ዋዜማ ራዲዮ- የሱማሌ ክልል ልዩ ኃይሎች በሱማሊያዋ ባኮል ግዛት ውስጥ “አቶ” በተባለ ወረዳ ትናንት ከአልሸባብ ታጣቂዎች ጋር በድጋሚ እንደተዋጉ የሱማሊያ ዜና ምንጮች ዘግበዋል።

የአልሸባብ ታጣቂዎች በክልሉ ልዩ ኃይል ላይ ሞርታሮችን በመተኮስ ውጊያውን እንደጀመሩ ዘገባዎች አመልክተዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትናንት ማምሻውን ለመንግሥት ዜና አውታሮች በሰጠው መረጃ፣ ቡድኑ በከፈተው አዲስ ውጊያ በድጋሚ ተመቶ መመለሱን እና ከ150 በላይ ታጣቂዎቹ መገደላቸውን ተናግሯል።

አልሸባብ ባኮል አውራጃ በምትገኝባት ሳውዝ ዌስት ክልል ከኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ባይደዋ ከተማ ላይ ትናንት የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት መፈጸሙን የአገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። በጥቃቱ የሳውዝ ዌስት ክልል ፍትህ ሚንስትር ሐሰን ሉግቡር ተገድለዋል።

የአሜሪካው የአፍሪካ ወታደራዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ጀኔራል ስቲፈን ታውንሰንድ የኢትዮጵያ ኃይሎች ሰርጎ ገቡን የአልሸባብ ኃይል በዋናነት እንደመከቱት ገልጸው፣ ሆኖም ግን ቡድኑ በድጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ እንደማይቀር ከትናንት በስቲያ ግምታቸውን ተናግረው ነበር።

አልሸባብ በርካታ ታጣቂዎቹን አሰልፎ ባልተለመደ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት መፈጸሙ፣ ከሱማሊያ ውጭ የኢትዮጵያንም ድንበር ጥሶ መግባት እንደሚችል በተንቀሳቃሽ ምስሎች ጭምር በማሳየት የደጋፊዎቹን እና የታጣቂዎቹን ሞራል ለማነቃቃት ሊሆን እንደሚችል ታዛቢዎች በመግለጽ ላይ ናቸው። ሆኖም የቡድኑ ጥቃት ገና እየቀጠለ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ላይ ማሳካት ያሰበው ዋነኛ እቅዱ ምን እንደሆነ በትክክል ለመናገር ጊዜ ገና ሊሆን ይችላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ አልሸባብ ወደ ኢትዮጵያ ያስገባው ተዋጊ ኃይል፣ ቡድኑ ከቀናት በፊት በ”ይድ” እና “አቶ” የድንበር ከተሞች ላይ በፈጸመው ጥቃት ያልተሳተፈ አዲስ ኃይል እንደሆነ የአልሸባብን ወታደራዊ እንቅስቃሴ የሚከታተሉ ታዛቢዎች ተናግረዋል።

አልሸባብ በኢትዮጵያ ላይ ድንበር ዘለል ጥቃት መክፈቱን የኢትዮጵያ መንግሥት ከገለጸ ቀናት ተቆጥረዋል። ሆኖም ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ የሚመሩት የሱማሊያ ፌደራል መንግሥት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ዝርዝር መግለጫ አልሰጠም። ሱማሊያ የሰሞኑን የቡድኑን የድንበር ላይ ጥቃት ለመመከት የራሷን ጦር ታሰማራ ወይም አታሰማራ እስካሁን የገለጸችው ነገር የለም።

የሱማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ኡመር፣ አልሸባብ ወደ ኢትዮጵያ የላካቸው ተዋጊዎች የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ተወላጅ የሆኑ የቡድኑ ታጣቂዎች መሆናቸውን መናገራቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ሱማሊያ ውስጥ በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ተልዕኮ ሥር እና በሁለትዮሽ ስምምነት ከአልሸባብ ጋር ለዓመታት እየተፋለሙ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች አሏት።

አዲሱ የሱማሊያ ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዛ ባሬ ቃለ መሃላ ከፈጸሙ አንድ ወር ቢያልፋቸውም፣ እስከዛሬው ቀን ድረስ ካቢኔ ማቋቋም አልቻሉም። ይህም ለአልሸባብ ምቹ ሁኔታ ሳይፈጥር እንዳልቀረ ተገምቷል።

አልሸባብ በኢትዮጵያ ላይ ድንበር ዘለል ጥቃት የከፈተው፣ አሜሪካ ልዩ ኮማንዶዎቿን በድጋሚ ወደ ሱማሊያ እንደምትልክ ካሳወቀች እና ፕሬዝዳንት ሞሐመድም የአሜሪካን ውሳኔ በደስታ ከተቀበሉት ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]