ዋዜማ ራዲዮ- በኢምፔርያል ሆቴል ላይ ከተደረገ የእድሳት ስራ ጋር በተያያዘ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ፕላንት ኢንስታሌሽን ም/ዋና ዳይሬክተር ኃላፊ ተወካይ በነበሩት ኮለኔል ተክስተ ሀይለማርያም ስም የከፈተውን የሙስና ወንጀል ክስ መዝገብ ማስረጃ እና ምስክሮቹነን በማስቀረብ ሲያስመረምር ሰንብቷል፡፡

የአቃቤ ህግ ክስ በ2004 ዓም ጥር ወር ላይ ግዥው የተፈፀመው የኢምፔርያል ሆቴል እድሳት የስም ዝውውር ሳይደረግ በተመሳሳይ አመት ሀምሌ ወር ላይ ያለጨረታ እና የግዠ መመርያን ባልተከተለ መልኩ እንደተከናወነ ያትታል፡፡

መመርያነን ጥሷል በተባለው የዚህ ሆቴል እድሳት ስራም የእድሳት ስራውን በድረድር ተቀብሏል የተባለው 9ኛ ተከሳሽ (አቶ ደጌና አሰፋ)ከ 1- 8 ካሉት የኮርፖሬሽኑ የስራ ሀላፊዎች ጋር በጥቅም በመመሳጠር በወቅቱ ከነበረው የገበያ ዋጋ እጅጉን የተጋነነ በአጠቃላይ 31,342,922.60 (ሰላሳ አንድ ሚሊዮን ሶስት መቶ አርባ ሁለት ሺ ዘጠኝ መቶ ሃያ ሁለት ብር ከስልሳ ሳንቲም) ክፍያ እንዲፈፀምለት በማድረግ ያለአግባብ በልዩነት ብር 21,140,615.60 (ሃያ አንድ ሚሊዮን አንድ መቶ አርባ ሺ ስድስት መቶ አስራ አምስት ብር ከስልሳ ሳንቲም) ጥቅም አግኝቷል ሲልም አቃቤ ህግ የወንጀል ድርጊቶቹን በዝርዝር በክሱ አስረድቶ ነበር፡፡

በዚህም ከ1- 7 ያሉትን ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት ሲዘረዝር 8ኛ አና 9ኛ ተከሳሽን ደግሞ በልዩ ወንጀል ተካፋይ በመሆን ስልጣንን ያለአግባብ የመጠቀም ወንጀል ፈፅመዋል በማለት ይህን የሚያጠናክርለትን 12 የሰው ምስክር እና 15 የሰንድ ማስረጃዎችን አስቆትሮ ነበር፡፡

ሆኖም አቃቤ ህግ ክስ ካቀረበባቸው 9 ተከሳሾች መሀል 4ቱ ብቻ ሲሆነ ጉዳያቸውን በችሎት ሲከታተሉ የቆዩት ቀሪ 5ቱ ጉዳያቸው በሌሉበት እንዲታይ በጋዜጣ የታወጀባቸው ናቸው፡፡

ይህን መዝገብ ሲመረምር የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ (ቀድሞ 15ኛ የነበረው) 3ኛ የሙስና ወንጀሎች ችሎት ትናንት ረፋድ ላይ ተሰይሞም ሲመረምር በቆየው የአቃቤ ህግ ማስረጃዎች ላይ ብን ሰጥቷል፡፡

በዚህም መሰረት ጉዳያቸው በሌሉበት ሲታዩ የነበሩትን 5 ተከሳሾች በጠቅላላ ማለትም አቶ ስምኦን ገብራይ ተወልደ (በኮርፖሬሽኑ የኒዉ ቢዝነስ ዲቨሎፕመንት ሰራተኛ) ፣ሕንፃ አመሓ ገብረማርያም (በኮርፖሬሽኑ የኒዉ ቢዝነስ ዲቨሎፕመንት ሰራተኛ)፣ ሃ/አ መሳይ ባዬ ሸኩባ (በኮርፖሬሽኑ የኒዉ ቢዝነስ ዲቨሎፕመንት ሰራተኛ)፣ ግርማ ብዙነህ ገብረማርያም (የኢሉጂ ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግል ማሕበር፣ ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ)፣ እንነዲሁም አቶ ደጌና አሰፋ መስፍን ( ደጌና አሰፋ ህንፃ እና ውሀ ስራዎች ተቋራጭ ባለቤት) ላይ የጥፋትኝነት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ሌ/ኮ/ል ያሬድ ሀይሉን፣ሌ/ኮ/ል ሙሉ ወልደ ገብርዔልን እና ሌ/ኮ/ል ሰሎሞን በርሄን ደግሞ ነፃ ናቸው ሲል በይኗል፡፡

በዚህ የክስ መዝገብ 1ኛ ተከሳሽ የሆኑትን ኮ/ል ተክስተ ብቻ እንዲከላከሉ ችሎቱ በይኗል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]