HR Ethiopia
30 ኛውን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክርቤት መደበኛ መርሃ ግብር በማስመልከት ተዘጋጅቶ በነበረው ኢትዮጵያን የሚመለከት የጎንዮሽ ጉባዔ ላይ ተሳታፊ የነበሩ የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ጉባዔውን ረግጠው ወጡ።

ራሳቸውን በስም ያላስተዋወቁት እነዚሁ የኢትዮጵያ መንግስት ወኪሎች ጉባዔውን ረግጠው ከመውጣታቸውም በፊት ከዲፕሎማት የማይጠበቁ የስድብ ቃላትን የጥናት ወረቀት ባቀረቡት እንግዶች ላይ ሲሰነዝሩ እንደነበረም በስፍራው የነበሩ የጉባዔው ታዳሚዎች ታዝበዋል። (መዝገቡ ሀይሉ ዝርዝሩን አዘጋጅቶታል እነሆ ያድምጡት)


መሰከረም 17 ቀን 2008 ዓም ተደርጎ የነበረው የመጀመሪያው የጎንዮሽ ጉባዔ የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ መብት ምክር ቤቱ አባል ለመኾን ዳግመኛ ለመመረጥ እያደረገ ያለውን ውትወታ የሚቃወም ይዘት ያለው ነበረ። በይዘቱም ውስጥ ኢትዮጵያ የምክርቤቱ አባል በኾነችባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚዘረዝሩ ጥናቶች ቀርበውበታል።

ጉባዔው የተዘጋጀው በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት፣በ ሂዩማን ራይትስ ዎች እና በምሥራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ጥምረት ነበር። ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ኾና ዳግመኛ እንዳትመረጥ የሚሞግቱ ሐሳቦች ያላቸው የጥናት ወረቀቶች ቀርበውበታል። በቀረቡትም መከራከሪያዎች ላይ ኢትዮጵያ መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች ድንጋጌን እንደማታሟላና ከመንግስታቱ ማኅበር ልዩ ራፖርተሮች የሚቀርቡላትን የጉብኝት ጥያቄዎች ለመመለስ ፈቃደኛ ያልኾነች አገር መኾኗ ተገልጿል።

የሰብአዊ ምክር ቤቱ መቀመጫ በልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች ለሚገኙ አገራት በኮታ የሚሰጥ ሲኾን አፍሪካም 13 መቀመጫዎች ይደርሷታል። ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት አፍሪካን ወክለው በምክር ቤቱ ለመቀመጥ ለሶስት ዓመት ከተመረጡ 13ቱ የአፍሪካ አገራት አንዷ ነበረች። ይህንኑ ውክልና ለሁለተኛ ዙር ለማግኘት እየወተወቱ የሚገኙት የኢትዮጵያ መንግስት ዲፕሎማቶች የዚህን ጉባዔ ውይይት መታገስ እንዳቃታቸው ተነግሯል።
የሰብአዊ መብት የማያከብሩ የምክር ቤቱ አባል አገራት ላይ ተጽዕኖ እንዲያድርግ የሚጠይቅ መግለጫ አውጥቷል። ድርጅቱ የሰብአዊ መብት ድንጋጌን አያሟሉም ካላቸው አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች።