Ethiopia Orthodox Church
Ethiopia Orthodox Church

በሀይማኖትና በፖለቲካ ትስስርም ይሁን ተቃርኖ ዙሪያ ብዙ የምርመር ፅሁፎች ተፅፈዋል። የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያን ደግሞ የፖለቲካ ጦስ መዘዝ ካመጣባቸው መካካል በቀዳሚነት ትጠቀሳለች። ሀገራችንን ጨምሮ በሌሎች የአለም አካባቢዎች ቤተ ክርስቲያኒቷን የመከፋፈል አደጋ እየፈተናት ይገኛል። መዝገቡ ሀይሉ ጉዳዩን የተመለከተ ዘገባ አለው። አድምጡት

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ሩሲያ ከዩክሬይን ጋር በነበራት ክራይሚያን የተመለከተ ፍጥጫ ወቅት ዜና ከነበሩት ነገሮች መካከል አንዱ በሁለቱ አገራት ባሉት የኦርቶዶክስ አብያተ ከርስቲያናት መካከል የተፈጠረው መከፋፈል ነበር።
የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬይንን ድምበር የዘለለውን ተጽእኑዋቸውን ሲያሳዩ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን የማያወላውል ድጋፉዋን አሳይታለች። መስቀል እና የቅዱሳን ስዕል የያዙ የቤተክርስትያኒቱ መነኮሳት ከሩስያ ታንኮች እና ወታደሮች ጋር በመሰለፍም አጋርነታቸውን አሳይተዋል። ከፑቲን ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸው የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ቄርሎስ ድሮም በአገራቸው ጉዳይ አንጀታቸው የማይጠና እና የቀድሞው የሩስያው ስለላ ተቁዋም ኬጂቢ አባል እንደነበሩ ይነገርላቸዋል።
ፓትርያርክ ቄርሎስ ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ከመጡበት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ 2009 ጀምሮ ለፕሬዚዳንቱ ለቭላድሚር ፑቲን የሩስያ ታላቅነት አጀንዳ ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል። በተለይ የሩስያ ዓለም ተብሎ ለሚታወቀው የሩስያን ተጽዕኖ ከሩሲያ ፌዴሬሽን ድምበሮች የዘለለ ታላቅነት እንዳለው ለሚያምነው አመለካከት መንፈሳዊ እና የታሪክ ድጋፍ መኖሩን በማሳየት ያደረጉት ንግግር ተጠቃሽ አጋጣሚ ነው። ፑቲንም ቤተክርስቲያን በመሳም እና በቤተክርስትያኒቱ ጉዳዮች ላይ ወገናዊነታቸውን በማሳየት ለቤተክርስቲያኒቱ ያላቸውን ታማኝነት አሳይተዋል።
ይህን የመሰለው ጉዳይ ግን በሩስያ ብቻ የተገደበ አይደለም። በብዙ የ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናት ተመሳሳይ ነገር ሲከሰት ይስተዋላል። እንዲያውም የኦርቶዶክስ አብያተክርስትያናትን በመከፋፈል በኩል አብያተ ክርስትያናቱ የሚያሳዩትን አገራዊ ስሜት የመሰለ አደገኛ ጉዳይ የለም ብለው የሚያምኑ ብዙዎች ናቸው።
በአብያተክርስቲያናቱ ውስጥ ይህን የመሰለ ስር የሰደደ አገራዊ ስሜት እንዲከሰት የሚያደርጉት ብዙ ምክንያቶች ቢጠቀሱም አገር እና ቤተክርስትያን ተደራራቢ የማንነት መገለጫ ኾነው የመገታቸው አጋጣሚ ዋነኛው ተጠቃሽ ነው። በተለይም የኦርቶዶክስ ክርስትና አማኞች ቁጥር አብላጫውን ይዞ ሲገኝ የሚያስከትለው ውጤት መኾኑን ስቲቭ ሄይስ የተባሉ በጉዳዩ ላይ የሚጽፉ ሰው ይናገራሉ።
የጉዳዩ አሳሳቢነት ዓለም አቀፍ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጉባዔም እንዲጠራ አድርጎ እንደነበረም በታሪክ ተመዝግቡዋል። ይህ በ1872 ዓመተ ምህረት በቁስጥንጥንያ ወይም ኮንስታንቲኖፕል ተደርጎ የነበረው ጉባዔ ይህን መሰል አጥባቂ የብሔራዊነት ስሜት በቤተክርስቲያን ውስጥ መኖር እንደኑፋቄ በመቁጠር እንዳወገዘውም ይነገራል። “የቤተክርስቲያን ሕልውና በአንድ አገር እጣፈንታ መወሰን የለበትም” ከሚል ድምዳሜ የደረሰው ይኸው ጉባዔ አብያተ ክርስትያናቱ ራሳቸውን ካቆራኙበት አገር ጋር ያላቸውን ትስስር በዓለም አቀፋዊ ዕይታ ለመቀየር ያሰበ ነበር።
ይህ ግን በብዙዎች ዕይታ የተሳካ አልኾነም። እስካሁንም ድረስ የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናት ጉዳይ ካሉበት አገር ጉዳይ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው።
የሩስያ እና የዩክሬይን አብያተ ክርስትያናት የደረሰባቸውን ክፍፍል የመሰለ ብዙ ክፍፍል በኢትዮጵያ አዕርቶዶክስ ቤተክርስትያንም ደርሶ ታይቱዋል። መንግስት በተቀየረ ቁጥር ፓትርያርኩ እና የቤተክርስትያኒቱ አስተዳደር አብሮ መቀየሩም የዚሁ ነጸብራቅ ነው። አሁን ባለበት ኹኔታ የእምነት እና የአምልኮ አፈጻጸም ልዩነት ሳይኖር ቤተክርስቲያኒቱ በሁለት ሲኖዶስ የመመራቱዋም ጉዳይ የአገሪቱ ፖለቲካ ምን ያህል ከቤተክርስትያኒቱ ሕልውና ጋር የተቆራኘ መኾኑን የሚያሳይ ነው።
ይህን የመሰለው ጉዳይ በካቶሊክ ቤተክርስትያን ሲከሰት አይታይም። ለዚህም እንደምክንያት ሲቀርብ የሚሰማው ነገር የካቶሊክ ቤተክርስትያን አወቃቀር ከኦርቶዶክስ አብያተክርስትያናት የተለየ መኾኑ ነው። የካቶሊክ አብያተ ክርስትያናት የሚመሩት መቀመጫውን ቫቲካን ባደረገ ማእከላዊ ስልጣን ሲኾን በተቃራኒው የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናት ርስበርሳቸው እንዲህ የሚያስተሳስራቸው ማዕከላዊ ነገር የላቸውም። በራሳቸው ፈቃድ ርስበርሳቸው ለመገናኘት እና ጉባዔ ለማድረግ ቢችሉም ይህ ግን እያንዳንዱ ቤተክርስትያን ያለውን ራስ ገዝ የኾነ ስልጣን የሚጋፋ አይደለም።
ከዚህም የተነሳ አብያተ ክርስትያናቱ በሚኖሩበት አገር ባህል ላይ ተጽእኖ ሲያደርጉ እና በእነርሱም ላይ ተጽእኖ ሲደረግባቸው በመኖራቸው አብያተክርስትያናቱ ርስበርሳቸው ያላቸው የባህል ልዩነት ራሱ በግልጽ የሚያታይ ነገር ነው። ይህ ከማእከላዊ ስልጣን ነጻ የመኾናቸው ጉዳይ የሰጣቸው ራሳቸውን ከሚኖሩበት ባህል ጋር የማስተሳሰር ነጻነት ከካቶሊክ ቤተክርስትያን ጋር ሲነጻጸር በጎ መኾኑ ቢመሰከርለትም፤ ለፖለቲካዊ ለውጦች ያላቸው ተጋላጭነት የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናቱን በመከፋፈል አደጋ ላይ እንዳይጥላቸው የሚሰጉም ጥቂት አይደሉም።