Moyale refugees in Kenya-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- የሀገሪቱ ባንኮች ከአመታዊ ትርፋቸው 0.5 በመቶ የሚሆነውን በሀገሪቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ ሊያዋጡ ነው። ዋዜማ ባገኘችው መረጃ መሰረት በሀገሪቱ ያሉ ሁለት ሚሊየን የሚጠጉ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም መንግስት አቅም አንሶታል፣ ከለጋሾችም የሚፈለገው ድጋፍ ሊገኝ አልቻለም።

ተፈናቃይ ዜጎች በብዛት ያሉባቸው ክልል አስተዳደሮች ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ነው ልገሳው የተጀመረው።
በአሁን ሰአት በኢትጵያ ውስጥ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች 1.8 ሚሊዮን እንደደረሰ የብሄራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መረጃ ያሳያል።ይህም ኢትዮጵያን የሀገር ውስጥ መፈናቀል ካሉባቸው ሀገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ አሰልፏታል።
እነዚህን ተፈናቃዮችንና ሌሎች በተፈጥሮ አደጋ ችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለማቋቋም መንግስት 1.4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚያስፈልገው ኮሚሽኑ ይገልጻል።

ይህን ያክል መጠን ያለውን ገንዘብ መንግስት ከራሱ ካዝና ማግኘት እንደቸገረው ታውቋል። መንግስት የዚህን ሰባ በመቶ ለመሸፈንና 30 በመቶውን ከለጋሾች ለማግኘት ነው ያቀደው ። ሆኖም ገንዘቡ የመንግስትን ካዝና በመፈታተኑ የክልል አስተዳደሮች በሀገሪቱ በአንጻሩ አትራፊ ስራ ላይ ናቸው ወደተባሉት የባንክ ዘርፍ አንቀሳቃሾች ፊቱን አዙሯል።
በሀገሪቱ ያሉ የንግድ ባንኮች ባደረጉት ውይይትም ከአመታዊ ትርፋቸው 0.5 በመቶ የሆነውን ገንዘብ ለዚሁ አላማ ለመለገስ ወስነው የሰጡም አሉ። ለመስጠት ውሳኔን የማጸደቅ ሂደት ላይ ያሉ ባንኮች መኖራቸውንም ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ያገኘችው መረጃ ያሳያል። እስካሁንም ከአንድ ባንክ 20 ሚሊየን ብር እንደተለገሰም ማወቅ ችለናል።
ባለፉት ወራት በኢትዮጵያ በተለያዩ ስፍራዎች ብሄር ተኮር ግጭቶች ተነስተው በርካቶች መፈናቀላቸው የሚታወስ ነው።በጌዲዮና ጉጂ አካባቢ በተፈጠረው ብሄር ተኮር ግጭት አንድ ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ኦሮምያ ክልል አዋሳኝ አካባቢ በተነሳው ግጭትም በርካቶችን ለመፈናቀል አብቅቷል።መስከረም ወር ላይ በቡራዩ ላይ በደረሰ አደጋ በሺዎች ተፈናቅለው ነበር።ቀደም ብለው ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎችን የማቋቋሙ ስራ አልተጠናቀቀም ።
እነዚህ ሁሉ ጫናዎች በየአመቱ በሴፍትኔት ዕርዳታ ከሚያስፈጋቸው ዜጎች ጋር ተዳምሮ ከባድ የበጀት ጫና እየፈጠረ መሆኑን ከመንግስት ባለስልጣናት በኩል እየተነሳ በመሆኑም ነው የባንኮቹ ድጋፍ ያስፈለገው።