ዋዜማ ራዲዮ- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በሁዋላ የደህንነትና ጸጥታ ተቋማት ላይ የአሰራር ማሻሻያ ከማድረግ አንስቶ የተቋማት ሀላፊዎችን ከመቀየር መልሶ እስከማዋቀር የደረሱ ስራዎች እየተሰሰሩ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎንም ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ በሶስቱ ተቋማት ማለትም በብሄራዊ የመረጃና የደህንነት አገልግሎት : በፌዴራል ፖሊስና በመከላከያ ሚኒስቴር ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት በፊት ከበላዮቻቸው ጋር በነበራቸው አለመግባባት ሳብያ ከስራቸው ተባረው የነበሩ ሰራተኞች ጉዳያቸው እየተጣራ እንዲመለሱ እየተደረገ እንደሆነ ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ አረጋግጣለች።

በተለይ በብሄራዊ የመረጃና የደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ውስጥ በነበሩ  አድሎአዊ አሰራሮች ምክንያት በርካቶች ከስራ ገበታቸው ሲባረሩ ሲያልፍም ሲታሰሩ ነበር። በኢኮኖሚ ኢንተሊጀንስ ውስጥ የአለቆቻቸው ኮንቴይነር ወይንም ከአለቆቻቸው ጋር ቅርበት ያላቸው ሰዎች ህገ ወጥ እቃ እንዳይገባ ሲያደርጉ የነበሩ ሙያተኞች እንዲሁም ጸረ ሽብር ላይ የነበሩ የደህንነት ባለሙያዎች ከመመሪያ ውጭ አንሰራም በማለታቸው ብዙዎች ከስራቸው ሲባረሩ ቆይቷል። በፌዴራል ፖሊስና መከላከያ መስሪያ ቤት ውስጥም ብሄር ላይ በተመሰረተ መልኩም ሰራተኞች እየተገሉ ከስራም እንዲገፉ ተደርጎ ነበር።

አሁንግን ሶስቱ መስሪያ ቤቶች በመድሎ ተባረናል ያሉ የቀድሞ ባልደረቦችን ጉዳያቸው  እየተጣራ ወደ ስራ ገበታቸው እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን ሰምተናል።
በብሄራዊ የመረጃና የደህንነት አገልግሎት በርካታ ቦታዎች ላይ የሀላፊዎች መተካካት ተከናውኗል። የአብይ መንግስት መምጣቱን ተከትሎ በተለይ በዚህ መስሪያ ቤት በርካቶች በራሳቸው ፍላጎት የለቀቁና በቁጥጥር ስር የዋሉ እንዲሁም የጠፉ እንዳሉ የሚታወቅ ነው። ከጠፉት መካከል በክልሎች የመረጃና ደህንነት ስራ ሲያከናውኑ የነበሩ ይገኙበታል። [የድምፅ ዝርዝር ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/nYeVyMDNN14