Eritrea mapዋዜማ ራዲዮ- ቅዳሜ ምሽት የተቀሰቀሰው የድንበር ግጭት ዛሬ ሰኞ ድረስ ቀጥሎ ማርፈዱን ከአካባቢው የተገኙ የዋዜማ ምንጮች ገለፁ።

የኢትዮጵያ መንግስት የኮምንኬሽን ጉዳዮች ሚንስትር ጌታቸው ረዳ በሁለቱ ሀገራት መካከል ውጊያ መደረጉንና ውጊያው መቀጠሉን ዛሬ ለፈረንሳይ አለማቀፍ ራዲዮ ተናግረዋል። ውጊያውን የጀመረው የኤርትራ መንግስት ነው ሲሉ ከሰዋል። የኢትዮጵያ ሰራዊት የተከፈተበትን ጥቃት መክቶ በመልሶ ማጥቃት ላይ መሆኑንም ገልፀዋል።

ቅዳሜ ምሽት እንደተጀመረ የተነገረለት የተኩስ ልውውጥ በፆረና ግንባር በኩል ዛሬም እስከ ረፉዱ አምስት ሰዓት ግድም በርትቶ መቀጠሉን ምንጮች ይናገራሉ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በድንበር ያለውን ለማጠናከር ተጨማሪ ኃይል ወደ ቦታው ማጋጋዙን እንደቀጠለ ጨምረው ገልፀዋል። የአድዋ ከተማ ነዋሪዎች ለሊቱን በታንክ የተደገፈ የሜካናይዝድ ጦር ወደ ድንበር አቅጣጫ ሲያመራ መመልከታቸውን ለዋዜማ አስረድተዋል።

የከባድ ተኩስ ልውውጡ በዋናነት እየተካሄደባት የምትገኘው ፃረና ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኃላ እንደ ዛላምበሳ ሁሉ ለሁለት ተከፍላለች። የፆረና ከተማን ጨምሮ አብዛኛው ክፍል በኤርትራ እጅ ሲገኝ የገጠር መንደሮቹ በኢትዮጵያ ቁጥጥር ስር ቆይተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ግጭት አይሎ ከሚታይባት ፆረና አካባቢ በተጨማሪ በተለያዩ የድንበር አካባቢዎች ጦሩን በተጠንቀቅ እንዲቆም አድርጓል። “ኢትዮጵያ ወረራ ልትፈፅምብኝ ነው” ያለችው ኤርትራ ከጦር ሰራዊቷ ከፍተኛ ልምድ ያለውን ዕዝ በሶስት አካባቢዎች እንዲስፍር አድርጋለች። የኤርትራ ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ የተቀመጡ ሲሆን ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ ክተት ሊያውጁ እንደሚችሉ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ሁሉም የክፍለ ጦር አዛዦችን ወደ ግንባር እንዲንቀሳቀሱ የደረገች ሲሆን በእረፍት ላይ የነበሩ ሁለት ከፍተኛ አዛዦችም በአስቸኳይ ወደ ምድባቸው እንዲመለሱ ታዘዋል።

በመሬት ላይ ስላለው የጦር እንቅስቃሴ ያለፉት ሀያ አራት ሰዓታትን የሳተላይት ምስል ለመመልከት ባደረግነው ሙከራ በሁሉም የድንበር አካባቢዎች የለው የጦር አስፋፈር የተበታተነና በትናንሽ የሜካናይዝድ ክፍሎች የታገዘ ነው። ይህም በጦርነቱ ለመቀጠል በሁለቱም ሀገሮች በኩል ፍላጎት አለመኖሩን ጠቋሚ ይመስላል። የክረምቱ ወራት መቃረብም ለወታደራዊ እንቅስቃሴ አመቺ አይደለም።