምጣኔ ቢደረግ የማበደርያ ወለድ ደግሞ 25 በመቶና ከዛ በላይ እንዲሆን ስለሚያደርግ ሌላ የዋጋ ግሽበት ፈጣሪ ይሆናል። ይህን የወለድና የዋጋ ግሽበት ምጣኔ ችግር ያባባሰው ፣ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት በሚል አስቀማጮች እየተጎዱ የወለድ ምጣኔ ከዋጋ ግሽበት በታች ሆኖ ቆይቶም በዚህ መንገድ የወጣ ብድር ምርታማነትን ፈጥሮ የሚፈለገውን እድገት ማምጣት አለመቻሉ ነው። የዋጋ ግሽበት በዚህ አስጊ ደረጃ ላይ ሆኖ መንግስት ቀጣዮቹን አመታት በሚመራበት የኢኮኖሚ እቅድ ውስጥ የወለድ ተመንን በገበያ እንዲመራ አደርጋለሁ ማለቱ አደናጋሪ ሆኗል።

ጥብቅ በሆነ የገንዘብ ፖሊሲ የዋጋ ግሽበትን ተቆጣጥሮ ወደ አንድ አሀዝ ስለማውረድ እቅዱ የሚያነሳቸው ጉዳዮች አሉ። ነገር ግን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲን መከተል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላም በተደጋጋሚ ሲነሳ የነበረ ነገር ግን በተግባር ያልታየ ፣ እንደውም ግሽበት ፈጣሪ የገንዘብ እንቅስቃሴ አሁን ድረስ እየታየ ነው ።

በገበያ የሚወሰን የወለድ ምጣኔ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት የኢኮኖሚ ችግር አደጋን የሚያመጣው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክን የመወሰን ስልጣን ስለሚገድበውም ነው።

ይህን አይነት የወለድ ተመንን የሚከተሉ ያደጉ ሀገራት ማእከላዊ ባንኮች እጅግ የተመረጡ ፖሊሲዎችን ለማስተግበር ሲያስቡ ብቻ ነው በወለድ ተመን ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡት። ይህን አይነት የወለድ ተመን እየተከተሉ ችግር ሳይገጥማቸው የቆዩትም የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ስለቻሉ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የወለድ ተመኑን ለገበያ ከመተው ይልቅ ብሄራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን እያየ የወለድ ተመንን ያስተካክል ቢባል እንኳ የዋጋ ግሽበት በእጅጉ እየጨመረ ስለሆነ ብዙም አዋጭ እንዳልሆነ ምሁራን ይገልጻሉ። ተመኑ እንዲሁ ለገበያ ቢተውም ለንግድና ኢንቨስትመንት የሚሰጡ ብድሮችን ውድ በማድረግ ኢኮኖሚውን የባሰ ችግር ውስጥ ይጨምረዋል ።

መንግስት የወለድ ምጣኔን ለገበያ የመተዉን ጉዳይ አሁን ላይ ለመተግበር ያሰበው ምናልባት የካፒታል ገበያን ለማቋቋም ከጫፍ ላይ ስለደረሰ ይሆናል ብለውናል ሌላ የኢኮኖሚክ ምሁር። የካፒታል ገበያ ላይ በሰነድ ገንዘባቸውን የሚያበድሩ ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች መንግስት ገደብ በሚያወጣለት የወለድ ተመን መመራትን ሳይሆን ገንዘቦቻቸውን በተሻለ ወለድ በሰነድ የሚበደራቸውን ተበዳሪ ነው የሚፈልጉት ; ለዚህም ለካፒታል ገበያ ሲልባ የወለድ ምጣኔ ጉዳይ ለገበያ እንዲተው ተፈልጎ ይሆናል ሲሉም ሀሳባቸውን ሰጥተውናል። [ዋዜማ ራዲዮ]