BBC Afaan Oromooየብሪታንያው የዜና አገልግሎት (BBC) የስርጭት አድማሱን የሚያሰፋበትን አዲስ ዕቅድ መንደፉን አሳውቁዋል። በማስፋፍያው እቅድ ላይ በሚዛናዊ የዜና ዘገባ ረገድ የዲሞክራሲ ችግር የሚታይባቸው ናቸው ያላቸውን ጥቂት የዓለም አገራት ለመድረስ የሚያስችሉ በልዩ ልዩ ቁዋንቁዋዎች የሚሰራጩ ፕሮግራሞች የማዘጋጀት ትልም አለው። BBC ስርጭርቱን ሊያስፋፋ ከሚፈልግባቸው የዲሞክራሲ ችግር የሚታይባቸው አገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዱዋ ናት።

ይህ ዜና ከተሰማ በሁዋላ ፕሮግራሙ ሲጀምር ኦሮምኛ ቁዋንቁዋን የስርጭቱ አካል እንዲያደርግ የሚጠይቅ የፌስቡክና የትዊተር ዘመቻ ተኪያሂዱዋል። እስካሁን ድረስ በቀጠለው በድረገጽ የድጋፍ ፊርማ የማሰባሰብ ዘመቻ ክ27 ሺህ በላይ የሚኾኑ ሰዎች የቢቢሲ እቅድ ኦሮምኛን እንዲጨምር በመጠየቅ አቤቱታቸውን አሰምተዋል።   (የመዝገቡ ሀይሉን ዘገባ እዚህ ያድምጡ)


በአፍ መፍቻ ቁዋንቁዋነት ጥቅም ላይ በመዋል ከሌሎች የኢትዮጵያ ቁዋንቁዋዎች ሁሉ የበላይነት ያለው የኦሮምኛ ቁዋንቁዋ በጥቅም ላይ የሚውልባቸው የመገናኛ ብዙኃን ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉት ብቻ ናቸው። የኦሮሞን ሕዝብ ጉዳዮች በአማርኛ ቁዋንቁዋ ያቀርቡ የነበሩ ጥቂት የግል ጋዜጦች የነበሩበትም ዘመን የነጻ ሚዲያውን ጠራርጎ ባጠፋው የመንግስት ተጽዕኖ ምክንያት ታሪክ ከኾኑ ቆይተዋል። በመንግስት የሚሰራጩት የኦሮምኛ ቁዋንቁዋ ሚዲያዎች በሌሎች ቁዋንቁዋዎች እንደሚሰራጩት ሁሉ የመንግስት የፕሮፓጋንዳ መገልገያዎች ናቸው።

ገና ብዙ ሊሰራበት በሚገባው የኦሮምኛ ሚዲያ እጥረት ውስጥ ቢቢሲ በሚጀምረው ኢትዮጵያን ዒላማው በሚያደርግ ዕቅድ ውስጥ የኦሮምኛ ቁዋንቁዋ ፕሮግራም መካተቱ አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም። ይህ በማኅበራዊ ሚዲያና በድረገጽ የተደረገው ዘመቻ የሚያመጣው ተጽዕኖ ምንም ይሁን ምን በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኦሮምኛ ተናጋሪዎች ተጨማሪ የመገናኛ ብዙኃን እንደሚያስፈልጋቸው ያሳየ ወሳኝ መልዕክት ማስተላለፉ በራሱ አንዱ የዘመቻው ስኬት ነው።