NBE(ዋዜማ ራዲዮ)-እርግጥ ነው አገሪቱ እንዲህ በዶላር በተጠማች ጊዜ ሁሉ እስክስታ የሚወርዱ ዜጎች አይጠፉም፡፡ በመከላከያ፣ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ ኢህአዴግ በሚቆጣጠራቸው የቤተሰብ ድርጅቶች እንዲህ ዶላር ሲጠፋ ሰርግና ምላሽ ይሆንላቸዋል፡፡ ይህ ወቅት በአንበሳና ወጋገን ባንክ ዙርያ የተጠለሉ ከጥቂት ባለሥልጣናት ጋር በሽርክና የሚነግዱ ‹‹የንጉሣዊያን ቤተሰቦች›› ብዙ ዉስኪ የሚያስወርዱበት፣ ብዙ ሻምፓኝ የሚራጩበት ወቅትም እንደሆነ ይነገራል፡፡ እነዚህ የዶላር ወረፋ ሲይዙ አንድም ቀን አይታዩም፡፡ ‹‹ኤልሲ›› ሲከፍቱ ተመለከትኩ የሚልም የለም፡፡ ነገር ግን እቃቸው ከደረቅ ወደብ ወደ መጋዘን በገፍ ሲጋዝ ብሎም ወደ ገበያ ወጥቶ በሽሚያ ሲሸጥ ይታያል፡፡ ‹‹ዶላሩን ያያችሁ…›› የሚለው መዝሙር የማይመለታቸው እነዚህ አንደኛ ደረጃ ዜጎች በእንደዚህ አስቸጋሪ ጊዝያት ብዙ ቤተሰቦቻቸውን ወደ ሚሊየነርነት ያሸጋግራሉ፡፡

[ከአዲስ አበባ የደረስንን ጦማር ሙሉ ጥንቅር እነሆ አድምጡልን- በንባብም ትዘልቁት ከሆነ ከታች አኑረነዋል]

 

 

አሸብር ጌታሁን-ለዋዜማ ራዲዮ

የመርካቶ አስመጪዎች የሰሞኑ ገጽታ ‹‹ዱቤ ነገ እንጂ ዛሬ የለም!›› ከሚለው ፖስተር ጎን የሚሰቀለውን በዱቤ ነግዶ የከሰረ ነጋዴን ምስል ያስታውሰናል፡፡ በመርካቶና አካባቢዋ አገጩን ተደግፎ ያልተከዘ ነጋዴ የለም፡፡ መርካቶዎች ዶላር ተርበዋል፡፡ ከእነርሱ በላይ ደግሞ አገሪቱ ዶላር ተጠምታለች፡፡ የብሔራዊ ባንኩ ገዢ ከሰሞኑ ይህንን ሐቅ ሙልጭ አድርገው ቢክዱም መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ይኸው ነው፡፡ ዶላር የለም፡፡ መርካቶ እያዛጋች ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት እንደሸንበቆ እየተምዘገዘገ የነበረው የገቢ ንግድ ከሰሞኑ እንደ ሙቀጫ መንከባሉ የምንዛሬ ክምችት የመመናመኑ አንድ ማሳያ ነው ሲል ቀጣዩ ዘገባ ይሞግታል፡፡

©©©
በዉብ የኪነ-ሕንጻ ጥበብ የታነፀው ክቡ ወርቃማው ባንካችን ብሔራዊ ባንክነቱን ትቶ ወደ ንግድ ባንክነት ከተቀየረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ክብነቱን ተከትሎ ታዲያ ሁልጊዜም የደንበኛ እሽክርክሪት አይለየውም፡፡ ሁለተኛ ፎቅ ላይ የሚገኘው መስኮት ቁጥር 69 ሲደረስ ታድያ እሽክርክሪቱ አዙሮ ይደፋል፡፡ አንዳንዶች ይህን መስኮት ‹‹የነፍስ ዉጭ- ነፍስ ግቢ›› መስኮት በሚል ይጠሩታል፡፡ ቪዛ የያዙ ዜጎች ዘወትር የሚሻኮቱበት ይህ መስኮት እያነቡ ጭምር ዶላር የሚለማመኑ ኢትዮጵያዊያንን በየዕለቱ ያስተናግዳል፡፡ መስኮት 69 ለሕክምና ወደ ዉጭ የሚጓዙ ዜጎች የሚስተናገዱበት የምጽዋት በር ነው፡፡
በዚህ ዴስክ የተመደቡ የንግድ ባንኩ ሠራተኞች ከደንበኛ ጋር ነጋ ጠባ መነታረክ ስልችት እንዳላቸው መገመት አያዳግትም፡፡ በየትኛውም የሥራ ሰዓት ግንባራቸውን ከስክሰው ይታያሉ፡፡ ለሚጠየቁት ጥያቄ የተብራራ መልስ ከመስጠት ይልቅ በምልክት ማውራትን ይመርጣሉ፡፡

ዶላር ፈላጊ ሁሉ ቪዛ የተመታበት ፓስፖርት፣ የተረጋገጠ የጉዞ ትኬት፣ የንግድ ባንኩ ደንበኛ መሆኑን የሚመሰክር የባንክ ደብተር፣ እንዲሁም የዉጭ ምንዛሪ መጠየቂያ ፎርም በጥንቃቄ ወደ መስኮቱ 69 አንዲያቀርብ ይገደዳል፡፡ ይህን ካላደረገ የሚሰማው ሰው የለም፡፡ ወደ ዉጭ ለሕክምና የሚሄዱት ደግሞ ከጤና ጥበቃ ሚኒስትር ማረጋገጫ ወረቀት፣ የጥቁር አንበሳ የሜዲካል ቦርድ የዉሳኔ የምስክር ወረቀት አያይዘው ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ በመስኮቷ ዉስጥ ያሉ ኃላፊዎች እነዚህን ዶክመንቶች ፈትሸው በተሞላው ፎርም ላይና በተጓዡ ፓስፖርት የመጨረሻ ቅጠል ላይ እያመነቱም ቢሆን ማኅተም ይመታሉ፡፡ በዚህ መስኮት የዉጭ ምንዛሪን ለማግኘት የሚደረገው ተጋድሎ በአማካይ ከተኩል ሰዓት እስከ አንድ ሰዓት የሚፈጅ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ እንግልት በኋላ የሚፈቀደው የዉጭ ምንዛሪ መጠን ግን ለመጽዋቹም ለተመጽዋቹም አስቂኝ ነው፡፡ አምስት መቶ ዶላር፡፡

በርግጥ ለዉጭ ጉዞ የሚሆን ዶላር ለማግኘት ወደ ግል ባንኮች ሄዶ ማመልከት ይቻላል፡፡ ማግኘት ግን የማይታሰብ ነው፡፡ ‹‹አንዳንድ በዉጭ ምንዛሪ ዴስክ የሚሰሩ የግል ባንከሮች ዶላር ሲጠየቁ ሳቃቸው ይቀድማቸዋል›› ይላል በሥራ ጉዳይ ወደ ቻይና አብዝቶ የሚመላለስ የንግድ ሽርክና ጉዳዮች አማካሪ፡፡ ‹‹እኔ ዶላር ስፈልግ ምንድነው የማረገው መሰለህ….በብዛት ሂልተን ወይም ሸራተን የሚገኙ ባንኮች ጋ እሄዳለሁ፡፡ እነሱ ብዙዉን ጊዜ ለኪስ የምትሆን ዶላር አያጡም፣ ስለሚያዉቁኝም ነው መሰለኝ መቶም ሁለት መቶም ዶላር ጨመር አድርገው ይሰጡኛል›› ይላል ይኸው አማካሪ ተሞክሮዉን ሲያካፍል፡፡
ለአጭር ጊዜ የስልጣና፣ የሥራ፣ የጉብኝትና የትምህርት ቆይታ የሚሄዱ ዜጎች ከአምስት መቶ በለጥ ያለ ዶላር ማግኘት እንዲህ ፈተና ሲሆን በ24 ዓመታት የኢህአዴግ ዘመን ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ ጥቂት ቀደም ያሉ ዓመታትን ተሞክሮ ያየን እንደሆነ በፈረንጆች 2001 ዓ.ም አካባቢ ለተጓዦች አንድ ሺ ዶላር ድረስ ይፈቀድ ነበር፣ በ2009 ደግሞ ማንኛውም ተጓዥ ቪዛ በማሳየት ብቻ እስከ ሦስት ሺ ዶላር መያዝ ይፈቀድለት ነበር፡፡ ከዚህ ከፍ ያለ ገንዘብ ያስፈልገኛል የሚል ተጓዥ ‹‹ትራቭለር ቼክ›› ከአገር ዉስጥ ባንኮች በመውሰድና በሚሄድበት አገር ቼኩን በመመንዘር እስከ 7 ሺ ዶላር ተጨማሪ ገንዘብ መመንዘር ያስችለው ነበር፡፡ ይህ አሰራር ‹‹ለመጭበርበር
የተጋለጠ ነው በሚል›› በዋናነት አገልግሎቱን ይሰጥ የነበረው ‹‹አሜሪካን ኤክስፕረስ›› ህጋዊነቱን እስኪያቋርጠው ድረስ ተጓዦች የዉጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚመርጡት መንገድ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት ብዙም ይፋ ባልሆነ መንገድ ይህ የሦስት ሺ ዶላር ገደብ ወደ አስር ሺ ዶላር ከፍ ተደርጎ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ባለፉት አራት ወራት ዉስጥ የተከሰተው ሁኔታ ግን ለብዙዎች ትንግር ነው፡፡ ከዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ባለቤቶች በስተቀር የሕክምና ተጓዦችን ጨምሮ ዜጎች ከአገር ቤት ይዘው መዉጣት የሚችሉት የዶላር ወይም የዩሮ መጠን ወደ አምስት መቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል፡፡

እርግጥ ነው በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ቀላሉ መፍትሄ ወደ ጥቁር ገበያ ማቅናት ሊመስል ይችላል፡፡ ኾኖም በሕጋዊ መንገድ ከሚሰጠው ዶላር በላይ ገንዘብ ከአገር ይዞ መውጣት ከባድ ወንጀል መሆኑን የሚደነግገው ማስታወቂያ ገና የቦሌ ተርሚናሉን እንደረገጡ በጉልህ እንዲነበብ ተደርጎ ተሰቅሏል፡፡ ክፋቱ ደግሞ ሁልጊዜም በተጓዦች የፖስፖርት የመጨረሻ ቅጠል ላይ በባንክ በሕጋዊ መንገድ የተሰጠው የዶላር መጠን በግልጽ ይጻፋል፡፡ ተጓዡ ዶላር ጠይቆ ያገኘበትን ደረሰኝ አብሮ እንዲይዝ ጭምር ይመከራል፡፡ ከተጠቀሰው ከፍ ያለ ዶላር መያዝ በገዛ ፍቃድ ራስን ለከፋ ችግር መዳረግ የሚሆነውም ለዚሁ ነው፡፡ አስገራሚው ነገር ደግሞ እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ አንዳንድ አገሮች ከወባ ክትባት ማስረጃ ወረቀት ጋር ቢያንስ አንድ ሺ ዶላር የሚሆን ጥሬ ገንዘብ ያልያዙ ጎብኚዎች ወደ አገራችው
እንዳይገቡ ጥብቅ መመሪያ ማስተላለፋቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቦሌ አየር መንገድ የቅድመ በረራ ዴስክ ላይ በሚደረስበት ሰዓት ተጓዡ ‹‹አንድ ሺ ዶላር ወይም ዩሮ›› መያዙን መረጃ እንዲያቀርብ ይገደዳል፡፡ የተጠቀሰውን ገንዘብ ያልያዘ ተጓዥ ከጉዞ የሚስተጓጉልበት አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል፡፡ ‹‹አንድ ሺ ዶላር ስጠኝ›› ሲሉት አፍ አውጥቶ ‹‹የለኝም!›› ያለ መንግሥት ዜጎቹን በር ላይ ጠብቆ ‹‹አንድ ሺ ዶላር ከሌላችሁ ከአገር አትወጡም›› ማለቱ ምን የሚሉት ‹‹አያዎ›› እንደሆነ ለሰሚ ግራ ነው፡፡
©©©
በአጉል ሰዓት የመጣው የምንዛሬ ምች

በዓለም ትልቋ ወደብ አልባ አገር ኢትዮጵያ ከሕዝባዊ ተቃዉሞ ባልተናነሰ የዉጭ ምንዛሪ እጥረት እያነቃት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ነጋዴዎቿ በዶላር እጥረት ምክንያት እጅና እግራቸውን አጣጥፈው ለመቀመጥ ተገደዋል፡፡ አንዳንዶቹም ከዚህ በኋላ በአስመጪነት ብቻ መቀጠል በዚች አገር ነባራዊ ሁኔታ አስተማማኝ እንዳይደለ በመረዳት ወደ ቀላል ገዝቶ የመሸጥ ንግዶች ፊታቸውን እየመለሱ ነው፡፡
ዉስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት የዉጭ ምንዛሬ ፈተናው ከተደራራቢ የመንግሥት ወጪዎች ጋር ተያይዞ የመጣበት ዓመት በመሆኑ መፍትሄው በአጭር ጊዜ የሚመጣ አይደለም፡፡ በቅርቡ ብቻ የስንዴና የአልሚ ምግቦች ግዢ እስከ 7 ቢሊየን ብር ወጪ ኪሱን ያራቆተው መንግሥት ስኳርና ዘይትን ሳይቀር ከዉጭ ገበያ እጅ በእጅ በዶላር ግዢ መፈፀሙ የምንዛሬ ቅርቃር ዉስጥ ሳይከተው አልቀረም፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ከሰሞኑ ጂቡቲ የዕቃ ፍተሻዬን ከእጅ ወደ ማሽን በማሳደጌ በያንዳንዱ እቃ 35 ዶላር ልትከፍሉኝ ይገባል የሚል ደብዳቤ ለኢትየጵያ መንግሥት መላኳንና ይህም በብዙ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቅርቃር ዉስጥ የገባውን መንግሥት ማደናገጡን ሪፖርተር ጋዜጣ በቅርቡ አስነብቧል፡፡ ቀድሞም በምንዛሬ ክምችት እጦት አቅም ያጣው መንግሥት ለጅቡቲ
ድንገተኛ የታሪፍ ጥያቄ ተማጽኖ ለማቅረብ አንድ ልኡክ ወደ ጅቡቲ ለመላክ ዝግጅት ሲያደርግ ነበር፡፡ ከጅቡቲ ሌላ በመንፈቅ ዉስጥ በትንሹ ሦስት ጊዜ ወደ ሳኡድ አረቢያ የተመላለሱት የአቶ ኃይለማርያም ሚኒስትሮች የዶላር እጥረቱን በተመለከተ ትብብር እንዲደረግላቸው አሚሮቹን በቀጥታ መማጸናቸው ተሰምቷል፡፡ ወትሮ ተመሳሳይ ችግር ሲኖር ቀድመው የሚደርሱት ትውልደ ኢትዮጵያዊዉ የሳኡዲ ዜጋ ሼክ ሞሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ከአቶ መለስ ሕልፈት በኋላ እምብዛምም ከሰዎች ጋር ዉስኪ የሚራጩ ሰው አልሆኑም ይላሉ ታዛቢዎች፡፡ ከዚህም አልፎ በሞሮኮ በሚገኘው ሳሚር የነዳጅ ማጣሪያ ጫን ባለ እዳና ኪሳራ ዉስጥ በመዘፈቁ ምክንያት ለአሁኑ የመንግሥት የአድኑኝ ጥሪ እንደከዚህ ቀደሙ ፈጣን ምላሽ ይሰጣሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡

©©©
እንደ ዝናባችን የሚዋዥቀው የመጠባበቂያ ክምችት ኢትዮጵያ

በየትኛውም ወቅት ከዉጭ ምንዛሬ ቅርቃር ወጥታ አታውቅም፡፡ በእርግጥ ሕዝቧ እየጨመረ፣ ምርታማነቷ እየቀጨጨ፣ ወደ ዉጭ የምትልካቸው እሴት አልባ ምርቶች አንድ ሁለት ተብለው ለሚቆጠሩላት ኢትዮጵያ፣ የዉጭ ምንዛሬን ችግር እስከወዲያኛው መፍታት በአንድ ትውልድ የሚያልቅ የቤት ሥራ አይደለም፡፡ ባለፉት 24 ዓመታት አገሪቱን የምንዛሬ ኢሌኖ ያልመታት ወቅት የለም፡፡ የአገሪቱ የመጠባበቂያ ክምችት ከፍና ዝቅ ዘላለሙን ዝናብ እንደሚጠብቀው ግብርናችን በብዙ ዉስጣዊና ዉጫዊ ምክንያቶች የተተበተበ ነው፡፡
ቀጣይና የማይዋዥቅ ሀዋላ፣ በእሴት የደለበ የላኪ ንግድ፣ ቀጥተኛ የዉጭ ኢንቨስትመንት፣ አዎንታዊ የገቢ ወጪ ንግድ ሚዛን፣ ቱሪዝም፣ የሰመረ የአቪየሽን ኢንደስትሪ፣ እርዳታና ጤናማ ብድር ለአንድ አገር የዉጭ ምንዛሬ ክምችት ማደግ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ አላባዊያን ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡ ሆኖም ገና በሁለት አግሩ ያልቆመና ባልሰከነ የፖለቲካ ድባብ ዉስጥ የሚፍጨረጨር እንደ ኢትዮጵያ ያለ ኢኮኖሚ የሚያቁረው የምንዛሬ ክምችት በጥቁር ገበያ በሚሰማ ኮሽታ ሊናድ ይችላል፡፡

ለምሳሌ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የጤና ሁኔታ መታወክና መሞታቸው በተቃዋሚ ሚዲያዎች መናፈስ በጀመረበት በያ ሰሞን የዉጭ ምንዛሬን በኢመደበኛ ሀዋላ መልክ ወደ ዉጭ ማሸሽ በስፋት በመጀመሩ አገሪቱ በከፍተኛ የዉጭ ምንዛሬ ድርቅ ተመታ ቆይታ ነበር፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት በኋላም ቢሆን አገሪቱ አንድም ጊዜ ቢሆን ለሦስት ወር የገቢ ንግድ የሚያበቃ የዉጭ ምንዛሬ ክምችት ኖሯት አያውቅም፡፡ በአመዛኙ ከሁለት እስከ ሁለት ነጥብ ሁለት ወራት የሚያበቃ ክምችት ዉስጥ ስትዋልል ከርማ እፎይ ሳትል ነው የአሁኑ ቀውስ የተፈጠረው፡፡ ከዓለም ገበያ የዩሮ ቦንድ ግዢ በኋላ በነበረው ክምችት ላይ የአንድ ቢሊየን ዶላር ጭማሪ ቢታይም ገንዘቡ በቀጥታ እንዲዉል የታሰበው በዶክተር አርከበ ፊታውራሪነት ለሚገነቡ የኢንደስትሪ ፓርኮች ስለነበር በገቢ
ንግድ ላይ ለውጥ ማምጣት አልቻለም፡፡

ከ2005-2010 ባሉት ዓመታት የገቢ ንግድ የ87 በመቶ ጭማሪ እንደነበረው ግሎባል ሴንተር ኦን ኮኦብፕሬቲቭ ሴኩሪቲ የተሰኘ ዓለማቀፍ ተቋም ያጠናው ጥናት ያስረዳል፡፡ ይህን ያህል ያደገው የገቢ ንግድ 50 በመቶ ይደጎም የነበረውም ዜጎች ከዉጭ በሚልኩት ገንዘብ እንደነበር ያትታል፡፡ ይህ የሚያሳየው ከዉጭ ወደ አገር ቤት የሚላክ ገንዘብ ምን ያህል ኢኮኖሚውን ያግዝ እንደነበረ ነው፡፡ ኾኖም ሳኡዲ በዜጎቻችን ላይ የጅምላ ወከባና የማባረር ዘመቻ ማካሄዷን ተከትሎ ብዙ ሺ ኢትዮጵያዊያን ከስራ መፈናቀላቸው፣ እንዲሁም በሌሎች የአረብ አገሮች ሠርተው ምንዛሬ ወደ አገር ቤት ይልኩ የነበሩ ዜጎች የአረብ አብዮትን ተከትሎ ወደ አገር ቤት መመለሳቸው፣ በመንግሥት ላይ እምነት በማጣት ኢ-መደበኛ የማስተላለፊያ መንገዶች በመዘውተራቸው ወደ በሃዋላ ወደ አገር ቤት የሚገባው ገንዘብ መጠን እየቀጨጨ መመጣቱን ባለሙያዎች ያትታሉ፤ ምንም እንኳ የሃዋላ ገቢ በየአመቱ ጥቅል እድገት ማሳየቱን ቢቀጥልም፡፡

በዚህና በሌሎች ዉስጣዊና ዉጫዊ ምክንያቶች በአሁኑ ወቅት ባንኮች የሚቀርብላቸውን ‹‹የሌተር ኦፍ ክሬዲት›› መተማመኛ ሰነድ ጥያቄ መመለስ ካለመቻላቸው በላይ የአንድ ዓመት ተኩልና ከዚያ በላይ ቀጠሮ ለመስጠት ተገደዋል፡፡ በእንደዚህ አይነት ያልተረጋጉ ሁኔታዎች አስመጪ ነጋዴዎች ‹‹አንዱ እንኳ በተሳካልኝ›› በሚል ቢያንስ ሦስትና ከዚያም በላይ የአስመጪ ፕሮፎርማዎችን ለተለያዩ ባንኮች ያስገባሉ፡፡ ዘንድሮ ግን አንዱም የሚሳካለቸው አልሆነም፡፡ አንድ ፕሮፎርማ ለማስገባት የሚመጣው እቃ ዝርዝርና ዋጋ፣ የዶላር መጠን መጠየቂያ ፎርም፣ ሙሉ ኢንሹራንስ፣ የፍቃድ ሰርተፍኬቶችን አያይዞ ማቅረብን ይጠይቃል፡፡ ተስፋ በመቁረጥ ይመስላል አሁን አሁን ለባንኮች ተጨማሪ የዶላር ጥያቄ ማቅረቡም እየቀነሰና አንዳንዶችም እርግፍ አድርገው እየተዉት እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህን እውነታ የሚያጎላው ወትሮ በሰው የሚጨናነቁት በመርካቶ የሚገኙ የኢንሹራንስ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ዛሬ ዛሬ አንድም ሰው ዝር ሳይልባቸው የመዋላቸው አጋጣሚ ነው፡፡ ‹‹ኮምፒተራቸው ላይ ካርታ ሲጫወቱ እኮ ነው የምታያቸው›› ይላል ሳዲቅ የሚባል የደብተር አስመጭ በኢንሹራንስ ቢሮዎች የታዘበውን ሲያካፍል፡፡

 

ዶላሩ አለ ወይስ የለም?
የዕድሜያቸውን ሲሶ በገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትርነት አሳልፈው፣ በኋላም ለአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው ወድቀው፣ አሁን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ሆነው ላይኛው ቤተመንግሥት የከተሙት አቶ ሶፍያን አሕመድ በአንድ ወቅት ስለ ዉጭ ምንዛሪው እጥረት ተጠይቀው ‹‹የዉጭ ምንዛሪ እጥረት በኔ የሕይወት ዘመን ይፈታል ብዬ አላስብም›› ብለው እቁጩን መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ሰውየው ይህን ይበሉ እንጂ የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ከሰሞኑ ዓይናቸውን በጨው አጥበው ‹‹አገሪቱ ዉስጥ አንዳችም የዉጭ ምንዛሪ ችግር የለም›› ሲሉ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የዜና እወጃ ላይ ቀርበው ተናግረዋል፡፡ ይህ ንግግራቸውን የሰሙ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ‹‹ሰውየው በጤናቸው ነው?›› እንዲሉ አድርገዋቸዋል፡፡

መብራት ሲጠፋ የትራንስፎርመር እንጂ የኃይል እጥረት የለም፣ ዉኃ ሲቋረጥ የብክነት እንጂ የዉኃ እጥረት የለም፣ ስልክ ሲቋረጥ የአጠቃቀም እንጂ የስልክ መቆራረጥ የለም…እያለ ከሕዝብ በተቃራኒ መቆምን ፋሽን ያደረገው መንግሥት ዜጎች የዉጭ ምንዛሪ ለማግኘት በዶላር 3 ብር ማትጊያ ከፍለው እንኳ ሦስት ወራት ወረፋ ለመጠበቅ በተገደዱበት በዚህ ወቅት ‹‹ዶላር ሞልቶ ተትረፍርፏል›› ብሎ መናገር ምን የሚሉት ፈሊጥ ይሆን?

የርሳቸው ሲገርመን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ለመጀመርያ ጊዜ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር በቅርቡ ባደረጉት ቃለምልልስ ‹‹የዶላር እጥረት በታዳጊ ኢኮኖሚ ውስጥ ሁሉም አገራት አልፈውበታል፡፡ ቻይናም በዚህ ዓይነት አልፋለች፤ ኮርያም በዚህ ዓይነት አልፋለች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ይህ እጥረት እንደሚያጋጥም ይታወቃል፡፡ እስከሚያልፍ ያለፋል እንጂ፡፡›› ሲሉ ዶላር በአይኑ ለሚዞረው ሕዝባቸው ሙዚቃዊ ጽናትን ተመኝተዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ይበልጥ አነጋጋሪ የሆነው ደግሞ ‹‹የዶላር እጥረቱን ተከትሎ አንድ ዶላር በ3 ብር ጭማሪ የሚሸጡ የባንክ ኃላፊዎችን ደርሰንባቸዋል›› ሲሉ መናገራቸው ነው፡፡ ይህ ችግር ተብሎ ተብሎ ዘመን ያለፈው ጉዳይ ሆኖ ሳለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ብቅ ብለው እንደ ልዩ ግኝት ‹‹ደርሰንባቸዋል›› ማለታቸው የመርካቶ ነጋዴዎችን በሐዘን ዉስጥ ሆነውም ሳያስቃቸው አልቀረም፡፡ በተለይም ይህን ባሉበት ቃለመጠይቃቸው ንግግር አሳምራለሁ ብለው ‹‹እነዚህን…ጣታቸውን እንቆርጣለን›› ብለው በመናገራቸው በነገታው የዶላር የጥቁር ገበያ ዋጋ ከ3 ብር ወደ 4. ብር ከ25 ሳንቲም ከፍ እንዲል ሆኗል፡፡ አሜሪካን ግቢ የሚገኙ የዶላር መንዛሪዎች በአንድ ሌሊት እንዴት 1.50 ትጨምራላችሁ ሲባሉ…‹‹አንድ ብር ከሀምሳው ለሚቆረጠው ጣታችን ኢንሹራንስ የሚሆን ነው›› ሲሉ መቀለዳቸው አንድ በጉዳዩ የተማረረ አስመጪ ለዚህ ጽሑፍ ፀሐፊ አጫወቶታል፡፡
‹‹ባንኮች ከፍተኛ ብር ላበደሩት የሕይወት ዘመን ደንበኛቸው እንኳ የውጭ ምንዛሬ ማቅረብ አለመቻላቸው የችግሩን ጥልቀትና ስፋት የሚያሳይ ነው›› ይላል ከንብ ባንክ የ13 ሚሊዮን ብር ብድር ያለበትና ወረቀት በማስመጣት የሚተዳደር ወጣት ባለሀብት፡፡ ‹‹አንድ 60 ግራም ሪም ወረቀት 580 ብር ነበር፡፡ አሁን በዶላር እጥረት ምክንያት 770 ብር አስገብተነዋል፡፡ በርግጥ ዋጋው ከምንጩ አልጨመረም፡፡ እኔ ከኢንዶኔዢያ ነው የማስመጣው፡፡ ዋጋው ያው ነው፡፡ ዋጋ የጨመርነው እኛ ነን፡፡ ለምን ጨመራችሁ ብትለኝ ለምሳሌ እኔ 100 ሺ ዶላር ለማግኘት ሦስት መቶ አምሳ ሺ ብር ለባንክ ኃላፊዎች ጉርሻ ሰጥቻለሁ፡፡ ገብቶኃል አይደል? 350 ሺ ብር ማለት እኮ አንድ ቪትዝ መኪና ማለት ነው፡፡ ይሄን ብር ለማካካስ ወረቀቱን አምጥቼ ዉድ ስሸጠው ብቻ ነው፤ ሰሞኑን ጋዜጣ በለው፣ መጽሔት በለው፣ መጽሐፍ በለው ዋጋ በእጥፍ ሲጨምር ታየውና ይገባሀል፡፡ ሲል የዶላር ጥማቱ ወደ ዋጋ ንረት፣ የዋጋ ንረቱ፣ ወደ ኑሮ
ዉድነት የሚያሸጋግሩ ድልድዮች እንደሆኑ ያስረዳል፡፡ ‹‹ለነገሩ አሁን የትኛውንም ዓይነት ጉርሻ ለባንክ ሠራተኛ ብትሰጥም ዶላር አታገኝም፣ እኔ በደህና ጊዜ ያገኘሁት ነው›› ሲል የችግሩን ጥልቀት ያብራራል፡፡
©©©
ክምችቱን ምን ሸረሸረው?
አንድ አገር አነስተኛ የዶላር ክምችት አላት የሚባለው የሁለት ወራትን የገቢ ወጪን ከሚሸፍን ክምችት ያነሰ የዶላር ክምችት ሲኖራት ነው፡፡ አነስተኛ የዶላር ክምችት አገራት ወደ ምጣኔ ሐብት ቀውስ እየገቡ እንደሆነ ተደርጎ እንዲታሰብ የሚያደርግ የኢኮኖሚክስ እኩይ ምልኪ ነው፡፡ የዶላር ክምችቱ ለሁለት ወራት ብቻ የሚበቃ ሆኖ ሲቆይ አገራት ለመድኃኒትና ሌሎች በሕይወት ለመቆየት እጅግ አስፈላጊ ለሆኑ ገቢ እቃዎች ብቻ ዶላር መፍቀድ ይጀምራሉ፡፡ የቅንጦት እቃ ለሚባሉ ገቢ ሸቀጦች የሚዉል ዶላር መጠየቅ በዚህ ወቅት እንደቅንጦት ይቆጠራል፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ላሉና ከመርፌ ቁልፍ ጀምሮ እስከ ከባድ ተሸከርካሪ ድረስ ሁሉም ነገር በዉጭ ምንዛሪ ከዉጭ የሚሸምቱ አገራት በዚህ ወቅት ከፍ ያለ ፈተና ላይ ይዘፈቃሉ፡፡ በተለይም የዉጭ ምንዛሪ የሚያዝገኙላቸው በጣት የሚቆጠሩት ምርቶች በዓለም ገበያ ዋጋቸው መቀነሱ ፈተናቸውን ያበዛዋል፡፡ የኢትጵያ ገቢ ንግድ ከ2010 ጀምሮ ከነበረበት 8 ቢሊየን ዶላር ተነስቶ በየአመቱ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን በ2013 ወደ 13 ቢሊየን ዶላር ደርሶ እየተጠናቀቀ ባለው የፈረንጆች ዓመት የመጀመርያ 6 ወራት ብቻ 8 ቢሊየን ዶላር መድረሱን ከብሔራዊ ባንክ የተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡አመታዊው የተዛባ የንግድ ሚዛን (ኔጌቲቭ ትሬድ ባላንስ) አማካይ መጠን ላለፉት ዓመታት 2 ቢሊየን ዶላር የነበረ ሲሆን በያዝነው ዓመት ግን ወደ አራት ቢሊየን ዶላር ደርሷል፡፡

በአንጻሩ የወጪ ንግድ ትልቅ ተስፋ ቢጣልበትም በተለያዩ ዓለማቀፍ እውነታዎችና የዉስጥ ማነቆዎች እንደታሰበው ሊያድግ አልቻለም፡፡ ለምሳሌ ብዙ የተወራለት የአምስት አመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማብቂያ ላይ የአገሪቱ ጠቅላላ የወጪ ንግድ 3.5 ቢሊየን ዶላር በታች ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በዚያው ዓመት የአገሪቱ የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛን ከዜሮ በታች አስር ቢሊየን ዶላር (-10 ቢሊየን ዶላር) ደርሶ ነበር፡፡ ይህ በእድገት ሰረገላ እየገሰገሰች ነው ለምትባል አገር እንደ መርዶ የሚነገር መጥፎ ዜና ነው፡፡ ለዚህ ከፍተኛ የወጪ ንግድ ዉድቀት የዓለም ገበያ እንደምክንያት ይወሰድ እንጂ አገሪቱ ወደ ዉጭ የምትልካቸው ጥራጥሬዎችና የቅባት እህሎች፣ ሌጦና ቡና ብቻ መሆናቸው ሁልጊዜም ገዢዎቻችን ዋጋ እንዲያወጡልን የሚያደርግ ነው፡፡ አገሪቱ በአንድ ወቅት ተስፋ ያደረገችበት የአበባ ምርትም ከዓመት ዓመት እየጠወለገ እንጂ እየፈካ አልመጣም፡፡

አገሪቱ የገባችበትን የምንዛሬ ማጥ ተከትሎ የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ከፍተኛ የቦርድ አመራሮች ከወራት በፊት መታገዳቸው የመተማመኛ ሰነድ (ኤልሲ) አከፋፈት ጋር በተገናኘ አንዳንድ የቻይና ካምፓኒዎች ገዋንዙ ተነስተው አዲስ አበባ ብሔራዊ ባንክ ድረስ በመምጣት ባቀረቡት አቤቱታ እንደሆነ ተዘግቧል፡፡ የባንኮቹ ኃላፊዎች ኮሚሽናቸው አጓጉቷቸው ዶላር በቅርቡ ይገባልናል በሚል እሳቤ ብቻ ለነጋዴዎች ኤልሲ ከከፈቱ በኋላ በሚፈለገው ፍጥነት ያ ሳይሆን በመቅረቱ የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ ችግሩን ተከትሎ በውጭ የሚገኙ እቃ አቅራቢዎች ለተወሰኑ ባንኮች ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት መጀመራቸው ተዘግቧል፡፡ ‹‹ከብርሃን ባንክ ኤልሲ ከፍቼ ቻይናዎቹ አልቀበልም ብለውኝ ያውቃሉ›› ይላል በዋናነት ደብተር በማስመጣት የሚተዳደረው ሳዲቅ፡፡

ሁሉም ባንኮች ዉስጥ ዶላር የለም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ባንኮች ለአንዳንድ ደንበኞቻቸው መቼም ቢሆን የሚለግሱት ዶላር አያጡም፡፡ እንደ አምባሰል፣ ዲንሾ፣ መሶቦና ጉና የመሳሰሉ የገዢው ፓርቲ የንግድ ሱቆች እንዳሁኑ የዶላር እጥረት በሚከሰትበት ወቅት በአምባሰል ቅኝት መዝፈን የሚያምራቸውም ለዚሁ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ዶላር በመጠነኛ ገደብ ቅድሚያ እንዲያገኙ ስለሚደረግ አዳዲስ ባለሐብቶችን ለመፍጠር የተመቻቸ አውድ ይፈጥርላቸዋል፡፡

ችግሩ ሙሉ በሙሉ የሚቀረፍበት ጊዜ ቅርብ አይመስልም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጋዜጠኞች ‹‹እንዲህ አይነት ሁኔታ ሁልጊዜም በመጀመርያው ሩብ አመት ይገጥመናል›› ሲሉ ችግሩ ጊዝያዊ እንደሆነ ለማመላከት ሞክረዋል፡፡ የዶላር ክምችቱ መሸርሸር እርሳቸው እንደሚሉት ጊዝያዊ ችግር ብቻ አይመስልም፡፡ አመታትን ሊሻገር የሚችልበት እድል ሰፊ ነው፡፡ ምናልባት ቀጥተኛ የወጭ ንግድ በተወራለት ስፋትና ትኩረት መሳብ ከተቻለ ችግሩ እየቀለለ መምጣቱ አይቀርም፡፡
ለአምራች ኢንደስትሪው በልማት ባንክ በኩል እንዲደርስ በሚል ባንኮች ከሚያበድሩት መጠን 27 በመቶ ቦንድ እንዲገዙ ተደርጎ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ብቻ 45 ቢሊየን ብር መሰብሰብ ተችሏል፡፡ ይህ ላለፉት አምስት ዓመታት የቀጠለ ሲሆን መንግሥት ገንዘቡን በማኑፋክቸሪንግ ለሚሳተፉ ባለሀብቶች አበድሬ የወጪ ንግዴን በከፍተኛ ደረጃ አሳድጋለሁ ብሎ ከያዛቸው እቅዶች እንደዋናው የሚጠቀስ ነው፡፡ ሆኖም አምራች ኢንደስትሪው አሁንም ከዛቻና ቀረርቶ ያለፈ ትርጉም ያለው ለውጥ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ለማምጣት የሚያስችል ቁመና ላይ አልደረሰም፡፡ በቅርቡም ይደርሳል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ አምራቾች ትርፍ በዶላር መዛቅ ከመጀመራቸው በፊት መጀመርያ ዶላር ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ጥሬ እቃዎችን በሚፈልጉት መጠን ማስገባት ሳይችሉ ደካማውን ኢኮኖሚያችንን ሊደግፉት አይችሉምና፡፡

የዶላር እጥረቱን ተከትሎ ተራ አስመጪ ነጋዴዎች እሮሯቸውን በስፋት ያሰሙ እንጂ በተገቢው ሁኔታ ተስተጋብቶላቸው አያውቅም፡፡ ይህም የሆነው አምራቾች ፖለቲካዊ ትርጉሙን በመፍራት ስለ ምንዛሬ እጥረቱ ለመናገር ባለመድፈራቸው ነው፡፡ በቅርቡ የቴክኖ ሞባይል አምራች የሆነው ካምፓኒ ‹‹ፈተና ዉስጥ ገብቻለሁ፣ ሰራተኞቼን ያለ ስራ እየቀለብኩ ነው›› በሚል በሳምንታዊው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ፈራ ተባ እያለም ቢሆን ይፋ መግለጫ መስጠቱ የችግሩን ስፋት ጠቆም ያደረገ ጉዳይ ሆኖ አልፏል፡፡ ምንም እንኳ አሁን ባለው አሰራር ለወጪ ንግድና ለአምራች ፋብሪካዎች የዶላር ጥያቄ ቅድሚያ የሚሰጥ አሰራር ቢዘረጋም እጥረቱ ስር የሰደደ ከመሆኑ ጋር እንቅፋቶች መግጠማቸው እየተሰማ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በፈረንጆች ሕዳር 2009 የተከሰተውን የዶላር እጥረት ተከትሎ ኮካ ኮላ ምርት ማቆሙ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ለምርት ማቆም የዳረገው ቆርኪ በዉጭ ምንዛሬ ተገዝቶ ከዉጭ የሚገባ ጥሬ እቃ በመሆኑ ነበር፡፡ በወቅቱ አንድ ሺ የሚሆኑ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሰራተኞቹን የግዳጅ እረፍት እንዲወስድ አድርጎም ነበር፡፡ በዚያው ዓመት የሐረር ቢራና ሐኪምስታውት ምርቶች በተመሳሳይ ምክንያት እንዲቆሙ መደረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡

በዘንድሮው የዉጭ ምንዛሬ እጥረትም እንደ ቴክኖ ሞባይል ያሉና ምርታቸውን ወደ ጎረቤት አገራት ጭምር የሚልኩ ድርጅቶች ምርት ለማቆም መገደዳቸው መዘገቡ ለአምራች ኢንደስትሪው ክፉ ጊዜ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ ሰሊጥና ሌሎች የቅባት እህሎች በዓለም ገበያ ዋጋቸው ዝቅ በማለቱና ከቡና የሚገኘው ትርፍ አዋጪ አለመሆኑ ላኪዎች ምርቶቻቸውን በርካሽ ዋጋ ለዓለም ገበያ እንዲያቀርቡ እንዳስገደዳቸው ይነገራል፡፡ ኪሳራቸውን የሚያካክሱትም በኪሳራ ከሸጡት የዉጭ ንግድ ባገኙት ዶላር በአስመጪ ፍቃድ መልሰው ሌሎች ቁሶችን ወደ አገር ዉስጥ አስገብቶ በመሸጥ ነው፡፡
ላኪዎች የዉጭ ምንዛሪ ቅድሚያ ማግኘት ስለሚችሉ እሴት አልባ ምርቶቻቸውን በኪሳራ ወደ ዉጭ በመላክም፣ ከዚህ የሚገኘው ዶላር መልሶ በመሸጥ ወይም በዚያው በተገኘው ዶላር ገቢ እቃ በመጫን ሞቅ ያለ ትርፍ ማጋበስ አስችሏቸዋል፡፡ ይህም ብዙ እቃዎች በአንድ ጊዜ የዋጋ ጭማሪ እንዳያሳዩ ማድረጉን ነጋዴዎች ይስማማሉ፡፡ ‹‹ላኪዎች በዚህ መንገድ እቃ ቶሎ ቶሎ ማስገባት መቻላቸው፣ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ መውረዱና በአቋራጭ ዶላር የሚያገኙና ከባለሥልጣናት ጋር በሽርክና የሚነግዱ ሰዎች በብዛት ባይኖሩ ኖሮ እስካሁን በእቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት በተከሰተና አገሪቱም ወደከፋ ፈተና በገባች ነበር›› ይላሉ ለጉዳዩ ቅርበት የላቸው የማክሮኢኮኖሚ አዋቂዎች፡፡
እርግጥ ነው አገሪቱ እንዲህ በዶላር በተጠማች ጊዜ ሁሉ እስክስታ የሚወርዱ ዜጎች አይጠፉም፡፡ በመከላከያ፣ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ ኢህአዴግ በሚቆጣጠራቸው የቤተሰብ ድርጅቶች እንዲህ ዶላር ሲጠፋ ሰርግና ምላሽ ይሆንላቸዋል፡፡ ይህ ወቅት በአንበሳና ወጋገን ባንክ ዙርያ የተጠለሉ ከጥቂት ባለሥልጣናት ጋር በሽርክና የሚነግዱ ‹‹የንጉሣዊያን ቤተሰቦች›› ብዙ ዉስኪ የሚያስወርዱበት፣ ብዙ ሻምፓኝ የሚራጩበት ወቅትም እንደሆነ ይነገራል፡፡ እነዚህ የዶላር ወረፋ ሲይዙ አንድም ቀን አይታዩም፡፡ ‹‹ኤልሲ›› ሲከፍቱ ተመለከትኩ የሚልም የለም፡፡ ነገር ግን እቃቸው ከደረቅ ወደብ ወደ መጋዘን በገፍ ሲጋዝ ብሎም ወደ ገበያ ወጥቶ በሽሚያ ሲሸጥ
ይታያል፡፡ ‹‹ዶላሩን ያያችሁ…›› የሚለው መዝሙር የማይመለታቸው እነዚህ አንደኛ ደረጃ ዜጎች በእንደዚህ አስቸጋሪ ጊዝያት ብዙ ቤተሰቦቻቸውን ወደ ሚሊየነርነት ያሸጋግራሉ፡፡

ወጪ የማይፈራው መንግሥታችን
የኢኮኖሚ ተንታኞች የኢትዮጵያን በሰፋፊ ፕሮጀክቶች ክፉኛ መጠመድ አዲስ ቢጫ ፊኛ ተገዝቶለት ባሉኑ እስኪፈነዳ ድረስ በሚነፋ ሕጻን ይመስሉታል፡፡ የሕዳሴው ግድብ መቶ ቢሊየን ብር ይፈልጋል፣ 10 የስኳር ፕሮጀክቶች በድምሩ አንድ መቶ ቢሊየን ብር ይፈልጋሉ፣ የቀላል ባቡሩ ፕሮጀክት ግማሽ 8 ቢልየን ብር ወስዷል፤ የአገር አቋራጭ የባቡር ፕሮጀክቱ 25 ቢሊየን ብር ይፈልጋል፣ የቦሌ ተርሚናል ማስፋፊያ 8 ቢሊየን ብር ጨርሷል፣ ፋይናንስ እየተፈለገለት የሚገኘው የአፍሪካ ትልቁ የአቪየሽን ከተማ 84 ቢሊየን ብር .ይፈልጋል፡፡ ተክለብርሃን አምባዬ ከመከላከያ ጋር በጋራ እየገነቡት የሚገኘው የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ከሕዳሴው ግድብ ቀጥሎ ትልቁ
የአገሪቱ ግዙፍ ፕሮጀክት ሲሆን 16 ቢሊየን ብር ይከሰከስበታል፡፡ የቅየሳ ሥራው የተጀመረው የግልገል ጊዜ አራት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ምንም እንኳ የራሱን የፋይናንስ ምንጭ ሳሊኒ እንደሚያመጣ ቢጠበቅም ከፍ ያለ ቢሊየን ዶላር ይፈልጋል፡፡ በዉድነታቸው የሚታወቁት ታዳሽ የንፋስ ኃይል ማመንጫዎች ማለትም አዳማ፣አሸጎዳ፣ አይሻና አዳማ 2 እንዲሁም አሰላ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች አገሪቷን ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ጠይቀዋታል፡፡

ከዶላር እጥረቱ ጋር ነገሮች ወደ ከፋ ደረጃ እንዳያመሩ ከተፈለገ ይላሉ ባለሞያዎች፣ ‹‹መንግሥት ያለ አቅሙ የጀመራቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጨክኖ ማርገብ ይኖርበታል፡፡›› በእርግጥ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማቆም የራሱን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ዋጋ ማስከፈሉን አይዘነጉትም፡፡

በኪራይ የሚገኙ ማሽነሪዎች፣ ከዓለማቀፍ ገንቢዎች የተገቡ ዉሎች ፕሮጀክቶቹ ለአፍታ እንዲቆሙ ሲደረግ መንግሥትን ላልተፈለገ ሌላ ወጪ እንደሚዳርጉት እሙን ነው፡፡ ቢያንስ ለፖለቲካ ፍጆታ እየተባለ የሚደረጉ የግንባታ ስምምነቶች ግን ጋብ ሊሉ ይገባል፡፡ ይህ ታዲያ ‹‹በዓለም ቁጥር አንድ ልማታዊ መንግሥት ነኝ›› ብሎ ራሱ ላይ የጵጵስና አክሊል ለደፋ ፓርቲ ቀላል ዉሳኔ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም፡፡