ዋዜማ ራዲዮ- ለገበያ ማረጋግያ አላማ የሚውል 400ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዥን በተመለከተ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 10 የቀድሞ የመንግስት ሀላፊዎች በቁጥጥር ስር ውለው ለምርመራ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡


የጊዜ ቀጠሮው ባበቃበት ሚያዝያ 24 ቀን 2011 ዓም የፌደራል ፖሊስ ሙስና ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ምርመራውን ማጠናቀቁን ተከትሎ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ መዝገቡን ተቀብሏል፡፡በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎትም የክስ ፋይል ከፍቶ ከሰዓት በኋላ አስሩን ተከሳሾች አቅርቧል፡፡


የመንግስት ግዥ እና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ይገዙ ዳባን ጨምሮ አቶ ተስፋዬ ብርሀኑ፣ አቶ ሰሎሞን በትረ፣ አቶ ሶሎሞን አይኒማዓር፣ አቶ ዮሴፍ ራፊሶ፣አቶ ተክለብርሀን ገ/መስቀል፣ አቶ ትሩፋት ነጋሽ፣ አቶ ዘሪሁን ስለሺ እና አቶ ጆንሴ ገደፋ የተባሉ የኤጀንሲው የቀድሞ ሀላፊዎችን እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን የቀድሞ ዋና ስራ አስፈፃሚ የነበሩት አቶ መንግስቱ ከበደ የተባሉት ናቸው የተካተቱት፡፡


የአቃ ህግ ክስ ዝርዝርም ወንጀሉ በ1996 ዓ የወጣውን የኢፌድሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 32(1)(ሀ) እና በ2007 ዓም የወጣውን የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 13(1)(ሐ) እና 2 ላይ ያሉትን ድንጋጌዎችን በመተላለፍ የተደረገ ነው ሲል ማብራርያውን ጀምሯል፡፡


ክሱ የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው ከ2010 እስከ 2011 ባለው ጊዜ መሆኑን የሚገልፅ ሲሆን ለገበያ ማረጋግያ እንዲሆን አለም አቀፍ የግዥ ጨረታ የወጣለት የ400ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ እንደነበር ይጠቅሳል፡፡


ለገበያ ማረጋግያነት እንዲሆን በኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽ እንዲገዛ የተጠየቀው ይህ ስንዴ ታድያ መጀመርያ ጥቅምት 19 በወጣው አለም አቀፍ ግልፅ ጨረታ ሻኪል ኤንድ ካምፓኒ የተባለ የፓኪስታን ኩባንያ 96.4 ሚሊየን ዶላር የሆነ ነዝቅተኛ ዋጋ በማስገባት አሸናፊ ሆኖ ነበር፡፡

ሁለተኛ የወጣው ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል ደግሞ ከእዚህ በሁለት ሚሊየን ዶላር የበለጠ ዋጋ ነበር ያስገባው፡፡ እናም አሸናፊው የፓኪስታን ካምፓኒ ስንዴውን ለማቅረብ ታህሳስ ላይ ውል ቢዋዋልም በ15 ቀን ውስጥ ግን የውል ማስከበርያ የሆነውን የባንክ ጋራንት ማስገባት አልቻለም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፓኪስታን ባንኮች ጋር ግንኙነት የለኝም በማለቱ ነበር፡፡ ሆኖም አቅራቢው ድርጅት ከሌላ ሶስተኛ ሀገር ባንክ ዋስትናውን ለማምጣት ተጨማሪ ቀን እንዲሰጠው ቀደም ብሎ የጠየቀ ቢሆንም ተከሳሾቹ በግዥ መመርያው መሰረት ተጨማሪ ቀን መስጠት የሚችሉ እንደሆነ እያወቁ ውሉን አቋርጠዋል መባሉን ክሱ ያስረዳል፡፡


ይህ ተግባር ከፍተኛ የስንዴ እረት አስከትሎ በመንግስት እና በህዝብ ላይ ጉዳት አድርሶ እያለ ወረሀ ጥር ላይ ለሁለተኛ ጊዜ ጨረታ ወጥቷል፡፡ ይህ ጨረታ ግን በጨረታ ኮሚቴዎቹ መካከል የተፈጠረ የሀሳብ ልዩነትን ተከትሎ የጠራ የውሳኔ ሀሳብ አልቀረበም በሚል 110.7 ሚሊየን የዶላር የሆነ ዝቅተኛ ዋጋ ቢቀርብበትም ሚያዝያ ላይ እንዲሰረዝ ሆኗል፡፡


ይህን ተከትሎም በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የስንዴ እጥረት የተከሰተ ሲሆን የስነዴ ግዥ በአፋጣኝ እንዲፈፀምለት የአደጋ ስጋት እና አመራር ኮሚሽን መጠየቁን ተከትሎ ከግዥ መመርያ ውጪ ፕሮሚሲንግ የተባለውን ድርጅት ለመጥቀም ሲባል ያለ ጨረታ 200ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴ እንዲያስገባ የ1.6 ቢልዮን ብር ውል ፈፅዋል ይላል የአቃቤ ህግ ክስ፡፡

ይሁን እንጂ የውል ማስከበርያ ከቀደመው በተለየ ለሁለት ወራት ሳያስገባ ቀርቷል ፡፡ ቆይቶም የውጪ ምንዛሬ ብክነትን ለማዳን ያስቸል ዘንድ ማንኛውም የመንግስት ግዥ በኢትዮጵያ ንግድ መርከብ አገልግሎት በኩል እንዲሆን የሚያዘው የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት መመርያ አያዋጣኝም በማለት ስንዴውን ሳያቀርብ ውሉን ሰርዞታል፡፡
እናም ለዚህ ተግባሩ በሌላ ጨረታ እንዳይሳተፍ መታገድ ሲገባው ነሀሴ ወር ላይ ለ4ኛ ጊዜ በወጣው ጨረታ ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል በግል መርከብ 200ሺህ ሜትሪክ ቶን ስንዴውን ጭኖ እንዲያስመጣ አስደርገዋል ሲል አቃቤ ህግ የወንጀል ድርጊቱን ዘርዝሯል፡፡


ይህን ተከትሎም ታድያ 5.8 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ብሏል፡፡ በተጨማሪም ፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል የተባለውን ድርጅት ከ101 ሚሊየን ብር በላይ እንዲጠቀም አድርገዋልም ብሏል፡፡


8 ገፆች ባሉት ክሱ ላይ አቃቤ ህግ በግልፅ የወንጀል ድርጊቶቹን ከብራራ በኋላ በተሰረዙ ጨረታዎች ሲከፈሉ የቆዩ የልዩነት ገንዘቦች እና የመርከብ ወጪውን ጨምሮ ከፕሮሚሲንግ ኢንተርናሽናል ጋር በመመሳጠር በመንግስት ላይ 24.9 ሚልዮን ዶላር ወይንም 688 ሚልዮን ብር ጉዳት አድረሰዋል ብሏል፡፡

በዚህ ላይም ከፍተኛ የሆነ የስንዴ ፣የዱቄትና የዳቦ እጥረት እንዲሁም የዋካ መናር እንዲከሰት በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነት የመንግስትን ስራ በማያመች አኳኋን መርተዋል ብሏል፡፡ ለዚህም 19 የሚሆኑ ሰው ምስክሮች ዝርዝር እና 43 ገደማ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡


ከሶስት ተከሳሾች በቀር ሌሎቹ ጉዳያቸውን ለመከራከር መንግስት ጠበቃ እንዲያቆምላቸው በመናገር ለዚህም የሚሆን በቂ ሀብት የሌላቸው ስለመሆኑ በመሀላ አረጋግጠዋል፡፡ ችሎቱ ተከላካይ ጠበቃ እንዲቆም የመደበላቸው ሲሆን በቀረበው ክስ ላይ ግንቦት 6 እንዲቀርቡ ሲል ቀጠሮ ይዟል፡፡[ዋዜማ ራዲዮ]