Pink Ribbonበየዓመቱ የ44 ሺህ ዜጎቻችን ሕይወት በካንሰር ይቀጠፋል፡፡ መንግስት እንደሚለው 70 ሺህ፣ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ደግሞ 150 ሺሕ አዳዲስ የካንሰር ታማሚዎች በየዓመቱ ይመዘገባሉ፤ ችግሩ እየከፋ እንጂ እየተሻለው ላለመሄዱ በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በአሕጉራችን አንድ ሶስተኛው የካንሰር ተጠቂ ሕይወቱን የሚያጣው በሕክምና ማጣት ነው፡፡ የሁሉም ካንሰር ዓይነቶች መነሻ ሠበቡ ይሕ ነው ተብሎ መደምደም ባይቻልም… ከባድ ኢንፌክሽንና ትምባሆ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ፡፡

[ዳንኤል ድርሻ ያዘጋጀውን መሰሉ ንጉስ በድምፅ አስናድታዋለች አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ]

 

በ2050 በሕዝብ ብዛት በዓለም 9ኛ ደረጃ ትይዛለች በተባለችው ባለ 96 ሚሊየኗ ኢትዮጵያም የካንሰር ሥርጭት አድማስ ሠፍቷል፡፡  የፖሊሲ አውጪው ትኩረት አለመስጠት፣ የመከላከልና ቁጥጥር መላላት፣ የሕዝብ ግንዛቤ ማነስ የካንሰር ስርጭት በሚቻልበት መጠን እንዳይቀንስ ሠበብ ሆነዋል፡፡

በኢትዮጵያ በብሔራዊ ደረጃ ከሚመዘገበው የሞት መጠን የ5.8 ፐርሰንቱ መንስዔ ካንሰር ነው፡፡ ከሶስት ሟቾች ውስጥ ሁለቱ ሴቶች መሆናቸው ደግሞ ይበልጥ ያሳዝናል፡፡ በሃገሪቱ ከፍተኛ ሥርጭት ያለው የጡት (30.2 %) ካንሰር ሲሆን፣ ተከታዩን ደረጃ የሚይዙት የማሕጸን [ሠርቪክስ] (13.4 %) እና የደንዳኔ [ኮሎሬክታል] (5.7 %) ናቸው፡፡

ስለ ሁኔታው አሳሳቢነት ከሰሞኑ ለቱርክ የዜና ተቋም ያብራሩት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የካንሰር ክትትልና ቁጥጥር አማካሪ ዶክተር ኩኑዝ አብደላ… መንግስት የአምስት ዓመት የካንሰር ዕቅ አውጥቶ ለለውጥ እንደሚተጋ ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ኩኑዝ በቀጣይ አምስት ዓመት የሚፈጸሙ ብለው የዘረዘሯቸው፣ ከ10 ዓመት በፊት በሌሎች ሹማምንት የተነገሩ… ነገር ግን ሥራ ላይ ያልዋሉ ናቸው፡፡ ለአብነት ያሕል በሃገሪቱ አምስት የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የካንሰር ማዕከላት እንደሚቋቋሙ ከተገለጸ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ ዶክተር ኩኑዝም በቀጣዩ አምስት ዓመት የመንግስት ዕቅድ በአምስት ዩኒቨርሲቲዎች የካንሰር ማዕከላት ይቋቋማሉ ነው የሚሉት፡፡

እስካለፈው የካቲት “አንድ ለናቱ” ሆኖ የቆየው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ያለው የካንሰር ማዕከል ነው፡፡ የካንሰር ተጠቂ እንደሆኑ ከታወቀላቸው ሰዎች እንኳ ከ1 % የሚበልጡት ሕክምና ማግኘት አልቻሉም፡፡ የባለሙያዎች እጥረት፣ የመሳሪያዎች አለመኖርና ያሉትም ማርጀት፣ የቦታ ጥበት… ወዘተ በጋሬጣነት ይጠቀሳሉ፡፡ የ1 ሲቲ ስካነር እና 1 ኤምአይ ስካነር ባለቤቱ ይሕ ማዕከል የሚገኝበት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ካለው 600 አልጋ አስራ ስምንቱ ብቻ ነው ለካንሰር ክፍሉ የተመደበው፤ ከ201 ዶክተሮች በተጠቀሰው ክፍል ሲያገለግሉ የቆዩት 2 ሄማቶሎጂስት፣ 4 ሜዲካል ኦንኮሎጂስት፣ 4 ራዲዮቴራፒ ሠጪዎች ናቸው፤ ከግቢው 627 ነርሶች ውስጥ 26ቱ ናቸው ለማዕከሉ የተመደቡት፤ ለሕጻናት ካንሰርም አንድ ዶክተር፡፡

በትልቁ የካንሰር ማዕከል ውስጥ፣ ቢያንስ በዓመት 250 ሺህ ታማሚዎችን የሚከታተሉት እነዚሕ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ማዕከሉ መድረስ ያቃታቸው በርካታዎች የሕክምና ክትትላቸው ከባሕል መድሃኒት ሳይዘል ሕይወታቸው ያልፋል፡፡ የካንሰር ምርመራ የጀመሩ የግል ክሊኒኮችና ሆስፒታሎች ክፍያ ለብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ የሚቀመስ አይደለም፡፡

ለካንሰር ማቃለያ በዕርዳታ የሚበረከተው ገንዘብ ቀላል አይደለም፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት በወጣ አንድ መረጃ ብቻ የሚከተሉት ተዘርዝረዋል፡፡ መድሃኒት አምራቹ ግላክሶ ስሚዝ ክላይን… ብሔራዊ የካንሰር ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅና ሕትመት ወጪ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ2 ሚሊየን ዶላር ላይ ለግሷል፤ ብሪስቶል ማየርስ ፋውንዴሽን ከ1.2 ሚሊየን ዶላር በላይ ፈቅዷል፤ ፔፕፋር ከማሕጸን ካንሰር ጋር በተያያዘ 1 ሚሊየን ዶላር ሠጥቷል፤ አሜሪካን ካንሰር ሶሳይቲ በማቲያስ ወንዱ ፋውንዴሽን በኩል ለግንዛቤ ማስጨበጫ 40 ሺህ ዶላር አበርክቷል፤ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኤጀንሲ በዩኒቨርሲቲዎች ይገነባሉ ለተባሉ ማዕከላት 2.2 ሚሊየን ዶላር ለቋል፤ ጄኔራል ኤሌክትሪክ 500 ሺህ ዶላር (በዳያስፖራዎች ይገነባል ተብሎ ለነበረው የካንሰር ማዕከል)፣ ኮርድኤይድ ግሎባል 600 ሺህ ዶላር፣ ግራውንድስ ፎር ሄልዝ 200 ሺህ ዶላር ሠጥተዋል፤ የካንሰር ሕክምና ክትትል ግን ባለበት ይረግጣል፡፡

መንግስት በተመረጡ የፌደራልና የክልል ሆስፒታሎች የካንሰር ታማሚዎች ምዝገባ፣ ቁጥጥርና ክትትል እንዲሁም የመድሃኒት እደላ ጀምሯል፡፡ በ2008 ዓ.ም መንግስት በመቀሌ፣ ጎንደር፣ ጂማ፣ ሐዋሳ እና ሐሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ይከፈታሉ ካላቸው የካንሰር ማዕከላት አንዳቸውም ተግባራዊ አልሆኑም፡፡ የሠርቪካል ካንሰር ክትትል ጣቢያዎች ከ25 ወደ 135 ያድጋሉ ቢባልም ከዚህም ግማሹ እንኳ አልተሳካም፡፡ የበጎ አድራጎት ተቋማት ድጋፍ ሳይለየው በጥቁር አንበሳና በጤና ጥበቃ አማካይነት በአዲስ አበባ ወረዳ 8 አዲስ የካንሰር ተቋም ተከፍቷል፤ አዲሱ ማዕከል በቀን ከ85 ታማሚዎች በላይ ክትትል ባያደርግም… ለተዳፈነው የካንሰር ሕመምተኞች ጭላንጭል ተስፋ ሳይፈነጥቅ አይቀርም፡፡