Adanech Abiebe (L)Mayor of Addis and Shimeles Abdisa (R) president of Oromia region

ዋዜማ ራዲዮ- ከዚህ ቀደም ለከረረ ፓለቲካዊ ውዝግብና ተቃውሞ ምክንያት የነበረው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል አስተዳደራዊ ወሰን አዲስ በተዘጋጀ ጥናት መሰረት የማካለል እንቅስቃሴ መጀመሩን ዋዜማ ከሁለቱም ወገኖች ካሉ ምንጮች ስምታለች::

የወሰን ማካለሉ በሁሉም የአዲስ አበባ ዙሪያ ወረዳዎችና በኦሮሚያ ክልል ስር ባሉ ልዩ ዞኖች መካከል የሚደረግ ሲሆን እንደየአካባቢው ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ አልያም ከኦሮሚያ ወደ አዲስ አበባ የሚካለሉ አካባቢዎች ተለይተዋል።

ማክስኞ ዕለት ከአዲስ አበባ መስተዳድር ምንጮች እንደሰማነው አጠቃላይ የከተማዋ አከላለል ዝርዝር ለገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች  ፣ ለየክፍለከተማና ወረዳ ሀላፊዎች እንዲያውቁት ተድርጎ ወደ ተግባር እንዲገባ መመሪያ ተላልፏል። ለገጣፎ፣ የካ አባዶ ፣ ቦሌ ቡልቡላ ፣ ጆሞ ኮንደሚኒየም ሁለት እስከ ረጲና ወይብላ ማርያም  በአዲሱ አከላለል የወሰን ለውጥ የተደረገባቸው አካባቢዎች  ናቸው። በሰሜን አዲስ አበባ (እንጦጦ)  ከኬላ እስከ ወረዳ 01፣ 06፣ እና 07 ሽግሽግ ይደረጋል።

የወረዳ እና የክፍለ ከተማ አመራሮችም የወሰን ማካለሉ የሚነካቸውን አካባቢ ነዋሪዎች እንዲያወያዩ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል።

ሁለቱን አስተዳሮች በአዲስ ወሰን ለመለየት ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ የሆኑ ምልክቶችን በመጠቀም ጥናት የሰራ አንድ ቡድን ከአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ጋር ከሚዋሰኑ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደሮች ጋር ውይይት ማደረጉንም ዋዜማ ራዲዮ ተረድታለች።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ  ከአዲስ አበባ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ እና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ ከኦሮምያ ደግሞ የገላን ክፍለ ከተማ አመራሮች የተሳተፉበት ስብሰባ ተካሂዶ በጉዳዩ ላይ ውይይት መደረጉን ዋዜማ ስምታለች።።

በማካለሉ ጉዳይ ላይ በቀረበው ጥናት መሰረት ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 በከፊል ወደ ኦሮምያ ይካለላል። ይህ ማለት የቱሉዲምቱ ኮንደሚኒየም በተለምዶ ፕሮጀክት 11 የሚባለው ሰፊ የጋራ መኖርያ ቤት ያለበት አካባቢ ወደ ኦሮምያ ይካለላል። ወረዳ 13ትም በዚህ አካባቢ ርክክብ ለማድረግ እየተዘጋጀ እንደሆነ ከወረዳው አመራሮች ሰምተናል።

በዚሁ ወረዳ አስፓልት ተሻግሮ ያሉት ማለትም የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርቲ እና በተለምዶ ፕሮጀክት 12 እየተባለ የሚጠራው የቱሉዲምቱ የጋራ መኖርያ ቤት አካል የሆነው ስፍራ እንዲሁም አለም ባንክ እየባለ የሚጠራው ሰፈር በአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ እንዲቀጥሉ ተለይተዋል።

በአንድ ወቅት የውዝግብ መንስዔ የነበረው የኮዬ ፈጬ የጋራ መኖርያ ያለበት  ወረዳ 9 ሌላው ከአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወደ ኦሮምያ ክልል የሚካተት ሲሆን የጋራ መኖርያው እና በዙርያው ያሉ አዳዲስ ሰፈራዎች በሙሉ ወደ ኦሮምያ ክልል እንዲገቡ በጥናቱ ምክረ ሀሳብ ቀርቦባቸዋል።። 

በዚሁ ወረዳ ዘጠኝ ሄኒከን ቢራ እና አዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ እና በዚያው ስፍራ ያሉ የቂሊንጦ የጋራ መኖርያ ቤቶች በአዲስ አበባ አስተዳደር ስር ይቀጥላሉ።

በዚሁ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የኮዬ ፈጬ ኮንደሚኒየምን ተከትሎ ያሉት ወረዳ 10 እና 11 እስከ ጎሮ መዳረሻ ድረስ ከአስፓልት በስተ ቀኝ ኦሮምያ ውስጥ እንዲካለሉ በስተግራ ደግሞ አዲስ አበባ አስተዳደር ስር እንዲቆዩ ታስቧል።

የቴክኖሎጂ ዘርፍ አገልግሎትና ኢንቨስትመንት ማዕከል የሆነው አይ ሲቲ ፓርክ አዲስ አበባ ውስጥ ይቀጥላል።

በሌላ በኩል በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ውስጥ የገላን ኮንደሚኒየም እና አካባቢው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ሲቀጥል አስፓልቱን ተሻግሮ በስተ ግራ ያሉ የአባ ሳሙኤል ማረምያ ቤት አካባቢዎች በኦሮምያ እንዲካለሉ ታስቧል።

የወሰን ማካለል ጥናቱ ውስጥ ከዚህ ቀደም በስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈርያት ካሚል መሪነት ጉዳዩን እንዲከታተል ተቋቁሞ የነበረው ቡድን ይሳተፍበት አይሳተፍበት የታወቀ ነገር የለም። በሌላ በኩልም እንዲሁ የወሰን መካለሉ ስራ የሚነካቸው አካባቢዎች በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምርጫ የተከናወነባቸው እንደመሆኑ ጉዳዩ የአዲስ አበባ ምክር ቤት  በሂደቱ ላይ የህዝበ ውሳኔ ይኑር አይኑር እስካሁን የተገለፀ ነገር የለም። [ዋዜማ ራዲዮ]