Hotelዋዜማ ራዲዮ-የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ባለኮከብ ሆቴል ለመገንባት የኢንቨስትመንት ፍቃድ የወሰዱ 87 ከፍተኛ ባለሐብቶችን ፍቃድ ለመሰረዝ በዝግጅት ላይ ነው፡፡ 

በተሻሻለው የኢንቨስትመንት አዋጅ ቁጥር 769/2004 መሠረት የባለኮከብ ሆቴል ገንቢዎች አገልግሎት መስጠት እስኪጀምሩ ድረስ በየዓመቱ ለኮሚሽኑ ያሉበትን ደረጃ ማስገምገምና ፍቃድ ማሳደስ እንዳለባቸው ያስገድዳል፡፡ ኾኖም በርካታ ገንቢዎች ፍቃዳቸውን ከሆቴል ልማት ጋር ተያይዞ የሚሰጡ የቀረጥ ነጻ አገልግሎቶችን በገፍ ለማስገባት ከተጠቀሙበት በኋላ እንደሚሰወሩ ይነገራል፡፡

ዓመታዊ እድሳት ማድረግ ያስፈለገውም አንድም ይህንኑ ለመቆጣጠርና ሆቴሎቹ ያሉበትን የግንባታ ደረጃ ለመረዳት ሲሆን ይህንን ደንብ ተላልፈው የተገኙ 87 አገር በቀልና ዓለም አቀፍ የባለኮከብ ሆቴል ገንቢዎች ከሚያዚያ 30 በኋላ ፍቃዳቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚሰረዝ በኮሚሽኑ ማስታወቂያ ሰሌዳ ተገልጾላቸዋል፡፡

ፍቃዳቸው ከሚሰረዝባቸው ገንቢዎች መካከል  በዓለማቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ስም ያለው የኩዌቱ አልኻራፊና ልጆቹ አክሲዮን ማኅበር ይገኝበታል፡፡ አልኻራፊ ኩባንያ ዓመታዊ ዓለም አቀፍ ትርፉ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የኾነና ከሆቴል ሰንሰለት በተጨማሪ በእርሻ በአልሙኒየም፣ በአቪየሽን፣ በነዳጅ፣ በሪልስቴትና በቴሌኮም ዘርፍ ከፍተኛ ስም ያለው በተለይም በአረቡ ዓለም ገናና ድርጅት ነው፡፡

አልኻራፊ ከፈረንሳዩ አኮር ሆቴሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር ከዚህ ቀደም መስቀል አደባባይ ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ማዶ፣ ከማርዮት አፓርትመንት ሆቴል ጎን የሚገኙ አንድ ባለ 6 ፎቅ (ባለ 3 ኮከብ) እና አንድ ባለ 7 ፎቅ (ባለ 4 ኮከብ) ሆቴሎችን መገንባት ጀምሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ኾኖም ማኔጅመንቱ በአገሪቱ የተዝረከረከ ቢሮክራሲ በመማረሩ ይዞታውን ሙሉ በሙሉ ዱባይ መቀመጫውን ላደረገው አሊ አልዋርዲ ግሩፕ በስድስት መቶ ሚሊዮን ብር በሽያጭ ለማስተላለፍ ተገዷል፡፡

አሊ አልዋርዲ በስሩ ኤ ኤስ ቢ (ASB)  ሆቴል የሚገኝ ሲሆን እነዚህን በጅምር ቀርተው የነበሩ ኩታ ገጠም ይዞታዎችን ቀላቅሎ ወደ አንድ ባለ ግዙፍ አምስት ኮከብ ሆቴል በመለወጥ ግንባታ ዉስጥ ገብቷል፡፡ ሆቴሎቹ ሲጠናቀቁ የማስተዳደሩን ሥራ የሚረከበው የአሜሪካው ሃይአት ሆቴልስ (Hyatt Hotels) ካምፓኒ እንደሚሆን መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ይህ የሆቴል ሰንሰለት በዓለም ደረጃ አምስት መቶ የሚጠጉ ሆቴሎችን በሥሩ ያቀፈ ነው፡፡

አልኻራፊ በወቅቱ ሆቴሎቹን መገንባት ሲጀምር የፈረንሳዩ አኮር ሆቴል የሚያስተዳድራቸው መንታ ሆቴሎችን ታሳቢ ያደረገ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ወደ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን የሚያየውን ሆቴል በኢቢስ (IBIS) ኢንተርናሽናል ስም በባለ ሦስት ኮከብ ደረጃ፣ ወደ ሰማዕታት ሀውልትና አዲስ አበባ ሙዝየም የሚመለከተውን ሕንጻ ደግሞ ኖቮቴል (NOVOTEL) በሚል ብራንድ በባለ 4 ኮከብ ደረጃ ታሳቢ በማድረግ ነበር ወደ ግንባታ የገባው፡፡ ኾኖም የአገሪቱ እጅግ የተተበተበ ቢሮክራሲና ሙስና የሚመጥነን አይደለም በሚል በከፍተኛ ቅሬታ የሆቴል ልማቱን በጅምር ጥለው እንደወጡ በወቅቱ ተዘግቧል፡፡

አሁን ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን ፍቃዳቸው ከሚሰረዝባቸው ኩባንያዎች የአልኻራፊን ስም መጥቀሱ ኩባንያው ቀደም ብሎ ከሆቴል ልማት መውጣቱን ዘንግቶት ይሆን አልያም ለሌላ ሆቴል ግንባታ ፍቃድ ወስዶ የታወቀ ነገር የለም፡፡

ከአልኻራፊ ሌላ በአዲስ አበባ፣ በመቀሌና በኦሮሚያ ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል እንገነባለን ያሉ የኤርትራ፣ የሱዳን፣ የህንድ፣ የቻይና፣ የአሜሪካና የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸው ባለሐብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃዳቸው እንዲሰረዝ ተወስኗል፡፡

ኤስ አር ጁኔራል ትሬዲንግ በኤርትራዊ የተያዘ ኩባንያ ሲሆን ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ለመሥራት አቅዶ የነበረው በአዲስ አበባ ከተማ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ አማል ጆርጅ አብረሃም የተባሉ ስዊድናዊ ባለሐብት ከባለ አምስት ኮከብ ሆቴል አልሚዎች ተርታ ስማቸው ተጠቅሷል፡፡ ይህን ባለአምስት ኮከብ ሆቴሉን ለመሥራት አቅደው የነበረው ባልተለመደ ሁኔታ በሱማሌ ክልል እንደነበር ሰነዳቸው ያሳያል፡፡

አቶ አንዷለም አድማው ሻረው፣ አቶ ተከተል በኩ ለማ፣ አቶ ወንድሙ ወልዴ፣ እንዲሁም አሜሪካዊ እንደሆነ የተገለጸ አቶ ብርሃኔ ተሸቴ  የተባሉ ግለሰቦችም በባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ተርታ የኢንቨስትመንት ፍቃዳቸውን ከሚያጡት ዉስጥ ይመደባሉ፡፡

ቀሪዎቹ ከባለ 4 ኮከብ እስከ ቅንጡ ሎጆች ለመገንባት ፍቃድ የወሰዱ የ18 አገራት ዜግነት ያላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ናቸው፡፡

ከሆቴል ንግድ ጋር በተያያዘ መንግሥት ለአልሚዎች ከፍተኛ ማበረታቻ ያደርጋል፡፡ ከነዚህም መሐል ሆቴሉን ሊያስጨርስ የሚያስችል ብረት፣ የግንባታ እቃዎች፣ የማጠናቀቂያ እቃዎች፣ ፈርኒቸር፣ እንደ ሆቴሉ የኮከብ ደረጃ ፒክ አፕና የእንግዳ ማመላለሻ ዘመናዊ መኪናዎች፣ እንዲሁም ለሥራ አስኪያጅ የሚሆን ላንድክሩዘር ፎርዊል ድራይቭ መኪና ይገኝበታል፡፡

ይህን ከፍተኛ የቀረጥ ማበረታቻ በመጠቀም በርካታ ባለሐብቶች በሆቴል ስም የሚያስገቡትን የአርማታ ብረት በብዙ ቶን በማስገባት በጥቁር ገበያ ይሸጡታል፡፡ በዚህ ሂደት በአንድ ጀንበር የበለጸጉ በርካቶች እንደሆኑ ይነገራል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት የባለ አምስት ኮከብ ሆቴል የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ከቀረጥ ነጻ ሐሰተኛ ሰነዶችን በማሰናዳት ያስገቡትን የአርማታ ብረት ለሦስተኛ ወገን በመሸጥ የ150 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘታቸው የተገለጹ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዉለው ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡

መንግሥት ይህንን ሕገወጥ ተግባር ለመቆጣጠር በሚል የሆቴል አልሚዎች ብረት ከአገር ዉስጥ ገበያ ብቻ እንዲገዙ የሚያስገድድ ሕግ ለማውጣት በሂደት ላይ የነበረ ሲሆን ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ እንዲቆም ተደርጓል፡፡ የኢንደስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው ከዚህ ቀደም እንደጻፉት በተነገረ ደብዳቤ የዉጭ ምንዛሬን ለማዳን ሲባልና ሕገወጥ ተግባሮችን ለማስታገስ አልሚዎች አርማታ ብረትን ከአገር ዉስጥ አምራቾች ብቻ እንዲገዙ እንዲደረግ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር፡፡ ኾኖም የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዳይሬክተር አቶ ፍጹም አረጋ የኢንቨስትመንት ማበረታቸው ቀድሞ በነበረው መልኩ እንዲቀጥል በማዘዛቸው ይኸው ተፈጻሚ እየኾነ ይገኛል ይላሉ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትምነት ኮሚሽን ባልደረባ፡፡

4ኛዋ የዲፕሎማቲክ መዲና ብላ ራሷን የምትጠራው አዲስ አበባ 1132 ሆቴሎች ብቻ ሲኖሯት የባለኮከብ ሆቴሎቿ ቁጥር ግን ከ115 አይልቅም፡፡ ከነዚህ ዉስጥ ኢሊሌ፣ ራዲሰን ብሉ፣ ሸራተን፣ ካፒታል ስፓ፣ ጎልደን ቱሊፕ እና ማሪዮት የአምስት ኮከብ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በመዲናዋ ዓለም አቀፍ ብራንድ የሆኑ ሆቴሎች በቁጥር ስድስት ብቻ ነው፡፡