ዋዜማ ራዲዮ- የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ትናንት በተፈሪ ገረቦሼ፣ያደሳ ዮሴፍ ፣ቡርቃ ኩመራ፣መሀመድ ኢሳ ፣ኤፍሬም ኢያሱ፣ አብዲ ድሪባ እና መርጋ ጉታ ላይ የመሰረተውን የሸብር ወንጀል ክስ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብር ችሎት ክሱን አስነብቧል ።

ተከሳሾች በምስራቅ ወለጋ ከሚንቀሳቀሰው ኩምሳ ድሪባ ወይም ጃልማሮ በሀገር ውስጥ የሸኔ ታጣቂ እና አመራር ጋር ግንኙነት ይፈጥሩ እንደነበር በክሱ ተጠቅሷል።

የጦር መሳርያ እና የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገላቸው በአዲስ አበባ እና ቡራዩ በመንቀሳቅስ አባ ቶርቤ የተባለ እርምጃ ወሳጅ ቡድን ስለማቋቋማቸውም አክሏል።

ይህ ቡድን በመንግስት የስራ ሀላፊዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ በያዝነው ዓመት መስከረም 1 ላይ ከምሽቱ 1ሰዓት ተኩል ገደማ በኦሮምያ ክልል ቡራዩ ከተማ በፖሊስ አባላት ላይ ቦምብ በመወርወር በ9 አባላት ላይ ጉዳት ሰለማድረሳቸው አቃቤ ህግ በክሱ አብራርቷል።

የእያንዳንዱን ተከሳሾች የወንጀል ድርጊት በተናጠል ያስቀመጠ ሲሆን ሁሉም ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት የሽብር ድርጊት ዝግጅት መፈጽም ወንጀልም ፈጽመዋል ብሏል። [ዋዜማ ራዲዮ]