FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በምስራቅ እና ምዕራብ ወለጋ አካባቢ ኦነግ ሸኔ በስፋት በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የፈረሰውን መንግስታዊ መወቃር ለመመለስ እና ቡድኑን ከህዝብ ይነጥልልኛል ያለውን አዲስ የዘመቻ እንቅስቃሰሴ መጀመሩን ዋዜማ ከክልሉ መንግስት ምንጮቿ ሰምታለች ።

በአካባቢው የፈረሰውን መንግስታዊ መዋቅርን ለመመለስም ሆነ በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ የቡድኑን ደጋፊዎች ለማጥራት ያግዛሉ የተባሉ ቁጥራቸው ከ250 በላይ የሆኑ አመራሮች ከክልሉ መንግስት አቅጣጫ እና ስልጠና ወስደው ወደ ስፍራው ማምራታቸው ዋዜማ ከምንጮቿ አረጋግጣለች።

በክልሉ መንግስት ተመልምለው እና ስልጠና ወስደው ወደ ወለጋ ዞኖች ያቀኑት አመራሮች የአካበቢውን ህዝብ የማወያየት እና በኦነግ ሸኔ የተጠለፉ የወረዳ እና የዞን መዋቅሮችን መልሶ የማጥራት እና የማደራጀት ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ባለፈው ማክሰኞ በምክር ቤት በነበራቸው የስድስት ወራት የአፈፃፀም ሪፖርት ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ‘’ሸኔ ከህዝቡ ጋር ተቀላቅሎ እና በህዝብ ተከልሎ ጥፋት እየፈጸመ በመሆኑ ቡድኑን ለይቶ እርምጃ ለመውሰድ አዳጋች እንዳደረገው’’ መናገራቸው አይዘነጋም።

የክልሉ መንግስት አሁን በልዩ ትኩረት ታጣቂ ቡድኑን ከህዝቡ ለመነጠል ያስችለኛል ያለውን አዲስ ስልት በመከተል እስከ ቀበሌ የዘለቀ ህዝብን የማወያየት ሰፊ ስራ ለማከናወን መታሰቡንም ዋዜማ ወደ ስፍራው ከሚያቀኑ ሃላፊዎች ሰምታለች። 

ኦነግ ሸኔ በተለይ በምእራብ እና ምስራቅ ወለጋ በንፁሃን ላይ ለሚደርሱ ተደጋጋሚ ግድያዎች በመንግስት ሲከሰስ ቆይቷል። በቅርቡ እንኳን በወንጪ አካባቢ በገበታ ለሀገር መርሀ ግብር የሚከናወነውን የወንጪ ፕሮጀክት ተሽከርካሪዎች ማቃጠሉን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በምክር ቤት መናገራቸው የሚታወስ ነው [ዋዜማ ራዲዮ]