ዋዜማ ራዲዮ- ከአምስት አመት በፊት ኢትዮጵያ የገዛቻቸውን ሰባት የደረቅ ጭነትና ሁለት የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ሰባት ቢሊየን ብር ያህል ወጥቶባቸዋል። ገንዘቡ በዋናነት ከቻይና የተገኘ ብርድ ነው። አሁን መርከቦቹ ሰርተው ዕዳቸውን መክፈል የሚችሉ አልሆኑም። እንዳውም ተጨማሪ ዕዳ ይዘው እየመጡ ነው። ይህ በተገቢው ጥናት ላይ ያልተመሰረተ ግዥ እንዲፈፀመ ያደረጉ ባለስልጣናት አልተጠየቁም።

ዝርዝሩን ያንብቡት። [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

ከሁለት ዓመት በፊት

የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2011 በጥቅሉ ዘጠኝ መርከብን ከቻይና ለመግዛት የገባው ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ አዋጭነት እና ሀገሪቱ ምን አይነት መርከብ ያስፈልጋታል የሚለውን ጥያቄ በተገቢው  ያልመለሰ ውል ሀገሪቱን ከባድ ኪሳራ ውስጥ እንደጨመራት ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ ያሳያል።

አውሮፓውያኑ 2011 የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት መርከቦችን ለመግዛት ያሰበው አንድም ነባሮቹ የሀገሪቱ መርከቦች እያረጁ በመምጣታቸው በሌላ በኩልም ሀገር ውስጥ የሚገባ ጭነትን የመጨመር አቅምን ከፍ ለማድረግ በማሰብ ነው።

ታድያ በወቅቱ የቻይና ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ (Exim Bank)  80 በመቶ ብድር አቅርቦ በጥቅሉ በወቅቱ በነበረው ምንዛሬ በ300 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር (ሰባት ቢሊየን ብር) ዘጠኝ መርከቦች እንዲገዙ ውል ይገባል።የመርከቦቹ አቅራቢዎችም የቻይና ኩባንያዎች ናቸው። በመርከብ ግንባታ ጥራት የሚታሙ ብዙ የቻይና ኩባንያዎች ቢኖሩም: የመርከቦቹን መግዣ ብድር የምታቀርበው ቻይና በመሆኗ :አበዳሪም መርከብ ገንብቶ ሻጭም ቤይጂንግ ሆነች ።

በዚህም እያንዳንዳቸው 28 ሺህ ቶን ደረቅ ጭነት የሚሸከሙ ሰባት መርከቦችን ለእያንዳንዳቸው 32.5 ሚሊዮን ዶላር ወጥቶባቸው ከሻንዶንግ ሁዋንጋይ መርከብ ገንቢ እንዲገዛ ውል ይፈረማል።ሁለት እያንዳንዳቸው 41 ሺህ 500 ቶን ነዳጅ የሚጭኑ መርከቦችን ደግሞ በጥቅሉ በ80 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እንዲገዙ ከጂንሊንግ ሺፕ ያርድ ጋር ውል ይታሰራል።የእነዚህ መርከቦች አጠቃላይ ዋጋ 300 ሚሊየን ዶላር ሆኖ 80 በመቶው ሀገሪቱ ብድር ገብታ ያሰረችው ውል ነው።

የብድር ዓመት

ግዥው የሀገሪቱን ኢኮኖሚያ የሚጎዳ ሆኖ ተገኝቷል።ጉዳቱ በተለይ ከነዳጅ መርከቦቹ የመጣ ነው።ሲጀመር ነዳጅን ሙሉ ለሙሉ ከውጭ ለምታስገባ ድሀ ሀገር እነዚህን ሁለት ውድ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ለእያንዳንዳቸው 40 ሚሊየን ዶላር እዳ ገብቶ መግዛት ምን ያክል አዋጭ ነው የሚለው ምንም አስተማማኝ ጥናት ያልተደረገበት ነገር ነበር። ሂደቱን የሚያውቁት ሰዎች ለዋዜማ ራዲዮ እንደተናገሩት መርከብ ድርጅቱ ሁለቱን ነዳጅ ጫኝ መርከቦች ለመግዛት ውል ሲገባ ሀገር ውስጥ ደንበኛው ሊሆን ለሚችለው የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅትን እንኳ በቅጡ አላማከረውም።

የመርከብ ድርጅቱ መርከቦቹን በአውሮፓውያኑ 2013 ከገንቢው የቻይና ኩባንያ ሲረከብ ችግሮቹ አግጥጠው ይመጣሉ።የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት መርከቦቹን ደንበኛ ሆኖ እንዲጠቀም ጥያቄ ሲቀርብለት : መርከቦቹን ስትገዙ የማውቀው ነገር የለም አላማከራችሁኝም። እኔ የሚያወጣኝ ነዳጅ ከሚሸጡልኝ ሀገራት ኩባንያዎች ላይ መርከብ ተከራይቼ ነዳጅ ሳመጣ ነው የሚል ምላሽን ሰጠ።የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ከዚህ በሁዋላ የነበረው ምርጫ በከፍተኛ ብድር የተገዙትን ነዳጅ ጫኝ መርከቦችን ለሌሎች ሀገራት ወይም ደንበኞች አከራይቶ ብድራቸውን እንዲከፍሉ ማድረግ ነው።

ለተወሰኑ ጊዜያት ወጣ ገባ እያሉም ሲከራዩ እንደነበር ምንጮቻችን ነግረውናል።ከዚያ በሁዋላ ግን ለረጅም ጊዜ መርከቦቹ ፈላጊ አጥተው ጅቡቲ ወደብ ላይ ቆመዋል። የሚገርመው መርከቦቹ ጅቡቲ ወደብ ላይ ሲቆሙ ሰራተኛ ተቀጥሮላቸው እንደ ዲዝል ላሉ የተለያዩ ወጭዎቻው ለጅቡቲ የሚከፈል የወደብ ኪራይን ጨምሮ በቀን ለእያንዳንዳቸው እስከ አምስት ሺህ የአሜሪካን ዶላር ይከፈልባቸዋል።

የፈረንጆቹ አቆጣጠር 2013 ኢትዮጵያ በታሪኳ ከፍተኛውን የውጪ ብድር የወሰደችበት ዓመት ነበር። ከቻይና ከተበደረችው አጠቃላይ 13.5 ቢሊየን ዶላር ብድር ግማሽ ያህሉ 6.5 ያህሉ ቢሊየን ዶላር በዚህ ዓመት የተወሰደ ነው።

ሰባቱ መርከቦች

ሀገሪቱ ባልተጠና እዳ ውስጥ የገባችው በነዳጅ ጫኝ መርከቦቹ ብቻ አይደለም በደረቅ ጫኝ ሰባት መርከቦቹም ጭምር ነው። የእነዚህ መርከቦች ርክክብ ከተፈጸመ በሁዋላ : ብዙም ሳያገለግሉ  የሞተርን ጨምሮ በተደጋጋሚ ብልሽት እያጋጠማቸው ለጥገና የቆሙበት ጊዜ አለ። ይህም ብቻ ሳይሆን ከመርከቦቹ ግንባታ የጊዜ መዛነፍ ኢትዮጵያ የግዥ ውሉን ተከትሎ ሊከፈላት ይገባ የነበረ ብር በመርከብ ድርጅቶቹ አመራሮች ዝርክርክነት ይሁን ሙሰኝነት ባልለየ ምክንያት አልተከፈላትም።ለምሳሌ ከሰባቱ የደረቅ ጭነት ተሸካሚ መርከቦች መካከል መቀሌ የሚል ስያሜ ተሰጥቷት የነበረችውን መርከብ ርክክብን ገንቢው የቻይናው ኩባንያ ከውሉ ውጭ ከስልሳ ቀን በላይ ያዘገየዋል።በዚህ ጊዜ ለኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት እስከ 50 ሚሊየን የኢትዮጵያ ብር ቅጣት መክፈል ነበረበት።የወቅቱ የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አህመድ ቱሳ ቻይና ድረስ ሄደው ውል የተጣሰበትን ሀምሳ ሚሊየን ብርና መርከቡን ተረክበው እንደመምጣት መርከቧን ብቻ ተረክበው መጥተዋል።ይህ ለብዙዎቹ የድርጅቱ ባልደረቦች እንቆቅልሽ ነው አቶ አህመድ ቱሳም በጉዳዩ ላይ ተጠያቂ አልሆኑም ።
ሀገሪቱ በዘጠኙ መርከቦች የተዝረከረከ ግዥ ምክንያት እስካሁን ባለ እዳ ነች።መርከቦቹም በራሳቸው እዳቸውን በቅጡ የሚከፍሉ አልሆነም።

ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ የቻይና ብድር ከተጫናቸው ሀገሮች ሁለተኛዋ ናት። ይህን ብድር ለመክፈል አቅሟ በመዛሉም በቅርቡ በአፍሪቃ-ቻይና ጉባዔ ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የብድር መክፈያ ጊዜው እንዲራዘም ቤጂንግን ተማፅነዋል። በጎ ምላሽም አግኝተዋል። [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/rim6MdwWTgA