OMNዋዜማ ራዲዮ- ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ OMN በተፈጠረው አዲስ የፖለቲካ ድባብ ተነሳስቶ በሀገር ቤት ቅርንጫፍ ከፍቶ ለመንቀሳቀስ ማቀዱን አስታወቀ።
በዩናይትድ ስቴትስ ሜኒሶታ ግዛት ለትርፍ ባልተቋቋመ ድርጅትነት ተመዝግቦ የሚገኘው ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ(OMN) በሀገር ቤት ለመንቀሳቀስ የሚያስችለውን ዝርዝር ለመወሰን ሁለት የድርጅቱ አመራር አባላትን ወደ አዲስ አበባ መላኩን አስታውቋል።
ከተመሰረተ አምስት አመት ያስቆጠረው OMN እና የድርጅቱ መሪ አቶ ጃዋር መሀመድ ላይ ከዚህ ቀደም በአሸባሪነት ወንጀል ክስ ተመስርቶ የነበረ ሲሆን በቅርቡ በአዲሱ የመንግስት አመራር ክሱ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን (ESAT)) ላይ የቀረበው ክስም ተነስቷል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በስደት ያሉ መገናኛ ብዙሀን ወደ ሀገር ቤት ገብተው እንዲሰሩ ሁኔታዎችን እንደሚመቻቹ ከአንድ ወር በፊት ተናግረው ነበር።
ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ OMN የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱ አበረታች ነው ቢልም በሀገሪቱ ነፃ መገናኛ ብዙሀን እንዲንቀሳቀሱ የሚያስችል ተጨማሪ እርምጃ ያስፈልጋል፣ አፋኝ የሆነው የፕሬስ ህግ መሻሻል አለበት ብሏል።