ዋዜማ ራዲዮ- በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች የተደረገው ቤት የመቀመጥ አድማ ከታቀደው አስቀድሞ ግቡን ስለመታ በሶስት ቀናት ማብቃቱን የአድማው አስተባባሪዎች ተናግረዋል።
ሌሎች “አድማው አልተሳካም”  ከተቀመጡለት ግቦች አንዱን እንኳ ሳያሳካ እንዴት ስኬታማ ሊባል ይችላል? ሲሉ ይሞግታሉ። ይህ የዋዜማ ዘገባ አድማው በይፋ ከተነገረው ውጪ ተልዕኮ ነበረው ፣በአደባባይ ከተገለፀው ባሻገር ይፋ ያልተነገሩ የቅርብና የሩቅ ጊዜ ግብ አለው ይለናል። የኦሮሞ አክቲቪስቶች ከመጋረጃ ጀርባ ለኦሮሞ ህዝብ የራስን ዕድል በራስ መወሰን እየሰራን ነው እያሉ ነው። ሙሉ መረጃውን በድምፅ ይዝለቁት አልያም የቻላቸው ታደሰን ዘገባ ከግርጌ ያንብቡት

https://youtu.be/aADdX9XSwrs

 

መንግስት ለአምስት ቀናት ተጠርቶ በነበረው የኦሮሚያው ቤት ውስጥ የመዋልና ግብይት ማቆም አድማ ላይ አንዳንድ ርምጃዎችን ለመውሰድ መዘጋጀቱ መዘገቡን ተከትሎ አድማው ባለፈው ዐርብ በሦስተኛ ቀኑ ተቋርጧል፡፡
የአድማው አስተባባሪዎችም አድማው የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ለማስከበር መጥቀሙን ገልጸዋል፡፡ ያሁኑም ሆነ ካሁን በፊት የተጠሩት አድማዎች የኦሮሞ ብሄር መብት ተሟጋቾችና ፖለቲከኞች ለረዥም ጊዜ ሲያነሱ ሲጥሉት የኖሩትን የብሄሩን የራስን እድል በራስ የመወሰን ጥያቄ ምን ያህል ወደፊት መግፋት አስችለዋል? የሚለው ጉዳይ ግን መመርመር ያለበት ነው፡፡ የሰሞኑ አድማ በዚህ ረገድ ያሳካው ውጤት የለም፡፡ የአድማው አስተባባሪዎችም ቀደም ብሎ ያልተያዘውን የራስን እድል በራስ መወሰንን የአድማው አንድ ግብ እንደነበር መጥቀሳቸው ያልተጠበቀ ነው፡፡ ምናልባትም አጀንዳው በማንኛውም ህዝባዊ ጥያቄ ውስጥ ተደብቆ እንዲቀመጥ ይደረግና አስፈላጊ ሲሆን እየተመዘዘ ያለ አጀንዳ መሆኑን መታዘብ ይቻላል፡፡ የአድማው አስተባባሪዎች መግለጫ የሚጠቁመው አድማዎች በዋናነት ከመሠረታዊ ዲሞክራሲያዊ ማሻሻያዎች ይልቅ በዚሁ አጀንዳ ዙሪያ እንዲያጠነጥኑ እንደተፈለገ ነው፡፡
በርግጥ የአምናው የኦሮሚያው ህዝባዊ አመጽ ኦሮሚያ ክልል በአዲሳባ ከተማ ላይ ያለውን ልዩ ህገ መንግስታዊ ጥቅም የሚደነግግ አዋጅ እንዲወጣና በክልሉና በአዲሳባ መካከል ያለው ድንበር እንዲካለል ገፊ ምክንያት መሆን ችሏል፡፡ የሰሞኑ አድማም ይኸው የመብት ትግል መቋጫ ሳያገኝ ወደፊትም አድማዎች እንደማይቆሙ ለማስገንዘብ መሆኑ አስተባባሪዎች ጠቁመዋል፡፡ የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት የተራዘመ ትግል የሚጠይቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ይህንኑ መብት በሰላማዊ እና በሰሞኑ ዐይነት አድማ ከእስካሁኑ በላይ ወደፊት መግፋት የሚቻል መሆኑ ያጠራጥራል፡፡
የባለፈው ሳምንት አድማ የተጠራው አዲሱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለማ መገርሳ “በሃብት ራስን መቻል” የሚል አጀንዳ ቀርጸው የኦሮሞ ወጣቶችን ቀልብ ለመሳብ ተከታታይ ጥረት ማድረጉን በተያያዙበት ወቅት ነበር፡፡ ይህ ነው የሚባል ማሳመኛ ባይቀርብም አንዳንድ ወገኖች የኦህዴድ ካድሬዎች አድማውን በማነሳሳት እጃቸው እንዳለበት ይገምታሉ፡፡ አድማው በውጭ ሀገራት ባሉ ወይም በሀገር ውስጥ ባሉ ጸረ-ኦሕዴድ ወገኖች ብቻ የተመራ ከሆነ ግን ኦሕዴድ ራሱ በሚመራው ክልል ለሚደረጉት ህዝባዊ ንቅናቄዎች ባይተዋር ሆኖ መቀጠሉን እና በመከላከል ስራ ላይ ብቻ መጠመዱን መታዘብ ይቻላል፡፡
መንግስት ለዘጠኝ ወራት በመላ ሀገሪቷ ጥሎት የቆየውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲያነሳ በመላ ሀገሪቱ የህዝብንና መንግስትን የዕለትተለት እንቅስቃሴ የሚያውኩ ድርጊቶችን ማክሸፍ እንደሚችል ተማመኖ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም አዋጁ ከተነሳ ገና ወር ሳይሞላው የአማራ እና ኦሮሚያ አድማዎች በተከታታይ መካሄድ ችለዋል፡፡ አድማዎቹ የመንግስት ጸጥታ ሃይሎችም ሆኑ የመንግስት ፖለቲካ መዋቅር ድንገተኛ ህዝባዊ አድማዎችን የማክሸፍ ብቁ ዝግጁነት እንደሌላቸው አጋልጠዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል በድንገተኛው አድማ የተደናገጠው መንግስት ምንም ዐይነት ርምጃ ሳይወስድ የኦሮሚያው አድማ በሦስተኛ ቀኑ መቋጨት የቻለው፡፡
በኦሮሚያ ክልል የሚጠራ አድማ በሌሎች ክልሎች ከሚካሄዱ አድማዎች በተለየ ውጤታማ የመሆን ዕድሉ ከፍ ያለ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ባንድ በኩል ክልሉ ከበርካታ የሀገሪቱ ክልሎች ጋር ስለሚጎራበት በክልሉ የሚካሄድ ማንኛውም አድማ አዲሳባን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች ላይ ቀጥተኛ እና ፈጣን ተጽዕኖ ማሳረፍ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደሞ ክልሉ ግዙፍ ቆዳ ስፋት ያለው መሆኑ፣ የሀገሪቱ በርካታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱበት በመሆኑ እና ለዋና ከተማዋ መሠረታዊ ጥሬ እቃዎች እና የምግብ እህል አቅራቢ መሆኑ የሀገሪቱን ጸጥታ የማወክ እንዲሁም መሠረታዊ የኢኮኖሚ አውታሮችን የማሽመድመድ አቅሙ ላቅ ይላል፡፡ በተለይ የተራዘሙ አድማዎች ቢደረጉ ደሞ ሀገሪቱን ከጅቡቲ ወደብ ጋር የሚያገናኘው የባቡር ሃዲድ ሳይቀር ክልሉን አቋርጦ ስለሚያልፍ ለጊዜውም ቢሆን የሀገሪቱን ነዳጅ አቅርቦት እና አጠቃላይ የውጭ ንግድ ፍሰቱን በማስተጓጎል በመንግስት ላይ ጉዳት የማድረስ አቅም አያጣም፡፡
ምንም እንኳ የአድማው ጅኦግራፊያዊ ወሰን ክልላዊ ቢሆንም ባሳረፈው አለታዊ ተጽዕኖ ግን ከሞላ ጎደል ክልል ተሻጋሪ መሆኑ አልቀረም፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ኦሮሚያ ክልል ከብዙ የሀገሪቱ ክልሎች ጋር የሚጎራበት በመሆኑ አድማው የመጓጓዣ እና ንግድ ትስስሮች ላይ እክል መፍጠር መቻሉ ነው፡፡ አድማው የመንግስቱ መቀመጫ እና የሀገሪቱ ዋና የኢኮኖሚ አውታር የሆነችውን አዲሳባን ከቀሪዎቹ የሀገሪቱ ክፍሎች መነጠል እንደሚቻል ታይቶበታል፡፡ አድማው ከሞላ ጎደል ይህንን ስኬት ማስመዝገብ መቻሉን ዋዜማን ጨምሮ በውጭ ሀገራት ያሉ መገናኛ ብዙሃን አረጋግጠዋል፡፡ በክልሉ የተወሰኑ ዞኖች እና ወረዳዎች የአድማው ጥሪ ተቀባይነት አግኝቶ ንግድ ቤቶች ተዘግተው መሰንበታቸውን ራሱ ኦሕዴድም አምኗል፡፡
በሌላ በኩል ግን አድማው ብሄር-ተኮር በመሆኑና ባብዛኛው የኦሮሞ ብሔር ጥቅሞችን ለማስጠበቅ ያለመ መሆኑ በጥርጣሬ እንዲታይ እንዳደረገው የሚጠቁሙ አስተያየቶች በተለይ ከአንድነት አቀንቃኙ ወገን ይደመጣሉ፡፡ ይህም አካሄድ በሀገሪቱ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገውን ሁለንተናዊ ትግል እንደሚጎዳው ያስጠነቅቃሉ፡፡ የአድማው አስተባባሪ አካል በግልጽ አለመታወቁ ደሞ በዚሁ ዙሪያ ለመተጋገዝና በጋራ ለመስራት እንቅፋት መሆኑ አልቀረም፡፡ አድማዎቹ ሀገር በቀል አመራር ያላቸው ወይንም በውጭ ሀገራት ባሉ የመብት ተሟጋቾች የሚመሩ ስለመሆናቸው በርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ በርግጥ በማህበራዊ ሜዲያ ከሚታየው እንቅስቃሴ መታዘብ የሚቻለው አድማው በውጭ ሀገር ባሉ የብሄሩ መብት ተሟጋቾች የሚመራ መሆኑን ነው፡፡
በአድማው ሊሳኩ የታሰቡት አጀንዳዎች ማለትም የፖለቲካ እና ህሊና እስረኞች እንዲፈቱ፣ በግብር ከፋዮች ላይ ያላግባብ የተጣለው ከፍተኛ ግብር ክፍያ እንዲሰረዝ፣ የክልሉ አስተዳደር ወሰኖች አለመታወቅ እና በጠቅላላው ሰብዓዊ መብት እንዲከበር የሚሉ ጥያቄዎች ሳይመለሱ አድማው ሁለት ቀናት ቀድሞ መቆሙ ድክመት መሆኑን የሚከራከሩ ወገኖችም አሉ፡፡
የአድማው አስተባባሪዎች ግን ህዝቡ ለአድማ ያለውን ተባባሪነት ለመለካት፣ የመንግስትን ቅቡልነት እጦት ለማጋለጥ፣ ስርዓቱን በምጣኔ ሃብት ለማዳከም እና የኦሮሞ ብሄርተኝነት መጠንከሩን ለማሳየት የታለመ መሆኑን በመጥቀስ ስኬታማነቱን አጉልተውታል፡፡ በርግጥም አድማው የተወሰኑ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን መካድ አይቻልም፡፡ ባንድ በኩል ምናልባት መንግስት ሊወስዳቸው ያሰባቸውን ዋና ዋና መንገዶችንና ንግድ መደብሮችን በሃይል ማስከፈት የመሳሰሉ የሃይል ርምጃዎች ቀድሞ ማስቀረት ችሏል፡፡ በዚህም የሰው ህይወት እንዳይጠፋና ንብረት እንዳይወድም ማድረግ ችሏል፡፡ በሌላ በኩል አድማው በህዝቡ በተለይም በንግዱ ማህበረሰብ ላይ ከባድ ተጽዕኖ ከማሳደሩ በፊት መጠናቀቁ ህዝቡ ወደፊት ተመሳሳይ የአድማ ጥሪዎችን በአሉታዊ ጎናቸው እንዳይመለከታቸው ማስቻሉ አይቀርም፡፡
ባጠቃላይ የአድማው አስተባባሪዎች ወደፊትም ስትራቴጂያቸውን እየቀያየሩ ተመሳሳይ አድማዎችን ቢጠሩ ህዝቡ ተሳታፊ እንደሚሆን እና መንግስትም በቀላሉ አድማዎቹን ሊያከሽፍ የሚችልበት እድል አናሳ መሆኑን ለማሳየት ተጠቅመውበታል፡፡
የድንገተኛው የአድማ ጥሪ መጠራቱ በመንግስት ላይ ተጽዕኖ ከማሳደር ባለፈ የኦሮሞ ብሄር መብት ተሟጋቾችና ፖለቲከኞች የኦሮሞን ህዝብ በተለይም የወጣቶችን ቀልብ ለመሳብ የሚያደርጉት ውስጣዊ ሽኩቻ ነጸብራቅ ሊሆንም ይችላል፡፡ የኦሮሞ ብሄር በጅኦግራፊ፣ ታሪክ፣ ስነ ልቦና እና ሐይማኖት ክፍፍሎች የሚታዩበት በመሆኑ በመብት ተሟጋች ግለሰቦች ወይም ፖለቲካ ቡድኖች መካከል ሽኩቻ መኖራቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ በርግጥ አንዳንድ ምልክቶችም አሉ፡፡ ባሁኑ የአድማ ጥሪ ግን ድምጹ ጎልቶ የሚሰማው ራሱን የኦሮሞ ህዝብ ትግል አፈ ቀላጤ አድርጎ የሚያየው እና የኦሮሞ ሜዲያ ኔትወርክ ቴሌቪዥን ስራ አስኪያጅ የሆነው ጃዋር መሐመድ የበላይነቱን የያዘ ይመስላል፡፡
እንዲህ ያሉ የተናጥልና የአጭር ጊዜ አድማዎች በኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት መሠረታዊ አቋም እና ፖሊሲ ላይ የሚያመጡት ለውጥ መኖሩ ግን አጠራጣሪ ነው፡፡ መንግስት የአምናውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ መሠረታዊ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ለመውሰድ ቃል ቢገባም አንድም ትርጉም ያለው ማሻሻያ ሳይወስድ ዐመት ሊደፍን ተቃርቧል፡፡ እናም በአምናው ደም አፋሳሽ አመጽ ለተነሱት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ መስጠት ሳይችል ወይም ሳይፈልግ ለሰሞኑ የሦስት ቀን አድማ አመርቂ ምላሽ ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
ድሮ ለህዝባዊ አድማዎች ድንጉጥ የነበረው ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት አሁን አሁን ድንገተኛ ህዝባዊ አድማዎችን እየተላመዳቸው ይመስላል፡፡ በተለይ ድሃው ህዝብ በተለይም የንግዱ ማህበረሰብ የተራዘሙ አድማዎችን መሸከም የማይችል መሆኑን እንደድክመት ሳይወስደው አልቀረም፡፡
አሁን ባለው አያያዙ ኢሕአዴግ ማህበራዊ መሰረት ከሌላቸው ጥገኛ ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የታይታ ድርድር መያዙን እንደ ስኬት ቆጥሮታል፡፡ እናም ለዲሞክራሲ እና ፍትሃዊ ሃብት ክፍፍል የሚታገሉ ሀገር ውስጥ ያሉ የኦሮሞ ብሄር ተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችን በእስር ላይ ማቆየቱ የሚያስከትለውን መዘዝ የናቀው ይመስላል፡፡
አሁን ተወደደም ተጠላ የፖለቲካ ሃይል ሚዛኑ ከሀገር ውስጥ ሰላማዊ የትግል አራማጅ ፖለቲካ ድርጅቶች በውጭ ሀገር ወዳሉ አክራሪና የመገንጠል አጀንዳ አራማጅ ቡድኖችና ግለሰቦች እያመዘነ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ የመንግስት አካሄድ ለሰላማዊ ትግል እና ዴሞክራሲያዊ ማሻሻያዎች የሚታገሉ ድርጅቶችን የሚያዳከምና ከመድረኩ የሚያርቅ ሆኗል፡፡ የራስን እድል በራስ መወሰንን ብቻ እንደ ግብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አክራሪ ሃይሎች ማህበራዊ መሠረታቸውን እንዲያጠናክሩ ያልተፈለገ እድል ማመቻቸት ደሞ ሀገሪቱን ውሎ አድሮ በተዋረዳዊ እና አግድሞሽ ግጭቶች እንድትናጥ በሮችን መክፈቱ አይቀርም፡፡
ባጠቃላይ መሠረታዊ የፖለቲካና ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ማሻሻያዎች በቶሎ ካልተወሰዱ ሀገሪቱ ማባሪያ ወደሌለው ብጥብጥ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ልትገባ የምትችልበት እድል ሰፋ ያለ መሆኑን የሚስማሙበት ወገኖች ብዙ ናቸው፡፡