One-Belt-One-Roadዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር አዲሱ መስመር ዝርጋታ የሁለቱ ሀገራት የብቻ ፕሮጀክት እንደሆነ ይገለጽ እንጂ፣ የቻይና “ዋን ቤልት፣ ዋን ሮድ” ዕቅድ አንድ አካል መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡ በቻይናው መሪ ጂን ፒንግ ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው “ዋን ቤልት፣ ዋን ሮድ” ኢኒሼቲቭ በቻይና እና ወዳጅ ሀገራት መካከል የሁለትዮሽ የኢኮኖሚና ኢንቨስትመንት ትስስርን ለማጠናከር የተጀመረ ነው ቢባልለትም ዋና ዓላማው ግን ከዚህም የዘለለ መሆኑ ይነገራል፡፡ በባሕርና የብስ የቻይና “ቀበቶ” የጉዞ መስመር የተዘረጋባቸው ሃገራት፣ በመሰረተ ልማት ዝርጋታዎቹ ተጠቃሚ መሆናቸው ለጥያቄ ባይቀርብም፣ በዕቅዱ መሠረት በዋናነት የቻይናን ገበያ መር ፖሊሲ በተለያዩ ሃገራት ውጤታማ ለማድረግ የተበጀ ነው፡፡ ዳንኤል ድርሻ ያስናዳውን ዘገባ ዝለቁት

በየብስ የተዘረጋው የትራንስፖርት መስመር “ሲልክ ሮድ ኢኮኖሚክ ቤልት” (Silk Road Economic Belt -SREB) የሚሠኝ ሲሆን የውቅያኖስና ባሕሩ የመርከብ መስመር ደግሞ “ማሪታይም ሲልክ ሮድ” ተብሏል፡፡ መስመሩ ወደተዘረጋባቸው ሃገራት የቻይና ምርቶችን በፍጥነትና በምቹ ሁኔታ ማዳረስ… ከሃገራቱም ነዳጅ ዘይት፣ ጥሬ ዕቃና ማዕድናት ወደ ቻይና ማጓጓዝ ከዓላማዎቹ ውስጥ ይጠቀሳል፤ በየሃገራቱ የሚዘረጉት መሰረተ ልማቶች አብዛኛዎቹ በቻይናውያን ይዞታ ሥር እንዲሆኑ አለያም የባቡርና መርከብ ኩባንያዎች በቻይና ተቋማት እንዲዘወሩም ይደረጋል፡፡

መነሻውን ከቻይና በማድረግ… ስድሳ የኤዥያና የአውሮፓ ሀገራትን በየብስና በባሕር (ባቡርና መርከብ) በማስተሳሰር… በኤደን ባሕረ ሠላጤ አቋርጦ ምሥራቅ አፍሪካ የሚደርሰው “ዋን ቤልት፣ ዋን ሮድ”… ከኢትዮ ጂቡቲ የባቡር መስመር ጋር ይያያዛል፤ በሌላ የምስራቅ አፍሪካ ትስስር ከሞምባሳና ዛንዚባር ጋር ይገናኛል፡፡ ከአንድ ቢሊየን ዩአን (160 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር) የተመደበለትን ይሕን ሥራ የሚመራውን ኮሚቴ የሃገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንትና ሠባት የኮሙኒስት ፓርቲው አመራሮች ይከታተሉታል፡፡ በትንሿ የአፍሪካ ቀንድ ሃገር ጂቡቲ እየተገነባ የሚገኘው አዲስ ወደብ እንዲሁም የተሰሩት ሁለት አየር ማረፊያዎችና የነዳጅ ቱቦዎች በቻይና “ዋን ቤልት፣ ዋን ሮድ” ሥር ሲሆኑ፣ ግንባታው የተጀመረው ግዙፉ የጦር ሠፈርም የዚሁ ትስስር አካል ነው፡፡ ይሕም ቻይና በአፍሪካ ቀንድ በኩል ዘልቃ በአሕጉሪቱ ለመንሠራፋት እና ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ የምታደርገው እንቅስቃሴ ጠቅሚ ተደርጎ ተወስዷል፡፡ የሩቅ ምስራቋ ሃገር … በአፍሪካ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ውስጥ ሳይቀር እየገባች… ነዳጅ እስከ ከማውጣት የደረሱ ፕሮጀክቶችን አሳክታለች፡፡ በስፋት ከምትታወቅበት የመሠረተ ልማት ዝርጋታ… ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችን እስከ ማቋቋም ተሻግራለች፡፡ ትርፋማና አዋጪ በሆነ የማዕድን ማውጣት ተሠማርታለች፡፡

የ“ቀበቶ” መስመር ዝርጋታዋን ወደ አፍሪካ መለጠጧ… የቀደመውን ትስስር አጠንክራ ለመዝለቅ መጓዟን አመላካች መሆኑም ተገልጿል፡፡ ሆኖም አካሄዷን የሚቃወሙ ደግሞ ወደ አዲስ ቅኝ አገዛዝ ዘመን (ኒዎ ኮሎኒያሊዝም) የሚደረግ አዲስ ጉዞ ይመስላል እያሉ ነው፡፡ ከቻይና የሚነሳው ቀበቶ መስመር ውስጥ የታቀፉ የባቡርና መርከብ መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች ወይ ሙሉ በሙሉ… አለያም አብላጫ ወጪያቸው በቻይና መንግሥት ነው የሚሸፈነው፡፡ በብዙዎቹ የኤዥያ ሃገራት የተዘረጉ ባቡር መስመሮች የብድር ፕሮጀክትን ያመቻቸው… ራሷ ቻይና ያቋቋመችው “ኤዥያ ዴቨሎፕመንት ኤንድ ኢንቨስትመንት” የተባለው ባንክ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ በጂቡቲ የተካሄዱ መሰረተ ልማቶችና ጦር ሠፈር ግንባታ ሙሉ ወጪ በቻይና መንግሥት ይሸፈናል፡፡

ኢትዮጵያን ከጂቡቲ ወደብ የሚያገናኘው 756 ኪሎ ሜትር የባቡር መንገድ ወደ አገልግሎት የተሻገረ ሲሆን፣ ሁለቱ ሃገራት የባቡር ጣቢያውን የሚያስተዳድር የጋራ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ በክረምቱ ሠሞን ለድርቅ ተጎጂዎች የሚደርስ ስንዴ በማመላለስ የሙከራ ጉዞውን የጀመረው የባቡር መስመሩ በኢትዮጵያ ግዛት ያለው 656 ኪሎ ሜትር ርዝመት ተመርቆ የተከፈተው በጥቅምት 2009 ሲሆን፣ ቀሪው 100 ኪሎ ሜትር ተጠናቆ አሁን ዝግጁ ሆኗል፡፡ በኢትየጵያ በኩል የተከናወነው ሥራ 3.4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ማስወጣቱም ተገልጿል፡፡

ለኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ዝርጋታ ከኢትዮጵያ መንግስት የተገኘው ፋይናንስ 30 % ሲሆን፣ የተቀረው 70 % ገንዘብ የተገኘው ከቻይና ኤግዚም ባንክ፣ ከቻይና ልማት ባንክ እና ኢንዱስትሪያል ኤንድ ኮሜርሻል ባንክ ኦፍ ቻይና ከሚባሉ ሶስት ባንኮች ነው፡፡ ከግንባታ እስከ ሃዲድ ዝርጋታ ያለውን ሥራ ያከናወኑትም ቻይና ሬይልዌይ ግሩፕ እና ቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ናቸው፡፡ የሙከራ ጉዞውን በሚቀጥለው ሠኔ ወር የሚጀምረው የናይሮቢ-ሞምባሳ ኤሌክትሪክ ባቡር ፕሮጀክት 90 % ገንዘብ የተገኘው ከቻይና መንግሥት ነው፡፡ ግንባታውን የሚያከናውነትም ቻይና ሮድ ኤንድ ብሪጅ ኮርፖሬሽን እና ቻይና ሬልዌይ ኮንስትክራሽን ኮርፖሬሽን ሊሚትድ የተሰኙ ከሩቅ ምስራቅ የመጡ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ …በነገራችን ላይ 472 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የናይሮቢ-ሞምባሳ እና 756 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው የኢትዮ ጂቡቲ ባቡር ዝርጋታ የተመደበላቸው ወጪ… እኩል የሚባል ተቀራራቢ ዋጋ ነው፡፡ የኬንያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ለዚህ በሠጡት ምላሽ… ወጪው እንዲህ ባለ ሁኔታ ሊጋነን የቻለው የኢትዮ ጂቡቲው መስመር በጥራትና በአገልግሎት ዘመን ዝቅ በሚለው “ክላስ ቢ” ደረጃ ስለተሰራና… የናይሮቢ-ሞምባሳው በ“ክላስ ኤ” የሚገነባ በመሆኑ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የቻይና እና አፍሪካውያን ትስስር በተለይ በቅኝ ግዛት ዘመን እየተጠናከረ መሄዱ ይታወቃል፡፡ ከአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ነጻ ለመውጣት በተደረገው ትግል ብዙዎቹ አፍሪካውያን ታጋዮች ከቻይና የወታደራዊ ስልጠና፣ የመሳሪያ ሌሎች ዕርዳታዎች ማግኘታቸው የሚታበል አይደለም፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የቻይና አፍሪካ ግንኙነት በተለይ በኢከኖሚው ረገድ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ተሻግሯል፡፡ ከአሕጉሪቱ ጋር ከ200 ቢሊየን ዶላር በላይ ዓመታዊ የንግድ ትስስር የፈጠረችው ሩቅ ምስራቃዊቷ ሃገር ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ዩኤስ አሜሪካና አውሮፓን በብዙ እጥፍ አስከንድታለች፡፡ የቻይና አፍሪካ ትስስር እንዲህ የጠበቀው እንዲያው በአጋጣሚ ሳይሆን… የቻይና አዲሱ ገበያ መር ፖሊሲ ለአፍሪካ መንግሥታት በእጀጉ የተመቸ በመሆኑ ነው፡፡ በዚያም ላይ የአፍሪካ መሪዎች በሙስና መዘፈቅና የሠብዓዊ መብት ረገጣ ጉዳይ ለቻይና ቁብ የሚሠጣት አለመሆኑ ትስስሩን ለማጠናከር ሌላ ተጨማሪ ሠበብ ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩ ሃምሳ ዓመታት ቢጠጋም… ቀደም ባሉ ጊዜያት የጠበቀ ትስስር አልነበራቸውም፡፡ በአብዮቱ የመጀመሪያ ሠሞናት የመኢሶን አመራሮች የወታደራዊ መንግስቱን ሹማምንት ይዘው ወደ ቻይና ቢጓዙም የጠበቁትን ምላሽ አለማግኘታቸው ወታደራዊው መንግሥት ፊቱን ወደ ሶቪየት ሕብረት እንዲዞር አስገድዶታል፤ ይሕም ከቻይና ጋር የበረው ግንኙነት እንዳሻከረ እንዲዘልቅ አድርጎታል፡፡ ከወታደራዊው መንግሥት መውደቅ በኋላ  የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በ1984 ወደ ቻይና አምርተው የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ይሕ ከሆነ ከስምንት ዓመት አልፎ… ኢትዮጵያ ሁለተኛውን “የቻይና አፍሪካ ፎረም” ካስተናገደች በኋላ ግን ተመሳሳይ ፖለቲካና የፓርቲ አወቃቀር እንከተላለን ያሉት ሁለቱ ሃገራት ግንኙነታቸውን በእጅጉ አጥብቀውታል፡፡

ጥሬ ሀብት በማቅረብ ረገድ ከሌሎች አንጻር ኢትዮጵያ ለቻይና ያን ያሕል የምታወላዳ ባትሆንም፣ ከግብርና ምርት አቅርቦት በላይ ሠፊ የሕዝብ ቁጥሯ ሠፊ የገበያ ቦታ ፍለጋ ቻይናን ማማለሉ አይቀሬ ነበር፡፡ በ2014 ኢትዮጵያ ወደ ቻይና ከላከችው የግብርና ምርቷ 456 ሚሊየን ዶላር ስታስገባ፣ ቻይና በአንጻሩ ወደ ኢትዮጵያ ከላከችው የኢንዱስትሪ ምርት ያገኘችው 4.5 ቢሊየን ዶላር ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የገበያ አማራጭነትም በርካታ የቻይና ኩባንያዎች ተስበው እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ1992-2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ አጠቃላይ የቻይና ኢንቨትስመንት 16.2 ቢሊየን ብር (773 ሚሊየን ዶላር) የደረሰ ሲሆን፣ ይሕም ከየትኛውም የውጪ ሃገር ኢንቨስትመንት የላቀ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይሁን እንጂ ርካሽ ምርቶችን ከማራገፍ አንስቶ፣ በሙስና መተሳሰር፣ የዕውቀት ሽግግር ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆን… የብዙዎቹ የቻይና ኩባንያዎች ችግር ቢሆንም… “ልማታዊ ናቸው” የሚለው ምክንያት የመንግሥት ጡጫና ግልምጫ እንዳይደርስባቸው ከልሏቸዋል፡፡

95 % የኢትዮጵያ የውጪ ንግድ በር የሆነችው ጂቡቲ… በቻይና “ዋን ቤልት፣ ዋን ሮድ” ዕቅድ የተለየ ትኩረት ከተሠጣቸው የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት ቀዳሚዋ ሳትሆን አልቀረችም፡፡ ቻይና ቢሊየን ዶላሮችን በመከስከስ አዲስ ወደብ፣ ሁለት አውሮፕላን ማረፊያዎች ገንብታለች፡፡ በታጁራ የፖታሽ ማዕድን ማከማቻ፣  በአሳል ሐይቅ የጨው ማውጫ ፋብሪካ እንዲሁም የውሃ፣ የነዳጅና የጋዝ ቱቦዎች ዝርጋታ በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡ በዶራሌሕ አዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ እና በኦቦክ አቅራቢያ የቻይና የመጀመሪያው የባሕር ማዶ የጦር ሠፈር ግንባታ ተጀምሯል፡፡ ቻይና እስከ 2026 ትቆይበታለች የተባለችው ይሕ ጦር ሠፈር አስር ሺህ ወታደሮች የመያዝ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡ ቻይና እዚህም እዚያም በምትገኝበት በአሕጉረ አፍሪካ… ይሕን ያሕል ሠራዊት የሚያስተናግድ ጦር ሠፈር መገንባቷ ወደፊት በአፍሪካ በሠፊው ለመንሠራፋት ለመዘጋጀቷ ማረጋገጫ ተደርጎ እየቀረበ ይገኛል፡፡

የሻንጋይ ኢንስቲቲዩት መምሕር ፕሮፌሰር ሊ ዌይጂን “በጂቡቲ የሚዘረጉት ፋሲሊቲዎች በአፍሪካ የቻይናን ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ የታለሙ ናቸው” ሲሊ የሠጡት ማብራሪያም ወታደራዊ የጦር ሠፈሩ ከአካባቢያዊ ትብብር ባሻገር ለሌላ ዓላማ የታቀደ ስለ መሆኑ ጠቋሚ ነው አስብሏል፡፡ በጂቡቲ ከተገመተው በላይ በመፍሰስ ላይ የሚገኘው የቻይና መዋዕለ ነዋይ… ከጦር ሠፈሩ ጋር ሲዳመር  ሌላ መልዕክት እያስተላለፈ ነው የሚሉም አሉ፡፡ የቻይናን እንቅሰቃሴ በጥርጣሬ ሲከታተሉ የቆዩ ወገኖች ደግሞ… ቀደም ሲል በአንዳንድ ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ሲገለጽ የነበረውን በመድገም… “ቻይና በአፍሪካ አዲሱን ዓይነት የቅኝ አገዛዝ (ኒዎ ኮሎኒያል) እንቅስቃሴ እያራመደች ይሆን?” ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡