ዋዜማ ራዲዮ- በመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹሙ ግድያ የተከሰሰው 10 አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ ህክምና ባለማግኘቱ “ጉዳት የደረሰበት እግሩ ወደ ሽባነት እየተቀየረ” መሆኑን ጠበቆቹ ገለፁ፡፡

ሰኔ 15 ከተደረገው “የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ” ጋር በተያያዘ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ ሽብር እና ህገመንግስታዊ ስርዓት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ችሎት በ13 ግለሰቦች ላይ ክስ መመስረቱ ይታወሳል

የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን የግል አጃቢ የነበረው አስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ፣ አስጠራው ከበደ፣ ሲሳይ አልታሰብ፣ አበበ ፈንታ፣ አስቻለው ወርቁ፣ ተሸመ መሰለ፣ አለምኔ ሙሉ፣ ከድር ሰኢድ፣ የለ አስማረ፣ አማረ ካሴ፣ ፋንታሁን ሞላ፣ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ህዝብ ግንኙነት ሀላፊው ክርስቲያን ታደለ እና ሌላኛው የፓርቲ አባል በለጠ ካሳ የተባሉት እኚህ ተከሳሾች ህዳር 12 2012 ዓም በችሎት ቀርበውም ክሳቸው ተነቦላቸው ነበር፡፡

ተከሳሾቹ በተሰጣቸው ቀጠሮ መሰረትም የመጀመርያ ደረጃ መቃወምያቸውን ዛሬ ለችሎት አቅርበዋል፡፡

1ኛ ተከሳሽ የሆነው እና የመከላከያ ሰራዊት የቀድሞ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ባልደረባቸው ሜጀር ጀነራል ገዛዒ አበራን በሽጉጥ ተኩሶ ገድሏል ሲል አቃቤ ህግ ክስ የመሰረተበት የኢታማዦሩ የግል አጃቢ 10 አለቃ መሳፍንት ጥጋቡ የአቃቤ ህግ ክስ የወንጀል ድርጊቱን በዝርዝር አያስረዳም ብሏል፡፡

በፅሁፍ በቀረበው የተከሳሹ መቃወምያ በተጨማሪም መገለፅ የነበረባቸው ጊዜ እና ቦታዎች አልተጠቀሱም ያለ ሲሆን ጄነራሎቹ የት ቦታ እንደተገደሉም ሆነ የት ቦታ ለማምለጥ ስሞክር ተከብቤ እንደተያዝኩ የተገለፀ ነገር የለም፤ ይህ መሰረታዊ ስህተት ነው ሲል የመጀመርያ ደረጃ መቃወምያውን አስገብቷል፡፡

ቀሪዎቹ ተከሳሾች መቃወምያቸውን በቅድሚያ በጋራ ያቀረቡ ሲሆን በዚህም የአዴፓ አመራሮች እረስ በእርስ ተገዳደልን እያሉ በግልፅ እየተናገሩ ይህን ግልፅ ያልሆነና በፍትህ ስርዓቱ ታሪክ ተደርጎ የማያውቅ እንግዳ የሆነ ክስ ነው ብለዋል፡፡

አክለውም አቃቤ ህግ በክሱ ላይ በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮችን እና በአዲስ አበባ ጄነራሎችን ሰኔ 15 በመግደል የተሳተፉ በማለት በ2 ገፆች ላይ ከመጥቀስ በቀር በዝርዝር አንድም ቦታ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በግድያው ላይ ስለመሳተፋችን የተገለፀ ነገር የለም ብለዋል፡፡

ተከሳሾቹ በተጨማሪም ስለግድያው መንግስት በራሱ ሚዲያ ተቋማት ባለስልጣናት ከገለፀው መግለጫ ውጭ ሊታመን የሚችል በማስረጃ የተረጋገጠ እውነታ የለም ሲሉ በመቃወምያቸው አካተዋል፡፡

ዛሬ በነበረው የችሎት ቆይታ ተከሳሾቹ ከመቃወምያቸው በተጨማሪ ለችሎት አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን 10 አለቃ መሳፍንት በጊዜው በነበረው የተኩስ ልውውጥ ወቅት ጉዳት የደረሰበት እግሩ በፊት በነበረበት ማረፍያ በጦር ሀይሎች ሆስፒታል ህክምናውን የተከታተለ ቢሆንም አሁን ግን የተቋረጠበት በመሆኑ ወደሽባነት እየሄደ ነው ማለቱን ጠበቆቹ ለችሎት አስረድተዋል፡፡

ቀሪዎቹ ተከሳሾችም በበኩላቸው መፀሀፍት ሳንሱር እየተደረጉ ነው የሚገቡት እንደልባችን ማግኘት አልቻልንም ያሉ ሲሆን የአብን ህዝብ ግንኙነት ሀላፊው ክርስቲያን ታደለ በአለርት ሆስፒታል ሲከታተል የነበረውን ህክምና መቀጠል እንዳልቻለ አቤቱታ አቅርቧል፡፡

ከሳሽ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ህዳር 12 በመሰረተው ክስ በመፈንቅለ መንግስት ሙከራው 5 ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ጨምሮ 17 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ 20 የሚሆኑ ላይ ደግሞ ጉዳት መድረሱም ጠቅሶ ነበር፡፡

በዚህም ሁሉም ተከሰሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት በ1996 የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ህግ 32/1/ሀ/ለ፣ 35፣38 እና 238/2/ ሰር የተቀመጠውን ተላልፈዋል በማለት ነው ክሱን ያቀረበው፡፡

ከ2ኛ እስከ 9ኛ ያሉት ተከሳሾችም ከህግ ውጭ ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማፍረስ በማሰብ ከአማራ ክልል መደበኛ የፀጥታ መዋቅር ውጭ የአማራ የስለላ እና የደህንነት ድርጅት (አስድ) የሚል ተቋም መስረተዋል ሲል በክሱ ገልፆ ነበር፡፡

በዚህም ጠላት ተብለው የተፈረጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም ህ.ወ.አ.ት እና ኦዴፓን ለማዳከም እና የሀይል እርምጃ ለመውሰድ የስለላ እና የመረጃ ደህንነት ስልጠና እንዲሁም የተግባር ልምምድ ወስደው ሲንቀሳቀሱ ነበር በማለት ማካተቱ ይታወሳል፡፡[ዋዜማ ራዲዮ]