PM Netanyahu and PM Hailemariam
PM Netanyahu and PM Hailemariam

ዋዜማ ራዲዮ- የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያን፣ ኬንያን፣ ኡጋንዳን እና ሩዋንዳን ጎብኝተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንጃሚን ኔታኒያሁ ከጎበኟቸው አራት ሀገሮች ጋር እስራኤል ባንድ ሆነ በሌላ መልኩ ታሪካዊ ትስስር ያላት ሲሆን በሰላሳ ዓመታት ውስጥ በዓይነቱ የመጀመሪያ መሆኑ የተነገረለት ይኸው ጉብኝት መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ባንድ በኩል ኔታኒያሁ ጉብኝቱን ያደረጉት ዐረብ ሀገራት ከቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት ወዲህ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ስትራቴጂካዊ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ በሙሉ ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ አቅም እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ወቅት ነው፡፡

በሌላ በኩል ደሞ ምዕራባዊያን በኢራን ላይ ጥለውት የቆዩት ማዕቀብ ተነስቶ ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ በእስራኤል ተይዞ የቆየውን ኃይል ሚዛን ለመጋራት አፋፍ ላይ በደረሰችበት ወቅት ነው፡፡ ኢራን ወደ አፍሪካ ቀንድም አንገቷን ለማስገባት ቀዳዳ እየፈለገች ባለችበት ወቅት የተካሄደ ጉብኝት መሆኑ ወቅታዊ ያደርገዋል፡፡ የኢራን ማንሰራራት ሳዑዲ ዐረቢያ እንድትነቃቃና ተገዳዳሪ ቀጠናዊ ኃያል ሀገር ለመሆን ጥረት እንድታደርግ ገፋፍቷታል፡፡

ኔታናኒያኑ ባሁኑ ጊዜ ከሌሎች ሀገራት በተለየ ለምን ምስራቅ አፍሪካ ላይ ብቻ ማተኮሩር ፈለጉ? ጉብኝታቸው በቀጠናውና መካከለኛው ምስራቅ ስላለው ኃይል አሰላለፍ ምን ይነግረናል? መንግስታቸው ከአፍሪካዊያን ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ ምን እንቅፋቶች ይገጥሙት ይሆን? ምን ዕድሎችስ አሉት? ቻላቸው ታደሰ ዝርዝር ዘገባ በድምፅ አዘጋጅቷል አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ

ኔታኒያሁን ፊታቸውን ወደ አፍሪካ እንዲያዞሩ ያስገደዷቸው ወቅታዊ ስትራቴጂያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ፖለቲካዊ ምክንያቶች አሉ፡፡ ባንድ በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቀኝ አክራሪ መንግስታቸው በአሜሪካና አውሮፓ ያለው ተደማጭነት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በሌላ በኩል ምዕራባዊያን በኢራን ላይ ጥለውት የቆዩትን ማዕቀብ ማንሳታቸው በመካከለኛው ምስራቅ በእስራኤል ብቻ ተይዞ የቆየውን የኃይል ሚዛን ካሁኑ ማዛባት ጀምሯል፡፡ ኢራን እና ሳኡዲ ዐረቢያ በአፍሪካ ቀንድ እግራቸውን ለመትከል ፉክክር ውስጥ መክረማቸውንም እስራዔል በደህንነቷና ብሄራዊ ጥቅሞቿ ላይ አደጋ የሚጋብዝ የማስጠንቀቂያ ደወል አድርጋ የወሰደችው ይመስላል፡፡

በመካከለኛው ምስራቅ ያሉት ሁለቱ ተቀናቃኝ እስላማዊ መንግስታት ሳዑዲ እና ኢራን ቢሆኑም የእስራኤል ዋነኛ ስጋት ግን ኢራን ነች፡፡ በኢራን ላይ ሳዑዲ እና እስራዔል ያላቸው ፖሊሲ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁለቱም ምስራቅ አፍሪካ ላይ የሚከተሉት ፖሊሲ ኢራን በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖራትን ኃይል ሚዛን በማዳከም ላይ ያተኮረው ፖሊሲያቸው ቅጥያ ነው፡፡ ኢራን በተለይ በሱዳን፣ ሱማሊያና ኤርትራ እግሯን ለመትከል ሽር ጉድ ማለት ከጀመረች ከራርማለች፡፡

አራን፣ ኳታር፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ቱርክ ለሱማሊያ መንግስት ግዙፍ ዕርዳታ በመለገስም ፉክክር ውስጥ ገብተው ከርመዋል፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊት በኢራን ዕርዳታ የተገነባ መሆኑ የተነገረለትን የሱዳን የጦር መሳሪያ ፋብሪካን በሚሳይል ማውደሟ ይህንኑ ስጋቷን ያሳየ ነበር፡፡ በወቅቱ ከእስራኤል የወጡ መረጃዎች እንደጠቆሙት በፋብሪካው የሚመረቱ ጦር መሳሪያዎች በኢራን አማካኝነት ለፍልስጤሙ ሃማስና ለሊባኖሱ ሂዝቦላ ይላኩ ነበር፡፡

የእስራዔል ፖለቲከኞች የኢራንን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሲከታተሉት ቢቆዩም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ኢራን በቀጠናው ያላት ተፅዕኖ መቀዛቀዝ ጀምሯል፡፡ በተለይ ሳዑዲዎች ከነዳጅ የሚያገኙትን የተትረፈረፈ ሃብት ተጠቅመው የድሃ አፍሪካዊያን ሀገራትን ልብ በማማለል ኢራንን ወደጃ ሀገር እያሳጧት ይገኛሉ፡፡ ጠቀም ያለ ገንዘብ ስጦታን ዋነኛ የዲፕሎማሲ መሳሪያ በማድረግም በቅርቡ ሱዳን፣ ሱማሊያ እና ኤርትራ ከኢራን ጋር የነበራቸውን አጋርነት እንዲያቋርጡ ማድረግ ችለዋል፡፡ ሱዳን ከሳኡዲ የተቸራትን አምስት ቢሊዮን ዶላር ማማለያ በተቀበለች ማግስት በሳኡዲ አረቢያ መሪነት በየመን ሁቲ አማፂያን ላይ ዘመቻ የሚያካሂደው የዐረብ ጥምር ወታደራዊ ኃይልን በይፋ ተቀላቅላለች፡፡ ሱማሊያም ኢራንን ዓይንሽን ላፈር ብላ የሳኡዲን ሃምሳ ሚሊዮን ዶላር ወደ ካዝናዋ አስገብታለች፡፡

ዕርግጥ ነው፣ የኢራን እና አፍሪካ ቀንድ ሀገራት ግንኙነት ተመልሶ ለመቀዛቀዙ ኃይማኖታዊ ልዩነቱም አስተዋፅዖ አድርጓል፡፡ የሱኒ እስልምና የገነነበት ምስራቅ አፍሪካ ባብዛኛው የሺዓ ዕምነት ተከታይ ለሆነችው ኢራን አመቺ ሊሆንላት አልቻለም፡፡ ዓሊ የማይባለው እውነታ ግን ኢራን በምስራቅ አፍሪካ ያላት ተፅዕኖ በሳዑዲ ግፊት መቀዛቀዙ ለጊዜው የእስራኤልን ራስ ምታት አስታግሶላታል፡፡

ኢራን የምትተወውን የኃይል ሚዛን ክፍተት ግን ሳዑዲ ዐረቢያ፣ ኳታር እና Gulf Cooperation Council አባላት የሆኑት ቱጃሮቹ የባህረ ሳላጤው ሀገሮች ሊሞሉት መሞከራቸው ለእስራኤል ሌላ ራስ ምታት መሆኑ አልቀረም፡፡ በተለይ ኤርትራ በቅርቡ አሰብ ወደብን በአምስት መቶ ሚሊዮን ዶላር ለተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ወታደራዊ ጦር ሰፈርነት አከራይተዋች መባሉ እስራኤልንም ሆነ ኢትዮጵያን ክፉኛ የሚያሳስብ ነው፡፡ የኪራዩ መጠን የተጠቀሰውን ያህል ከሆነ አውሮፓ ህብረት ለኤርትራ ከሰጣት ልማታዊ ዕርዳታ የሚለቅ በመሆኑ ገንዘብ አጠር የሆነችውን ኤርትራን አማልሏት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡

ሳዑዲመራሹ ጥምር ኃይል ከየመን ያለፈ ሰፊ ስትራቴጂካዊ ግብ ያነገበ ነው የሚሉ ታዛቢዎች በርካቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ዐረቦች በኢራን በሚደገፉት የየመን ሁቲ አማፂያን ላይ በሚያደርጉት ወታደራዊ ዘመቻ እስራዔል ደስተኛ ብትሆንም በዘመቻው ሽፋን ስትራቴጂካዊውን ቀይ ባህርን እንዲቆጣጠሩት ግን አትፈልግም፡፡ ሳዑዲ በእስራኤል ብሄራዊ ደህንነት ላይ ቀጥተኛ ስጋት ባትደቅንም በእጅ አዙር ግን ሁሌም ደህንነቷን መፈታተኗ አልቀረም፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ሳዑዲመራሹ ወታደራዊ ጥምር ኃይል ሱዳን እና ኤርትራን ማካተት መቻሉም የሳዑዲ ተፅዕኖ በአፍሪካ ቀንድ ስር እየሰደደ መሆኑን ያሳያል፡፡

ግብፅ፣ ሱዳን፣ ሱማሊያ እና ጅቡቲ የባህረ ሰላጤው ሀገሮች ጋር ባላቸው ኃይማኖታዊና ባህላዊ ትስስር ሳቢያ ጠንካራ ግንኙነት መፍጠራቸው አንሶ እስላማዊት ያልሆነችው ኤርትራ የዐረቦቹን ጥምር ኃይል መቀላቀሏ በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ያለውን ኃይል ሚዛን እያዛባው ነው፡፡ በኔታኒያሁ ጉብኝት ያልተካተተችው ኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለዐረቦች ያሳዩት ፊት በየአቅጣጫው አጣብቂኝ ውስጥ በመግባታቸው የወሰዱት ታክቲካዊ እርምጃ ይሁን ወይስ በመርህና ዘላቂ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ውሳኔ አሁን አፍን ሞልቶ መናገር አይቻልም፡፡

ዐረብ ኢምሬትስ በአሰብ ወደብ ብቻ ሳትወሰን የሱማሌላንዷን በርበራ ወደብ ጭምር ለመከራየት አሰፍስፋለች መባሉ ደሞ በተለይ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ደህንነት ላይ ስጋት ይደቅናል፡፡ የኤርትራ ወዳጅ የሆነችው ኳታርም ከኢትዮጵያ ጋር ተበላሽቶባት የቆየውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደገና ማደሷ ኢትዮጵያ ለሰፊው ስትራቴጂካዊ ግቧ እንቅፋት እንዳትሆንባት ለማለዘብ የታለመ ስልት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

የዐረቡ ዓለም አውራ የነበረችው ግብፅ በፀደዩ አብዮት ኢኮኖሚዋ ከደቀቀ ወዲህ የየዕለት ስራዋ ሳዑዲ ዓረቢያን ደጅ መጥናት ሆኗል፡፡ በቅርቡም አወዛጋቢዎቹን ሳናፊር እና ቲራን የተባሉ የቀይ ባህር ደሴቶቿን ለሳዑዲ መሽለሟም ይህንኑ እንደሚያሳይ ታዛቢዎች ይናገራሉ፡፡ ደሴቶች የሚገኙበት መስመር ከእስራኤል፣ ዮርዳኖስ፣ ኢራን እና ምዕራቡ ዓለም ነዳጅ ጫኝ መርከቦች የሚተላለፉበት መሆኑ ደሴቶቹ ለሳኡዲ ቁልፍ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አላቸው፡፡

ግብፅ 1967 የስድስቱ ቀን ጦርነት ጊዜ መስመሩን ዘግታ ዓለም ኣቀፍ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መፍጠር ችላ ነበር፡፡ ለዚህም ነበር እስራኤል በጦርነቱ መጨረሻ ደሴቶችን ተቆጣጥራ ለብዙ ዓመታት የቆየችው፡፡ በተለይ እስራኤልና ኢራን የፕሬዝዳንት አል ሲሲን ውሳኔ በደህንነታቸው ላይ አደጋ የሚደቅን አድርገው ሊያዩት ይችላሉ፡፡ ከእስራዔል ጋር የሰላም ስምምነት በመፈረም ቀዳሚ የሆነችውና ከእስራኤል ጋር መልካም ግንኙነት ያላት ግብፅ ቀስ በቀስ ተዳክማ የሳዑዲ ጥገኛ መሆኗ ለእስራኤል መልካም ዜና አይሆንም፡፡

ማዕቀብ የተነሳላት ኢራን ግዙፍ ነዳጅ ሃብቷን ተጠቅማ በአፍሪካም ሆነ በመካከለኛው ምስራቅ እንደገና የክፉ ቀን ስትራቴጂካዊ ወዳጆች ለማፍራት እንደምትችል እስራኤል ያመነች ይመስላል፡፡ ስለሆነም የኔታኒያሁ ጉብኝት አፍሪካዊያን ወዳጆቻቸውን ቀድመው በማበራከት ከኢራንም ሆነ ከሳዑዲ ተፅዕኖ ሊያወጧቸው ቆርጠው ይሆን? የሚል ጥያቄ አጭሯል፡፡

የእስራኤል መሪዎች ላለፉት ዓመታት ሙሉ ትኩረታቸውን መካከለኛው ምስራቅ ላይ በማድረጋቸው ከአፍሪካ አህጉር ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ድሮ ወደነበረበት ለመመለስ እምብዛም አልተጨነቁበትም፡፡ አሁን ግን የኔታኒያሁ ቀኝ አክራሪ መንግስት በዌስት ባንክ በቀጠለው ሰፈራ ፕሮግራሙ፣ ለሁሉን ዓቀፍ ሰላም ስምምነት ዳተኛ መሆኑ እና በኢራን ላይ በሚከተለው አፈንጋጭ ፖሊሲ ሳቢያ በአሜሪካና አውሮፓ ህብረት የነበረው ተደማጭነት እየቀነሰ በመምጣቱ ፊታቸውን ወደ አፍሪካ ለማዞር ተገደዋል፡፡

ኔታኒያሁም ቢሆኑ ሀገራቸው አፍሪካዊያን ወዳጆችን ማበራከት የምትፈልግበት ወሳኝ ወቅት ላይ መድረሷን አልሸሸጉም፡፡ ሰውዬው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ እና ሰብዓዊ መብት ካውንስሉ በመንግስታቸው ላይ ለሚያወጧቸው አሉታዊ ሪፖርቶችና ውሳኔ ሃሳቦች አፍሪካዊያን ድጋፋቸውን እንዲነፍጉ ማግባባት ሌላኛው ተልዕኳቸው አድርገውታል፡፡ እስራዔል በተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ዐረቦች ባንድ ድምፅ እያወገዟት አብላጫውን መያዛቸው እንቅልፍ ነስቷታል፡፡

ሀገራቸው በአፍሪካ ህብረት የነበራትን የታዛቢነት መቀመጫ እኤአ 2002 ከተነጠቀች ወዲህ ኔታኒያሁ መቀመጫውን እንደገና መልሶ ማግኘትን አንደኛው ዓላማቸው አድርገውታል፡፡ ሀገራቸው ከብዙዎቹ አፍሪካ ሃገሮች ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ስላላት ቀላል ባይሆንም በርትተው ከሰሩበት ግን ላይቸገሩ ይችላሉ፡፡ ብዙዎቹ አፍሪካዊያን ግን አጋርነታቸውን በአፍሪካ ህብረት ውስጥ የታዛቢነት መቀመጫ ላላት ፍልስጤም አድርገው ስለቆዩ የኔታኒያሁ ጥረት ከባድ ፈተና እንደሚጠብቀው መገመት አይከብድም፡፡ አፍሪካ ህብረትም ቢሆን በእስራኤል ጉዳይ ከቶውኑም አንድ አቋም ሊይዝ አይችልም፡፡ ለዚህም ይመስላል ደጋግመውሀገሬ ወደ አፍሪካ በሰፊው መጥታለችበማለት አብዛኛዎቹን አፍሪካዊያን መንግስታት ከወዲሁ ማማለል የፈለጉት፡፡

የአፍሪካዊያን ስደተኞች ጉዳይም መረሳት የለበትም፡፡ አፍሪካዊያን መንግስታትን እምብዛም አያሳስባቸውም እንጂ ጥቁር ስደተኞች በእስራኤል ሰቆቃ እንደሚደርስባቸው ዓለም ኣቀፍ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሁሌም የሚገልፁት ሃቅ ነው፡፡ የኔታኒያሁ መንግስትም ለስደተኞች ጥገኝነት መስጠት አልፈቀደም፡፡

እንዲያውም ለሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ጠቀም ያለ የገንዘብ ጉርሻ ወይም ወታደራዊ ቁሳቁሶች በመለገስ 40 ሺህ ኤርትራዊያንና ሱዳናዊያን ስደተኞችን ከእስራኤል ተቀብለው ሊያሰፍሩ ሚስጢራዊ ስምምነት መድረሳቸውን ታዋቂው ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ በቅርቡ ዘግቧል፡፡ ምናልባትም ኔታኒያሁ በጉዳዩ ላይ ከፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ እና ፖል ካጋሜ ጋር ተመካክረውበት ይሆናል፡፡

ኔታኒያሁ ከአፍሪካዊያኑ መሪዎች ጋር የደረሱባቸውን ፀጥታ እና ቀጠናዊ ጅኦፖለቲካ ነክ ስምምነቶችን በዝርዝር ለማወቅ ቢያስቸግርም በኦፊሴል ግን እስራዔል በምግብ ዋስትና፣ ዘመናዊ ግብርና ቴክኖሎጂ፣ ኢንቨስትመንት፣ ፀጥታ፣ ፀረሽብር እና ጤና ዘርፍ ዙሪያ ድጋፍ ለማድረግ መፈለጓን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ የኔታኒያሁ መንግስት በጉብኝቱ ዋዜማ ለአፍሪካዊያኑ ኢኮኖሚያዊ እና ፀጥታነክ ድጋፎችን ለመስጠት 13 ሚሊዮን ዶላር መመደቡምወደ አፍሪካ በሰፊው መጥተናልለሚለው አባባላቸው ማጠናከሪያ ዕርምጃ ተደርጎ ተወስዶላቸዋል፡፡

በጠቅላላው እስራኤል ፊቷን ወደ አፍሪካ ብታዞርም እንኳ አብዛኛዎቹ አፍሪካዊያን ፊታቸውን ወደ እስራኤል ለማዞራቸው ገና አስተማማኝ ማረጋገጫ የለም፡፡ ለዚህም አንዱ እንቅፋት ቀጥተኛና ሆነ ልማታዊ ዕርዳታ መቀበልን በለመደችው አህጉር ውስጥ እስራኤል የለጋሽነት ስም የሌላት መሆኑ ነው፡፡ በርግጥ በፀጥታ ዘርፍ የምትሰጠው ዕርዳታ የብዙ መንግስታትን ልብ ማማለሉ አይቀሬ ነው፡፡ እስካሁንም ለአፍሪካዊያን ዋነኛዋ ጦር መሳሪያ ሻጭ ነች፡፡ ከጠቅላላ ምርቷ ግን ወደ አፍሪካ ገበያ የሚገባው ሁለት በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው፡፡

የሆነው ሆኖ ብልጣብልጡ ፖለቲከኛ ኔታኒያሁወደ አፍሪካ በሰፊው መጥተናልያሉትን ቃላቸውን ማክበር አለማክበራቸው ወደፊት የሚታይ ነው፡፡ ተንታኞች እንደሚሉት ግን አሁንም የኔታኒያሁን ቁርጠኝነት በጥርጣሬ የሚያዩት አፍሪካዊያን ቀላል አይደሉም፡፡ ኔታኒያሁ ከአፍሪካ የሚፈልጉትን ያህል መልሰው መስጠታቸውን ይጠራጠሩታል፡፡

በተናጥል ሲታይ ግን የእስራኤልን ቁርጠኛ አጋርነት የሚፈልጉ ሀገሮች አሉ፡፡ በተለይ በዲፕሎማሲ ድክመት ሳቢያ ብሄራዊ ደህንነቷ አጣብቂኝ ውስጥ እየገባባት ያለችው የባህር በር አልባዋ ኢትዮጵያ የእስራኤልን ቁርጠኛ አጋርነት የምትፈልግበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ትገኛለች፡፡ ኔታኒያሁም ለፓርላማው የሁለቱን ሀገሮች ታሪካዊ ዳራ ያሳየና በስሜት የተሞላ ንግግር ማድረጋቸው ኢትዮጵያን የአዲሱአፍሪካ ፖሊሲያቸውማዕከል ሊያደርጓት ማሰባቸውን ጠቋሚ ነው፡፡ ኡጋንዳና ኬንያም ቢሆኑ ከአልሸባብ ጋር በሚደረገው ፀረሽብር ትግል፣ ሽብር ቀድሞ በማክሸፍ ስልጠና ዘርፍ የእስራኤልን ድጋፍ ለማግኘት የቋመጡ ይመስላል፡፡ ኬንያ በተለይ ብዙም ያልተወደደላትን ከሱማሊያ ጋር የሚያዋስናትን ድንበሯን በአጥር በመከለል ረገድ ከእስራኤል ልምድ እና ቴክኒካዊ ድጋፍ ትሻለች፡፡

በተረፈ ግን እስራኤል በምስራቅ አፍሪካ ቁልፍ ብሄራዊ ጥቅሞች አልነበሯትም፡፡ ቀጠናው የሽብርተኞች መናኸሪያ ሆኖ መክረሙም ያሳደረባት ቀጥተኛ ተፅዕኖ የለም፡፡ ምናልባት ወደፊት ግንኙነቱ ተጠናክሮ ብሄራዊ ጥቅሞች የሚኖሯት ከሆነ ግን የሱማሊያ መረጋጋት አስፈላጊዋ ነው፡፡ ባሁኑ ጊዜ ከአልሸባብና አል ቃይዳ ባሻገር ራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ የሚጠራው አሸባሪ ቡድንም ትኩረቱን ወደ ሱማሊያ እያደረገ መሆኑ እስራኤልን ሊያሳስብ ይችላል፡፡