ዋዜማ ራዲዮ- ባለፉት ሁለት የክረምት ወቅቶች ውሀ በያዘው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኋይል ማመንጫ ተርባይኖችን በውሀ የመሞከር ስራ መጀመሩን ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ሰምታለች።

አስቀድሞ የኋይል ማመንጫ ተርባይኖቹ  የተሳካ ደረቅ ሙከራ ተደርጎላቸዋል። የኋይል ማመንጫ የደረቅ ሙከራ የሚባለው የኋይል ማመንጫዎች ተገጥመው መስራታቸው የሚረጋገጥበት የቴክኒክ ሙከራ ነው።

ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮቻችን እንደሰማነው አሁን ሁለቱን የኋይል ማመንጫ ተርባይኖችን በውሀ የመሞከር ስራ እየተከናወነ ነው። ይህም ተርባይኖቹ ውሀን ተጠቅመው የኤሌክትሪክ ኋይልን ማመንጨት እንደሚችሉ የሚረጋገጥበት ሲሆን በውሀ ኋይል ማመንጫዎቹን የመሞከሩ ስራም በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑንም ነው የሰማነው።

የኋይል ማመንጫዎቹ በውሀ ተሞክረው የሚመነጨው ኋይልም ወደ ብሄራዊ የኋይል ቋት የሚገባ ሳይሆን ለሙከራ ያህል ብቻ የሚከናወን መሆኑንም ነው የተረዳነው። ሆኖም በውሀ የሚደረገው ሙከራ ግድቡ የኤሌክትሪ የኋይል  አመንጭቶ ወደ ብሄራዊ ቋት ለማስገባት ለሚደረገው ጥረት ግን ወሳኝ ደረጃ ነው።

በውሀ ሙከራ እየተደረገላቸው ያሉት የኋይል ማመንጫ ተርባይኖች በግድቡ በታችኛው የውሀ መቀበያ አካባቢ ያሉት ሲሆኑ የተቀሩት ዘጠኝ የሀይል ማመንጫዎች በአንጻሩ ከፍ ወዳለው የግድቡ አካል ላይ ስለሚገጠሙ በቀጣይ ግድቡ በሚይዘው ውሀ የሚሞከሩ ይሆናል። የአሁኑ የኋይል ማመንጫዎቹ የውሀ ሙከራ ሲጠናቀቅም ወደ ሙሉ የኋይል ማመንጨት ይገባሉ።

 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በ2012 አ.ም እና 2013 አ.ም ሁለት ክረምቶች ለተከታታይ ጊዜ ውሀ ይዟል። በ2012 አ.ም ክረምት የግድቡ ቁመት ከባህር ጠለል በላይ 565 ሜትር ላይ ደርሶ 4.9 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ የያዘ ሲሆን ባለፈው አመት ክረምት ደግሞ መንግስት የግድቡን ቁመት እና የያዘውን ተጨማሪ ውሀ በቁጥር ባይገልፅም የውሀ ሙሌቱ የተሳካ እንደነበር አስታውቋል።

ባለፈው አመት ግድቡ ቁመቱ 595 ሜትር ከባህር ጠለል በላይ መድረስ እንደሚጠበቅበት እና የሚይዘው ተጨማሪ ውሀም 13.5 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ እንዲሆን የግድቡ የግባታ እቅድ ያሳያል። ሆኖም ሀገሪቱ ከነበረችበት ሁኔታ አንጻር የግድቡ ግንባታ እቅድ መሳካቱ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ቢኖሩም ህዳሴው ግድብ በሁለት ተርባይኖች የኤሌክትሪክ ሀይልን ማመንጨት እንደሚያስችለው ግን ማረጋገጥ ተችሏል።

ግንባታው ከተጀመረ 11 አመታት ሊደፍን ቀናት በቀሩት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ሲደረግ የነበረው ድርድር በአፍሪካ ህብረት ተይዞ የነበረ ቢሆንም ግብጽና ሱዳን በውሀ አያያዝና አለቃቀቅ ላይ አስገዳጅ ስምምነት ይፈረምልን በማለታቸው ኢትዮጵያ ደግሞ ይህ አይነቱ ስምምነት ጥቅሜን ይጎዳል በማለቷ ድርድሩ ሳይቋጭ  ቀርቷል። [ዋዜማ ራዲዮ]