Book 3ዋዜማ ራዲዮ- ባለፈው ወር The Horn of Africa: State Formation and Decay የሚል አዲስ መጽሐፍ የጻፉትና በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክ ዙርያ ተሰሚነት ያለው ትንታኔ በማቅረብ የሚታወቁት ክርስቶፈር ክላሀም ከታተመ ቆየት ያለ አንድ ሥራቸው በዚህ ሳምንት ለአማርኛ አንባቢ ተተርጉሞ ቀርቧል፡፡

እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1988 ዓ. ም ለሕትመት የበቃውና በ60ዎቹ አጋማሽ የተካሄደውን አብዮትና ያስከተለውን ዉጤት በጥልቀት የሚተነትነው ይህ የክሪስቶፎር ክላኸም ቆየት ያለ መጽሐፍ Transformation and Continuity in Revolutionary Ethiopia የሚል ርዕስ ነበረው፡፡ ወደ አማርኛ የመለሱት ተርጓሚው አቶ ሙሉቀን ታሪኩ ‹‹መንግሥቱ ኃይለማርያም እና አብዮቱ›› የሚል ርዕስ ሰጥተውታል፡፡

ክርስቶፎር ክለሃም ይህ መጽሐፋቸው የተጸነሰው በደርግ ጊዜ ስምንተኛው ዓለማቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት ኮንፈረንስ ለመታደም አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት እንደነበር በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ጠቅሰዋል፡፡ መረጃ የመሰብሰብ የመስክ ሥራቸውን በስፋት ያከናወኑት ደግሞ በ1970ዎቹ መጨረሻ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጋባዥ ፕሮፌሰር ኾነው ለሰባት ወራት በቆዩበት ወቅት ነበር፡፡

ደራሲው በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ባንጸባረቁት ተጨማሪ አስተያየት ኢትዮጵያ ዉስጥ በአመዛኙ ጉዳት የለሽ መረጃዎችን የመደበቅና በምስጢር የመያዝ አባዜ እንደሚስተዋል፣ የፈጠራ ታሪኮችንና አፈ ታሪኮችን እውነት አድርጎ የመቀበል ባህል በስፋት እንደሚታይ ይህም በምርምር ሥራቸው ላይ ተግዳሮት ኾኖ እንደቆየ ጠቅሰዋል፡፡

በደርጉ ሊቀመንበር የአስተዳደር ዘይቤ ላይ ባሰፈሩት ጥቅል አስተያየት ደግሞ ደራሲው የሚከተለውን ብለዋል፤

‹‹የመንግሥቱ ኃይለማርያም የአመራር ጥበብ ብዙዎች እንደሚገምቱት የካስትሮ ወይም የኦል ሱንግ ግልባጭ አልነበረም፤ መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ፍጹማዊነት ወርሰዋል፡፡ የንጉሡን ቤተ-መንግሥት ከነሙሉ አገልጋዮቻቸው የወረሱት መንግሥቱ እንደ ቀ.ኃ.ሥ ሁሉ እርሳቸውም ከተራው ሕዝብ በመነጠል በርቀት እንዲከበሩና እንዲፈሩ ሆነዋል›› ሲሉ የኮሎኔሉን የአስተዳደር ዘይቤ ተችተዋል፡፡

የዋቢ ጽሑፎችን መዘርዝር ጨምሮ 350 ገጾች ያሉት ይህ መጽሐፍ በአስር ምዕራፎች ነው የተዋቀረው፡፡ በይበልጥ ከአብዮቱ አንስቶ እስከ ኢህድሪ ምሥረታ ያሉ አንኳር ጉዳዮች ተዳሰውበታል፡፡ የብሔር ጥያቄዎች ማቆጥቆጥ፣ አብዮቱና የምዕራባዊያን ምላሽ፣ የግብርና ምርታማነት ቀውስ፣ የትምህርት እድገት፣ የከተሞች ቁጥጥርና አገዛዝ በደርግ ምን ይመስል እንደነበር መጽሐፉ ይተነትናል፡፡

በመጽሐፉ መደምደሚያ ደርግ ሁሉንም ነገር ብቻውን ለመፈጸም ያደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል፣ አንድነትና ልማትን ለማሳካት የደከመው ድካም ሁሉ ያሰበውን አንድነትም ኾነ ልማት እንዳላመጣለት፣ ይልቁንም ተቃውሞዎች እንዲበረቱበት እንዳደረገው ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

‹‹የአብዮቱ መንግሥት ዋና ችግር በመዳፉ ከሚጨብጠው እፍኝ ስኬት ይልቅ በርቀት ለመያዝ የሚመኘው ግብ ሰፊና ከአቅሙ በላይ መሆን›› እንደነበር አውስተዋል፡፡ ሥርዓቱ የግብርና ልማትና ማኅበራዊ ሽግግርን ለማምጣት ባለው አቅም ሁሉ ቢጥርም የረሀብን አደጋ እንኳ ማስቀረት እንዳልቻለ ጠቁመዋል፡፡ ከአርሶ አደሩ የሚገኘው ምርትና የሚሰበሰበው ግብአት ለመንግሥት ኢንዱስትሪዎች ድጋፍና ለወታደራዊ ወጪ መዋሉ የሥርዓቱ ዉድቀት መነሻ እንደሆነም ተንትነዋል፡፡ የኢትዮጵያን ብሔራዊ አንድነት ለመጠበቅ የተደረገው የቁጥጥርና የማማከል ሥራ ወታደሩን እረፍት የነሳው በመሆኑና ከሰሜን ወደ ደቡብ እየሰፋ የመጣ ተቃውሞ በመፈጠሩ ሳይሳካ እንደቀረም አብራርተዋል፣ በመጽሐፋቸው፡፡

በተጨማሪም ንጉሡ ‹‹የኤርትራን ችግር ለመፍታት የወሰዱት የዉህደት እርምጃ የመንግሥታቸውን ፖለቲካዊ ድክመት ያሳየ መሆኑ በአብዮቱ ዉጤት ታይቷል›› የሚሉት ፕሮፌሰር ክለኻም ደርግ ሁሉንም ችግሮች በተማከለ መንግሥታዊ ቅርጽ ምላሽ ለመስጠት መሞከሩ እንዲበተን አድርጎታል ይላሉ፡፡

ክርስቶፎር ክለኻም ይህን መጽሐፋቸውን መታሰቢያ ያደረጉት በግንቦት 1980 ድንገት በሞት ለተለያቸው ጥበቡ ደርቤ ለሚባል የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የ3ኛ ዓመት የስታትስቲክስ ትምህርት ክፍል ተማሪ ነው፡፡