Saudi Star facility in Gambella

 

የኢትዮዽያ መንግስት ብዙ ተስፋ የጣለበትንና የውጪ ምንዛሪ እንደሚያመጣ የተነገረለት የሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ውድቀት ገጥሞታል። መንግስት ላልተወስነ ጊዜ መሬት መስጠት ማቆሙን አስታወቋል። በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ከመሬት ጋር የተያያዘ ቀውስና የድርቅ አደጋ ኢህአዴግ በመሬት ጉዳይ አቋሙን እንዲመረምር ግድ ሳይለው አልቀረም። ቻላቸው ታደሰ ያዘጋጀውን ዘገባ እነሆ።

የኢትዮጵያ መንግስት ለኢንቨስተሮች ለግብርና ስራ የሚውሉ ሰፋፊ ለም መሬቶችን ላልተወሰነ ጊዜ መስጠት ማቆሙን ገልጧል፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ፌደራል መንግስቱ በውክልና የክልሎችን ሰፋፊ ለም መሬቶች ተረክቦ ለውጭ ባለሃብቶችና ዓለም ዓቀፍ የእርሻ ኮርፖሬሽኖች በርካሽ በሊዝ ሲያከራይ መቆየቱ ብርቱ ትችት አስከትሎበት ነበር፡፡ ሆኖም መንግስት ትችቶቹ ሁሉ “የሀገሪቱን ዕድገት ማየት የማይፈልጉ ኃይሎች ሴራ” ናቸው በማለት ሲያጣጥል ቢቆይም በድንገት ግን ፖሊሲውን ለመፈተሸ ተገዷል፡፡  መንግስት ፖሊሲውን እርግፍ አድርጎ ባይተወውም በዘርፉ የታዩ ችግሮችን ገምግሜ መፍትሄ እስከምሰጥ ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ ለም መሬት ለባለሃብቶች መስጠቴን አቁሚያለሁ ብሏል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ ቀደም ሲል ሰፋፊ እርሻዎች ለባለሃብቶች ወደ ተሰጡባቸው ክልሎች የጥናት ቡድን መላካቸውን የዘገበው ራዲዮ ፋና የአሁኑ ውሳኔ የዚያ ጥናት ውጤት መሆን አለመሆኑን አልገለፀም፡፡

መንገድ የለም… ሰባራ ሳንቲም የለም….

መንግስት እዚህ ውሳኔ ላይ እንዴት ሊደርስ ቻለ? የሚለውን ጥያቄ መፈተሸ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ፋና ዘገባ ከሆነ ለፖሊሲ ለውጡ እንደምክንያት የቀረበው የግብርና ኢንቨስትመንት እና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ በአራት ክልሎች በአደራ ከተረከበው ለም መሬት 470 ሺህ ሄክታሩን ለ131 ባለሀብቶች ቢሰጥም ውጤታማ የሆኑት ግን ከ30 በመቶ ብቻ መሆናቸው ነው፡፡ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው መንግስት መስሪያ ቤቶች የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ግዙፍ እርሻ አልሚዎቹ ውጤታማ ሊሆኑ ያልቻሉት ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችንና የሰው ሃይልን ለም መሬቶች ወደሚገኙባቸው ሩቅ ቦታዎች ለማድረስ ባለመቻላቸውና ሰባት ያህል የውጭ ኢንቨስተሮችም በቅርቡ ፍቃዳቸው በመሰረዙ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ መንግስት ከዘርፉ አገኛለሁ ብሎ የጠብቀው የውጭ ምንዛሬም እንደታሰበው አለመሆኑ የመንግስትን ፖሊሲ አጣብቂኝ ውስጥ ያስገባ ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ታዛቢዎች ያስረዳሉ፡፡

ህንዶቹ… መጡ? ሄዱ?

ምንም እንኳ የአሁኑ የመንግስት ውሳኔ ድንገተኛ ቢመስልም በመንግስትና በግዙፎቹ እርሻ ኢንቨስተሮች መካከል ያለው ግንኙነት እየሻከረ መመምጣቱ የታወቀው ግን ቀደም ብሎ ነበር፡፡ በተለይ በጋምቤላ ክልል 25 ሺህ ሄክታር ተረክቦ የነበረው የህንዱ ሳበር፣ 5 ሺህ ሄክታር የነበረው ሌላኛው የህንድ ኩባንያ ጄ.ቪ.ኤል እና ግዙፉ ካራቱሪ ግሎባል ኩባንያ ፍቃዳቸው ከተሰረዘባቸው በኋላ፡፡

Indian Karaturi CEO, Karaturi
Indian Karaturi CEO, Karaturi

ባለፈው ታህሳስ ወር ደግሞ ግንኙነቱ ማሽቆልቆሉና የመንግስት መከራከሪያ ውሃ የማይቋጥር መሆኑ የተጋለጠው በጋምቤላ ክልል 100 ሺህ ሄክታር ተረክቦ የነበረው በዓለም በፅጌረዳ አበባ አምራችነቱ የሚታወቀው የህንዱ ካራቱሪ ከሁለት ዓመት በኋላም ስራ መጀመር ባለመቻሉ መንግስት መሬቱን ነጥቆ ወደ መሬት ባንክ ገቢ ሲያደርግ ነው፡፡ ካራቱሪ ገና ከማለዳው 300 ሺህ ሄክታር ተረክቦ በኋላ ግን ወደ 100 ሺህ ሄክታር ዝቅ መደረጉ መንግስት የኩባንያዎችን አቅም ግምት ውስጥ ሳያስገባ በደመ-ነፍስ ለም መሬት ሲሸነሽን እንደኖረ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ካራቱሪ ግን በመንግስት ያላግባብ የተጣሰውን መብቴን በዓለም ዓቀፍ ህግ አስከብራለሁ እያለ መዛቱን አላቆመም፡፡

መንግስት ግልፅነት የጎደለውን ግዙፉን የለም መሬት ኪራይ በረከት ይዞ መጥቷል እያለ ለማሳመን ቢለፋም ፖሊሲው በአብዛኛው ህዝብ ዘንድ በጥርጣሬ ይታያል፡፡ ሰፋፊ እርሻዎቹ ለሀገሪቱ ምግብ ዋስትና መሻሻል ጠብ የሚደርጉት አስተዋፅዖ አለመኖሩ ደግሞ ጥርጣሬውን አባብሶት ቆይቷል፡፡

በያዝነው ዓመት በሀገሪቱ መጠነ-ሰፊ ድርቅ ሲከሰት በወጭ ንግድ ላይ ለተሰማሩ አትራፊ ግዙፍ ኩባንያዎች ለም መሬት ሲሸነሽን የኖረው መንግስት ወደያውኑ ዓለም ዓቀፍ ለጋሾች ምግብ ዕርዳታ እንዲለግሱት መማፀኑ የመንግስት ምግብ ዋስትና ፖሊሲ ውድቀት ማሳያ እንደሆነ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡

ከውጭ ባለሃብቶች የግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ማግኘት ይቻላል በማለት ሲከራከር የኖረው መንግስት አሁን ግን አመርቂ ውጤት ስላልተገኘበት አሰራሩን ላቆመው ወስኛሁ ማለቱ ብዙዎችን ማስገረሙ አይቀርም፡፡ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ሲያድበሰብስ ቢኖርም በአስተዳደራዊ ችግሮች ሳቢያ ምክንያት ታች አምና ብቻ 43 መሬቶች ለተለያዩ ባለሃብቶቸ ተሰጥተው፣ መሬቶቹን የተረከቡ ባለሃብቶችም ለተመሳሳይ መሬት ከባንክ ተደራራቢ ብድር ወስደው መገኘታቸውን አምኗል፡፡ አበዳሪዎቹ የመንግስት ባንኮች ግን ለሰፋፊ እርሻ ልማት የሚሰጡት ብድሩ ምን ላይ እንደዋለ ማወቅ ያልቻሉበት ሁኔታ መፈጠሩን አምኗል፡፡  ባንኩ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ለሰፋፊ እርሻ ልማት ስድስት ቢሊዮን ብር አበድሯል፡፡ በመንግስት ፖሊሲ ድክመት ሳቢያ ባንኮች የገጠማቸው መጠነ-ሰፊ ኪሳራ ወደፊት ይታወቅ እንደሆን እንጂ እስካሁን የተሟላ መረጃ የለም፡፡ መንግስትን በፓርላማ ተጠያቂ የሚያደርግ አሰራር ባለመዘርጋቱ እንጂ ግዙፍ የመሬት ኢንቨስትመንት ፖሊሲው ከፍተኛ ውድቀት እንደሚያስከትል የዘርፉ ባለሙያዎች ማስጠንቀቅ የጀመሩት ገና ከማለዳው ነበር፡፡

በታዳጊ ሀገሮች የሚደረገውን መሬት ቅርምት ያባባሰው በሰለጠነው ዓለም ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ በምርት አቅርቦትና ምግብ ፍላጎት መካከል ያለው ክፍተት እየሰፋ በመምጣቱ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በተለይ እኤአ የ2007ቱ ዓለም ዓቀፍ የምግብ ሰብል ዋጋ ንረት እና የ2008ቱ ዓለም ዓቀፉ የፋይናንስ ቀውስ መንግስታትና ዓለም ኣቀፍ ኮርፖሬሽኖችን በተለምዶ ከሚታወቁት የኢንቨስትመንት ዘርፎች ወጣ ብለው በታዳጊ ሀገሮች ለም መሬቶች ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር ኢንቨስትመንት እንዲጀምሩ ገፋፍቷቸዋል፡፡

በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጥናት ሲነገር እንደኖረው በዓለም አቀፉ መሬት ሽሚያ ኢትዮጵያን የተለየ የሚያደርጋት ለም መሬቷን በገፍ ማቅረቧ ብቻ ሳይሆን መንግስት የሚያቀርበው ዓመታዊ የመሬት ኪራይ ዝቅተኛ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ ሳዑዲ ስታር እንኳ በሄክታር የሚከፍለው ዓመታዊ ኪራይ ስልሳ ብር ወይም ሶስት ዶላር ብቻ ነው፡፡ ኢንቨስተሮቹ የታክስ እፎይታ ጊዜ እና የባንክ ብድርም ተጠቃሚ ሲሆኑ ቆይተዋል፡፡ ለሰፋፊ እርሻ ኢንቨስትመንት ጀርባውን ሰጥቶ የኖረው ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት የዛሬ አስር ዓመት አካባቢ መሰረታዊ የፖሊሲ ለውጥ በማድረጉ ኢትዮጵያ በአወዛጋቢውና ውስብስቡ  የመሬት ቅርምት ስሟ በቀዳሚነት እንዲነሳ አድርጓታል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ ከቻይና፣ ህንድ፣ ሱዳን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ቱርክና ፓኪስታን የመጡ ከሃምሳ በላይ ኢንቨስተሮች  በተለያዩ ክልሎች መሬቶችን ይዘዋል፡፡ በተለይ ምግባቸውን ከውጭ የሚያስገቡት ቱጃሮቹ የዓረብ ሀገራት ኢትዮጵያ፣ ሞዛምቢክ፣ ዛምቢያ፣ ሱዳንና ታንዛኒያን በመሳሰሉ የአፍሪካ ሀገሮች ለም መሬት በመቀራት ላይ ተጠምደው ኖረዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም የአሁኑን ድንገተኛ ለውጥ እስካደረገበት ዕለት ድረስ በጠቅላላው 3.3 ሚሊዮን ሄክታር ለም መሬት በሊዝ ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ሲሰብክ ነበር፡፡

መንግስት ለም መሬቶችን ለኢንቨስተሮች ለማስለቀቅ ሲል በጋምቤላና ደቡብ ኦሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን “አስገድዶ በሌሎች ቦታዎች አስፍሯል፤ በሂደቱም ሰብዓዊ መብቶችን ጥሷል” በማለት ኦክላንድ ኢንስቲትዩትና ሂውማን ራይትስ ዎች የሰላ ውንጀላ ያቀርቡበታል፡፡ ኣለም ባንክም የመንግስትን ፕሮጄክት አግዟል የሚል ውንጀላ ቀርቦበት በያዝነው ዓመት ፖሊሲውን እንደገና ለመፈተሽ መገደዱ ይታወሳል፡፡ መንግስት ግን የሰፈራዎቹ ዓላማ መሰረታዊ ማህበራዊ አግልግሎቶችን ለዜጎች ለማዳረስ እንጂ ከመሬት ቅርምት ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም በማለት ሽንጡን ገትሮ ከመከራከር አልቦዘነም፡፡

ፓርቲውና አል አሙዲን

Gabella
Residents In Gambella

በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ ፋይናንሻል ታይምስ የተሰኘው ታዋቂው የእንግሊዝ ጋዜጣ በመልቲ ሜዲ ክፍሉ አማካኝነት ዓለም ዓቀፍ የእርሻ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ግዙፍ የመሬት ቅርምት ላይ ባጠናበት ሪፖርቱ ገዥው ፓርቲ ሰፋፊ ለም መሬቶችን በገፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች የሚያከራየው በመሬት ላይ ያለውን ባለቤትነት አስጠበቆ ለመቀጠል እንዲያመቸው ሊሆን እንደሚችል ያለውን ጥርጣሬ አልሸሸገም፡፡ በኢትዮጵያ የመሬት ባለቤትነት የፖለቲካ ስልጣን ማስጠበቂያ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ ፋይናንሻል ታይምስ የተሰኘው ታዋቂው የእንግሊዝ ጋዜጣ በመልቲ ሜዲ ክፍሉ አማካኝነት ዓለም ዓቀፍ የእርሻ ኢንቨስተሮች በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ግዙፍ የመሬት ቅርምት ላይ ባጠናበት ሪፖርቱ ገዥው ፓርቲ ሰፋፊ ለም መሬቶችን በገፍ ለውጭ ኢንቨስተሮች የሚያከራየው በመሬት ላይ ያለውን ባለቤትነት አስጠበቆ ለመቀጠል እንዲያመቸው ሊሆን እንደሚችል ያለውን ጥርጣሬ አልሸሸገም፡፡ በኢትዮጵያ የመሬት ባለቤትነት የፖለቲካ ስልጣን ማስጠበቂያ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በተለይ በሼክ ሙሃመድ አላሙዲን ባለቤትነት በተያዘው ሳዑዲ ስታር እርሻ ላይ ያተኮረው የፋይናንሻል ታይምስ ጥናት እንደሚያሳየው ባለሃብቱ በጋምቤላ ክልል ከ20 ሺህ እግር ኳስ ሜዳዎች ጋር የሚስተካከል ለም መሬት ይዘዋል፡፡ ይህም ቱጃሩን ከዓለም ግንባር ቀደም ለም መሬት ተቀራማቾች ተርታ እንደሚያሰልፋቸው ያትታል፡፡

ለአሁኑ የመንግስት ውሳኔ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች እንደተጠበቁ ሁነው መንግስት ከመሬት ጋር በተያያዘ የተነሳው በኦሮሚያ ክልል የተነሳው ህዝባዊ አመፅ ወደሌሎች ክልሎችም እንዳይጋባ ስጋት አድሮበት ሊሆን ይችላል፡፡ እንደ ሂውማን ራይተስ ዎችና ኦክላንድ ኢንስትቲዩት ያሉ የመብት ተሟጋች ዓለም ኣቀፍ ድርጅቶችም በመንግስት ላይ የሚያቀርቡት ውንጀላ ተባብሶ መቀጠሉም አስተዋፅዖ አይኖረውም ለማለት ያስቸግራል፡፡

ምንም እንኳ በመንግስት ብዙ ባይነገርለትም በተለይ በጋምቤላ አኝዋኮች በሚያዝያ 2004 በሩዝ አምራቹ ሳኡዲ ስታር እርሻ ላይ ጥቃት ፈፅመው አምስት ሰራተኞችንመግደላቸው ለመንግስትም ሆነ ለቱጃሩ ማስጠንቀቂያ ደወል ነበር፡፡ ከሀገሪቱ ክልሎች ከፍተኛ መጠን ያለው ለም መሬት ለውጭ ኢንቨስተሮች የተሰጠባት ጋምቤላ ግዙፎቹ የዓለም ዓቀፉ ገበያ ሃይሎች ከዘልማዳዊው አኗኗር ዘይቤ ጋር በቀጥታ የተላተሙባት ዓይነተኛ ማሳያ ሆናለች፡፡ የመሬት ቅርምቱ ወደፊት ግጭት ቀስቃሽ እንደሚሆን ዓለም ኣቀፍ ተቋማት የሚያስጠነቅቁትም  ይህንን ግጭት መነሻ በማድረግ ነው፡፡ ፋይናንሻል ታይምስም በሪፖርቱ ምንም እንኳ ባለሃብቶች በተለያዩ ሀገሮች ቴክኖሎጂና ስራ ዕድሎችን ለማቅረብ ተስፋ ቢሰጡም መሬት ግን በቀላሉ ሊያለምዱት ከማይችሉት አንበሳ ጋር ተመሳስሎባቸዋል በማለት መሬት ለገጠር ገበሬዎች ሸቀጥ ሳይሆን የምግብ ዋስትና ምንጭና የማህበራዊ ማንነታቸው መሰረት መሆኑን ያሰምረበትም ለዚህ ነው፡፡

በ2009 ለሃምሳ ዓመታት 10 ሺህ ሄክታር ለም መሬት በሊዝ በመግዛት በጋምቤላ ክልል ስራውን የጀመረው ሳዑዲ ስታር ለተወሰኑ ዓመታት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ቢንገዳገድም ብዙም ሳይቆይ ግን አራት ሺህ ሄክታር ለም መሬት በመጨመር የሩዝ ሰብል ምርቱንና ትርፍ ማካበቱን አጧጡፎታል፡፡ በጠቅላላው ከ2 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ ለም መሬት የወሰደው ሳዑዲ ስታር ከፓኪስታንና ህንድ ያስመጣቸውን ምርጥ የሩዝ ዘሮች በማዳቀል 62 ያህል ምርጥ ዘሮችን አዘጋጅቶ የተወሰኑት ዝርያዎች ለሀገር ውስጥ ገበያ ያሰበ ሲሆን ቀሪዎቹን ምርጥ ዝርያዎቹ ግን ለውጭ ገበያ ለመላክ እንዳሰበ መረጃዎች ይገልፃል፡፡ ሩዝ ምርቱን እስካሁን ከሀገር ውስጥ ገበያ አልፎ አንድም ፍሬ ሩዝ ለውጭ ገበያ እንዳላቀረበ የሚከራከረው ሳዑዲ ስታር በመጭዎቹ ሁለት ዓመታትም 100 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግና 21 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው የመስኖ ቦይ በመገንባት ዓመታዊ የሩዝ ምርቱን 140 ሺህ ቶን ለማድረስ ማቀዱን የፋይናንሻል ታይምስ ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡ ይህም የኢትዮጵያን ዓመታዊ የሩዝ ፍላጎት ማሟላት የሚችል የምርት መጠን ያህል እንደሆነ ይገመታል፡፡ ሳዑዲ ስታር መስኖ ውሃ የሚጠልፈው በሩሲያ ዕርዳታ በደርግ ጊዜ በአልዌሮ ወንዝ ላይ ከተገነባው ትልቁ አልዌሮ ግድብ ነው፡፡

በኢትዮጵያ በተበጣጠሱ ማሳዎች ላይ የሚመረተው የምግብ ሰብል 80 በመቶው ለአምራቾቹ ፍጆታ ብቻ የሚውል ሲሆን ቀሪው 20 በመቶ ብቻ ለገበያ እንደሚቀርብ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሰፋፊ እርሻዎች የሚያመርቱት ምርት ድርሻ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርቱ አምስት በመቶ ብቻ ነው፡፡ አሁን መንግስት ሁለት ምርጫዎች ያሉት ይመስላል፡ አንድም የእስካሁን አፈፃፀሙን ገምግሞና አሰራሩን አስተካክሎ አነስተኛ መጠን ያላቸውን መሬቶች መስጠቱን ሊቀጥል ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች አቅም እስኪዳብር ድረስ ለም መሬትን ለውጭ ባለሃብቶች መስጠት ጭራሹን ሊያቆም ይችላል፡፡ ወደ ስራ መግባት ባልቻሉት ኢንቨስተሮች ላይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደጀመረው ውል የመሰረዝና መሬቱን የማስመለስ ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ስኬታማነታቸው እየተነገረላቸው ያሉት እንደ ሳዑዲ ስታር ዓይነቶቹ ግን ትርፍ ማፈሳቸውን ይቀጥላሉ፡፡