Ginbot 20እንዴት ናችሁልኝ የዋዜማ ታዳሚዎች? እኔ ያው ደኅና ነኝ፡፡

እነሆ ጣሊያን ከሄደ ስንትና ስንት ዓመቱ! እኔ ግን ለምን እንደሆን አላውቅም ቅኝ እየተገዛሁ ይመስለኛል፤ የገዢዎቼን ልደት ለ25ኛ ጊዜ ተንበርክኬ ማክበሬ የፈጠረው ስሜት ይሆን? የደመኛዬን ልደት ሻማ ለኩሼ ከበሮ እየደለቅኩ እንዳከብር ስለተገደድኩ ይሆን? ደግነቱ ያበራሁት ሻማ ጥቁር እንጂ ነጭ እንዳልሆነ እኔም እነርሱም ያውቃሉ፡፡ ጥሩነቱ የመልካም ልደት መዝሙሬን በሞት ምኞት ለውሼ እንደምዘምር እኔም እነርሱም ያውቃሉ፡፡

እኔ ምለው! እንዴት ሰው ከአንድ ኋላቀር የአምባገነን ሥርዓት ወደሌላ ዘመናዊ የአምባገነን ሥርዓት የተሸጋገረበትን ዕለት እንዲህ በድምቀት ያከብራል? ደርግ ራሱን ተክቶ  እኮ ነው ያለፈው፡፡ ቁርጥ እሱን! Like Father- Like Son! ትናትና ጓደኞቼ  የሚከተለውን አጭር የጽሑፍ መልዕክት በሞባይሌ ላኩልኝ፤ ‹እንኳን ለ25ኛ ጊዜ ከመስከረም 2 ወደ ግንቦት 20 በሰላም አሸጋገረህ!››

የበዓል አከባበራቸው ሳይቀር እኮ ተመሳሰለ ጎበዝ! ሐኪሞች እንኳን በሽተኞቻችሁን ትታችሁ ግዳጅ ሰልፍ ውጡ ተባሉ ሲባል! ጉድ እኮ ነው! እነዚህ ሰዎች እኮ ዝም ካልናቸው በሽተኞችን ከነጉሉኮሳቸው አያሰለፉም ብላችሁ ነው? ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ!›› ማለት ይሄኔ ነው ጎበዝ፡፡

ዉድ የጦማሬ አንባቢዎች!

ይህንን በዓል እኮ እንኳን እኔ፣ የሥርዓቱ የክፉ ጊዜ ጠባቂና ለዘብተኛው ተቺ አቶ ልደቱም ቢሆኑ  ‹‹ከአንጀቴ አላከብረውም›› ብለዋል አሉ፡፡ ይሄ እንደ ፔንዱለም እየተወዛወዘ የሚያስቸግራቸው ህሊናቸው አልፈቀደውም መሰለኝ ከሰሞኑ ‹‹አሁንስ በዛ›› አይነት ቃለምልልስ ሰጡ የሚባል ወሬ ሰምቼ ተደሰትኩ፡፡ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

ለነገሩ እርሳቸው አፋቸውን ሞልተው በሥርዓቱ አልተጠቀምኩም ሊሉ አይችሉም፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት እኔ እንኳ የማውቃቸው ቢያንስ ሁለት ምን የመሳሰሉ ቪላዎችን ገንብተዋል፡፡ አንድም በቢሾፍቱ፣ አንድም በፊንፊኔ፡፡ እኔ ግን ባለፉት 25 ዓመታት ምን አገኘሁ? ምንም! ምንምን ነው ያገኘሁት፡፡ እንኳን ቤትና ለግንቦት 20 የምለኩሰውን ሻማ ለመግዛት የሚያስችል በቂ ኢኮኖሚ አልገነባሁም፡፡ ለምን በሉኝ! ፈዝዤ! ደንዝዤ….

የመጀመርያውን 10 ዓመት ሥርዓቱ ዲሞክራሲያዊ መስሎኝ በተስፋ ዐይን ዐይኑን ስመለከት አሳለፍኩ፡፡ ሁለተኛውን 10 ዓመት ኮንዶሚንየም ተመዝግቤ ስለነበር ‹‹ነጻነት ባይኖረኝ- ዞሮ መግቢያ ይኖረኛል›› በሚል ተስፋ አሳለፍኩ፡፡ በቀረችው የበካነቸው 5 ዓመት ግን መታለሌ ተገለጠልኝ፡፡ ይኸው ተስፋዬ ተሟጦ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እነሱን በመርገም አሳልፋለሁ፡፡ ይህ ጦማሬም የዚሁ እርግማን አካል ኾኖ እንዲታሰብልኝ ይሁን፡፡

ዉድ የጦማሬ አንባቢዎች!

ከሰላምታዬ ቀጥዬ የማስገነዝባችሁ ነገር ቢኖር ግንቦት 20 ፍሬ ስላፈራላቸው ዜጎች ሕይወትና አኗኗር ይሆናል፡፡

የምር ግን! ግንቦት 20ን ከልቡ የሚያከብራት ማን ነው? አላግባብ የበለፀጉት አይደሉምን?! ያለብቃታቸው ያተሾሙት አይደሉምን? እንዲያውም ሰዎቹን የሆዳቸውን ብንሰማቸው እንዲህ የሚሉ ይመስለኛል፡፡ ‹‹እኛ ሕዝቡ ይህን ያህል ጭቆናን የሚታገስ መሆኑን መቼ አወቅን››፣ ወይም ደግሞ ‹‹እኛ ሕዝባችን እንግዳ አክባሪ እንጂ አምባገነን አምላኪ መሆኑን መች ጠረጠርን”

በቆራጡ መሪ ተይዞ የነበረውን ሪከርድ በ8 ዓመት እኮ ነው ያሻሻሉት፡፡ የኢህአዴግ ሥልጣን የዛፍ ላይ እንቅልፍ ነው አሉ! ድንቄም የዛፍ ላይ እንቅልፍ፡፡ 25 ዓመታት ዛፍ ላይ እንቅልፍ ብሎ ነገር አለ እንዴ? በዚህ ዘመን የዛፉ  እድሜ ራሱ ከ24 ዓመት ይበልጣል ብላችሁ ነው!? ቀበሌ ይቆርጠዋል እኮ!

አንድ ለሚኒስትር ደመቀ የሩቅ ቤተሰብ የሆነ ወዳጄ እንደነገረኝ ‹‹ሰውየው ጧት ጧት ከእንቅልፋቸው በተነሱ ቁጥር ‹‹እኔ አላምንም! ወላሂ…እኔ አላምንም›› እያለ ሳሎኑን ይዞሩት ነበር አለኝ፡፡ ለምን ስለው ‹‹ደሜ በሕይወቱ አንድም ቀን የዚች አገር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እሆናለሁ ብሎ አስቦ አያውቅም ነበር፡፡ የረዥም ዘመን ሕልሙ በቻግኒ የአንድ ሃይስኩል ዳይሬክተር ሆኖ ማገልግል ነበር፡፡›› አለኝ፡፡ ብዙም አልተገረምኩም፡፡

ዉድ አንባቢዎቼ

የሰዎቹን የሰሞኑን የግንቦት 20 አከባበርን ቆም ብለን የተመለከትን እንደሆነ ብዙ የሚነገርን ነገር አለው፡፡ በየአውራጃውና ቀበሌው የሐዘን የሚመስል ድንኳን በመቀለስ መሆኑ ለኔ ‹‹እያነቡ እስክስታ›› ዓይነት ትርጉም እየሰጠኝ መጥቷል፡፡ ነገሩን ከልብ ካጤናችሁት የሩብ ምዕተ ዓመት የሥልጣን ድግስ እኮ አይመስልም፡፡ የሙት ዝክር ነው የሚመስለው፡፡ በመፈክር የተላዘዙ ሀይገር አውቶቡሶች ወደ ስቴዲየም ሲተሙ ዓይቼ ሙት አጅበው የሚሄዱ መስለው ታዩኝ፡፡ ከምሬን እኮ ነው፡፡

ለነገሩ አንዳንድ ነገን ማየት የቻሉ የገዢው ርዝራዦች ከዚህ በኋላ ብዙ ርቀት የመጓዙ ነገር እያከተመለት እንደሆነ ዉስጣቸው ሳይነግራቸው አልቀረም፡፡ ከዚህ በኋላ ሕዝቡ የቱንም ያህል ታጋሽና ለጭቆና የተመቸ ቢሆንም ኢኮኖሚውና ማኅበራዊ ምስቅልቅሉ ብዙም እንደማያዘልቃቸው አላጡትም፡፡ ሻንጣቸውን መሸከፍ የጀመሩም አሉ፡፡ በሜቴክ በኩል ወደ ዉጭ የሚሸሸው ገንዘብ የዚሁ ONE WAY TICKET አካል ይመስለኛል፡፡ አገሪቷን የጠላት ገንዘብ እስክትመስል እየቧጠጧት ነው፡፡ አሁን አሁን በእስያ በዘመድ አዝማድ ስም ቢዝነስ ያልከፈተ ቱባ ባለስልጣን ማግኘት በኢህአዴግ ዉስጥ ዲሞክራሲን እንደማግኘት እየከበደ መጥቷል፡፡

ኦህዴዶች ደግሞ ይብሳሉ፡፡ ኦህዴዶች ዘንድ የሙስናው መጠን እንኳን ለተዘራፊው ለዘራፊውም የሚዘገንን ዓይነት እየሆነ ነው፡፡ ሳር ቤትና የካ ተራራ ላይ የመኖርያ ግብይት ተጧጡፏል፡፡ ንብረት ለመያዝ የሚደረገው ጥድፊያ የኦሮሚያን ሕዝባዊ አመጽ ለማብረድ ከተካሄደው ጥድፊያ ቢበልጥ እንጂ አያንስም፡፡ ተአምር ቢመጣ ከ25 ሚሊየን ብር በላይ የማይሸጥ ቤት 40 ሚሊየን እየቀረበበት ነባር ነዋሪዎችን ‹‹ልቀቁልን›› እያሉ የሚያግባቡ ደላሎች ተፈጥረዋል፡፡ ገዢው ማነው ሲባል ግን ትንፍሽ የሚል ሰው የለም፡፡ እንዲሁ ለአንድ ባለሐብት ‹‹ተፈልጎ ነው›› ይባላል፡፡ በአጋጣሚ ግብይቱ ሊከናወን ዉልና ማስረጃ ተኪዶ ገዢዋ ስትታይ የሆነች ከአጋሮ-ጅማ የመጣች  የገጠር እመቤት ትሆናለች፡፡ ፊርማ በጣት የምትፈርም የወለጋ ሴት ታጋጥማለች፡፡ ይህ እንዴት ይሆናል ሲባል ‹‹ከጀርባዋ ኦህዴዶች አሉ›› የሚል ጭምጭምታ ዘግይቶ ይሰማል፡፡ እንዴ- ምን ያድርጉ ሰዎቹ! ሙሉ ሰበታን፣ ሙሉ ገላንን፣ ሙሉ ሱሉልታን፣ ሙሉ ፉሪን የሸጡ ኦህዴዶች ገንዘባቸውን እንኳን ቤት ገዝተውበት ቢያቃጥሉትስ ያልቃል እንዴ? እውነት እውነት አላችኋለሁ እሳቱ ያልቃል እንጂ ገንዘቡ አያልቅም፡፡

ዉድ የጦማሬ አንባቢዎች!

ሰፊ የቆዳ ስፋት ባላት አገር፣

ለሩብ ምዕተ ዓመት የሕሊና እስረኛ ሆኜ በተረገጥኩባት አገር፣

ተወልጄ ያደኩበትን ቤት በልማት ስም ፈርሶ እንደ ሶሪያዊ ተፈናቃይ በየጉራንጉሩ በተንከራተትኩባት ሸገር፣

አንድ ስቱዲዮ ገንብቶ ለማስረከብ የአንድ ጎረምሳን እድሜ በሚፈጅባት አገር፣

ገዢዎቼ መንፈቅ እንኳ ሳይሞላቸው የተንጣለለ ቪላ-ወፎቅ ገንብተው ለጥብስ አድርሰውት ብመለከት ሆድ ባሰኝ፡፡ እንደኔው ሆድ ለባሳቸው አንባቢዎቼ ጩቤ ከማውሳቸው እነዚህኑ ፎቅ ወቪላ አዳራሾችን በካሜራዬ አስቀርቼ ባሳያቸው መልካም እንደኾሆነ አሰብኩኝ፡፡ ለኔ ይህ የግንቦት 20 ልዩ ገፀበረከቴ ነው፡፡

በሚቀጥለው ሳምንት ጦማሬ ሁሉንም አስቃኛችኋለሁ!

አቦ እስከዚያው አንድ ደኅና ምርቃት ልመርቃችሁ!

የግንቦት 20 በዓል የማይከበርበት ግንቦት 20 ያድርሰን፡፡

አሜን በሉ!

==========

ተጻፈ
በአውግቸው ቶላ
አዲስ አበባ